ጠቅላይ ፍ/ቤት በነሃብታሙ አያሌው መዝገብ ላይ ውሳኔ አስተላለፈ | አብረሃ ደስታና ዳንኤል ሺበሺ ወደእስር ቤት ይመለሳሉ
* አብረሃ ደስታና ዳንኤል ሺበሺ ወደእስር ቤት ይመለሳሉ።
* ሐብታሙ አያሌውና የሺዋስ አሰፋ ነፃ ተብለዋል።
——————————————–
* ሐብታሙ አያሌውና የሺዋስ አሰፋ ነፃ ተብለዋል።
——————————————–
ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነፃ ባሰናበታቸው 5ት ተከሳሾች (ሃብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ አብረሃ ደስታ፣ የሽዋስ አሰፋ እና አብረሃም ሰለሞን) ላይ አቃቢ ህግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብሎ አመት ከ3ወር በላይ በቀጠሮ ሲራዘም የነበረው ጉዳይ ዛሬ ብይን ተሰጥቶበታል።
ዳኞች በአራቱ ተከሳሾች ላይ ማለትም፤ ሃብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሺበሺ፣ አብረሃ ደስታ እና የሽዋስ አሰፋ ላይ ከደህንነት መስሪያ ቤት የቀረበባቸውን የሽብርተኛ ድርጅት አባል ከሆኑ ግለሰቦች ጋር ካደረጉትን የስልክ ልውውጥ በመርመር ነው ውሳኔ የሰጡት። በዚህም መሰረት ሃብታሙ አያሌው ያደረጋቸው የስልክ ልውውጦች ሲታዩ በሽብርተኛ ድርጅት የተፈረጁ ድርጅቶች አባላት ጋር የተደረገ ቢሆንም “በሰላማዊ መንገድ ሁኔታዎችን ለመለወጥ እና ዲሞክራሲያዊ ስርአት ስለመገንባት” የሚያወሩ በመሆኑ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ትክክል ነው ብለው በነፃ እንዲሰናበት ወስነዋል።
ዳንኤል ሺበሺ እና አብረሃ ደስታ ከፋሲል የኔአለም ጋር ያደረጉት የስልክ ልውውጥ ሲታይ በክሱ እንደቀረበው የሽብር ተግባር ሊፈፅሙ ባያቅዱም፤ በሽብርተኛ ድርጅት ከተፈረጀው ግንቦት 7 ጋር ሁለገብ ትግል በሚለው ሃሳብ የመስማማት አዝማሚያ እንዳላቸው እና ከሰላማዊ ትግል ባለፈ የመንቀሳቀስ ፍላጎት እንዳላቸው እንደሚያሳይ ገልፀዋል ዳኞቹ። ስለሆነም የፀረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ 7(1)ን የእንዲከላከሉ ሲሉ ብይን ሰጥተዋል።
የሽዋስ አሰፋም እንዲሁ ከፋሲል የኔአለም ጋር ያደረገውን የስልክ ምልልስ እንዳዩት የገለፁት ዳኞቹ፤ የሽብር ድርጊት ለመፈፀምም ሆነ በሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ስለማያሳይ በነፃ እንዲሰናበት ተበይኗል።
አብረሃም ሰለሞንን በተመለከተ የቀረበ የተጠለፈ የስልክ ልውውጥ ከደህንነት የቀረበ ሪፓርት ስላልነበረ፤ በቀረቡት የአቃቢ ህግ ምስክሮችን መሰረት አድርገው ነው ዳኞች ውሳኔውን የሰጡት። ከአቃቤ ህግ ምስክሮች ተከሳሹ በመንግስት ላይ ያለውን ጥላቻ እና በግንቦት 7 እየተሳበ መምጣቱን መመልከት ይቻላል ሆኖም ግን በአባልነት ስለመመልመሉ እና ስለተሳትፎው የተገለፀ ነገር ባለመኖሩ በነፃ እንዲሰናበት ወስኗል።
በዛሬው ችሎት ላለፉት በርካታ ጊዜያት በህመም ምክንያት ችሎት ሳይቀርብ በተወካዩ አማካኝነት ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው ሃብታሙ አያሌው ከህመሙ በመጠኑ አገግሞ በችሎት የተገኘ ሲሆን አብረሃ ደስታ ደግሞ እዛው መቀሌ የሚገኝ ፍርድ ቤት በፕላዝማ ችሎቱን ተከታትሏል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ጥሰሃል በሚል በእስር የሚገኘው ዳንኤል ሺበሺ ችሎት ሳይቀርብ ቀርቷል።
በፀረሽብር አዋጁ አንቀፅ 7(1) እንዲከላከሉ የተበየነባቸው አብረሃ እና ዳንኤል፤ ክሳቸውን አቃቤ ህግ ሲያንቀሳቅስ እና መጥሪያ ከደረሳቸው በኋላ በድጋሚ ወደ እስር ቤት ተመልሰው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን መከታተል እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።
No comments:
Post a Comment