Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, January 4, 2017

ሀገርን የማዳን የመጨረሻ ጥሪ! ምሕረት ዘገዬ (ከአዲስ አበባ)

Image may contain: text

ብዙ የምለው የለም፡፡ ከዚህ በታች ያለው በየድረገፆች ተለጥፎ የሚገኘው የሕወሓት አስገዳጅ ደብዳቤ በግልጽ ከሚናገረው የተለዬ እምብዝም የተለዬ ነገር መናገር አይቻልም፡፡ ደብዳቤው በራሱ ከበቂ በላይ የሆነ የሀገር ዘረፋ መግለጫ ነው፡፡ ሀገር በደብዳቤ እየተዘረፈች ማለቋ ነው፡፡ በህግ ሽፋን የሚደረግ የለዬለት ሀገርን ራቁት የማስቀረት ዘረፋ እየተካሄደ ነው! ባንክን መዝረፍ፣ ግምጃ ቤትን መዝረፍ፣ ቋሚና ተንቀሳቃሽ የሀገርና የሕዝብ ንብረትን መዝረፍ፣ መሬትን መዝረፍ… ዜጎችን ማሰር… ማሰቃየት… መግደል… ደብዛ ማጥፋት… ማስራብ… ማጋዝ… ማሳደድና ማሰደድ… መቼም በማይረካ የዘረፋና የግድያ ሱስ ተጠምደው ሀገርን ማፍረስ የወያኔዎች ልዩ ባሕርይ እንደሆነ ወደዕድሜያቸው ጫፍ ደረሱ፡፡ እኛም እነሱም ስናሳዝን!
የደብዳቤው ኦሪጂናል ቅጅ በደንብ የሚነበብ ቢሆንም ከፎቶው ላውጣውና በግልጽ ላስነብባችሁ፡-
ጉዳዩ፡- በቋሚ ኤግዚቢሽን የሚቀመጡ ቅርሶችን አሰባስቦ መላክን ይመለከታል፡፡
የአብክመ [የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት] ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በትግራይ ክልል አዲገዛኢ በሚባል አካባቢ የአገራችንን ብሔር ብሔረሰቦች መገለጫ የሆኑ ቅርሶችን በአንድ አካባቢ አሰባስቦ ማስጎብኘት ይቻል ዘንድ አገር አቀፍ ሙዜም አስገንብቶ ፍጻሜ ላይ ማድረሱን በመግለጽ በዞናችን የህብረተሰቡን ማንነት ገላጭ የሆኑ ቅርፆችን በማሰባሰብ እስከ ታህሳስ 15/2009 ዓ.ም ድረስ ለክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንድናስረክብ በቁጥር ባ/ቱ 322/09 በቀን 23/3/2009 ኣ.ም (ዓ.ም) በተጻፈ ደብዳቤ አሳውቆናል፡፡ ስለሆነም ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የህብረተሰቡን ባህል ማስተዋወቅ እንዲቻል በእናንተ በኩል በተቻለ ፍጥነት ቁሳቁሶቹ ተሰባስበው እንዲላኩ እንዲደረግ እናሳውቃለን፡፡
ከሰላምታ ጋር
ሙላቱ አሩጋው
አያድርስ ከማለት ውጪ ምን ይባላል?
ይህን ደብዳበ ሳነብ ጠላታችሁ ክው ይበል ክው ነው ያልኩት፡፡ የሕወሓት ዐይናውጣነት፣ ትዕዛዙን ተቀብሎ ይህን ደብዳቤ የጻፈው ሰው ድፍረት፣ ይህን ደብዳቤ ከመዝገብ ቤት ያወጣው ሰው ድፍረት፣ ይህን ደብዳቤ ወስዶ ለየብሔር ብሔረሰቡ ያደለው ሰው ድፍረት… በጣም አስደምሞኛል፤ አሳምሞኛልም፡፡ ሰው እንዴት የገደል ማሚቶ ይሆናል? “ኧረ ይሄስ ይቅርብን፤ ያዋርደናል፣ ‹ያስፎግረናል›፣ ይህንስ እንተወው!ግዴለም…” ብሎ የሚመክር አንድ አስተዋይ ወያኔ እንዴት ይጥፋ? እንዲህ ያለ አንድ ሰው እንኳ መጥፋቱ እኮ ራሱ ያስጨንቃል፡፡ ወያኔዎች አንጎል የሚባል ነገር ከነጭራሹ የላቸውም ማለት ይሆን እንዴ – የዶሮ ታህል እንኳን? ሌሎቻችን በዞረብን “ድግምት” ምክንያት በስማም እንደተባለበት ሰይጣን ለጊዜው ብንፈዝ ከወያኔዎች መካከል አንዱ እንዴት በጎ ነገር ማሰብና ይህን የሞኝነት ሥራ ማስቆም አልሞከረም? ሁሉ ነገር መቼስ እንዳለ አይቆይም፡፡ ታዲያ ይህ ነገር ጨለማው ሲነጋ በነገው ቀን አያሳፍርም?እጅግ ያሳፍራል እንጂ! ይታያችሁ – ወያኔ ትግሬ ለአማራ ባህል ተጨንቆ የአማራን ቅርስ ወደ ትግራይ ወስዶ ሲጠብቅ፡፡ ይህ የወያኔ ሁኔታ ጅብ “አነ አአምር ግብሮሙ ለቆራዕብት” (የቆዳን ነገር ለኔ ተውልኝ) ብሎ ቆዳን ከቆዳ የመለየቱን ተግባር ለብቻው እንዲሰጠው የጠየቀበትን ሁኔታ ያስታውሰኛል፡፡
ልብ አድርጉ! በደብዳቤው መሠረት ሙዚየሙን ትግራይ ውስጥ አዲገዛኢ (ስሙ ደስ ሲል!) በሚባል አካባቢ ያስገነባው የአማራ ክልላዊ መንግሥት ነው፡፡ ወያኔዎች ተሸውደዋል – ወይም መሸወድ ምን እንደሆነ አያውቁም፡፡ የአማራ መንግሥት ከመነሻው የትግራይን መንግሥት ለምን የቅርስ ማስገንቢያ ቦታ ይጠይቃል? የአማራ መንግሥት በየትኛው ሥልጣኑስ ነው ሙዚየም ትግራይ ውስጥ የሚያስገነባው?  መገንባትም ሆነ ማስገንባትስ ቢፈልግ በአማራው አካባቢ ቦታ ጠፍቶ ነው ትግራይ ድረስ ሄዶ የሚገነባው? ምን ዓይነት ወያኔያዊ ደደብነትና ዕብሪት እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ እነዚህን ሰዎች ጭንቅላታቸውን ጮማ ደፍኖት ጥቂትም ማሰብ የማይችሉበት የትምክህት ወይም የዕብደት ደረጃ ደርሰዋል ማለት ነው፡፡
ቅርሶቹን በአስቸኳይ ሰብስቡ ይላሉ – “በተቻለ ፍጥነት ቁሳቁሶቹ ተሰባስበው እንዲላኩ…” በማለት ፡፡ ምን አስቸኮላቸው? የሰሙት ነገር ይኖር ይሆን? የምን ጥድፊያ ነው? የሌባ ነገር … ሌባ ቀልብ የለውም ዱሮም፡፡
የአማራው ቅርስ ለትግሬው ምኑ ነው? የአክሱሙ ሐውልት ለወላይታው ምኑም አይደል እያሉን አይደለምን? ምን ዓይነት ዕንቆቅልሽ ነው? ጄኖሳይድና ዘር ማጽዳት ያወጁበት ነገድ ቅርሱ ምን ይሠራላቸዋል? ከጠሉ ከነቅርሱና ከነሀብቱ እንጂ እንዲህ ያለ ግንጥል ጌጥማ ነውር ነው፡፡ ለነገሩ በወያኔ መንደር ሀፍረትትም ሆነ ይሉኝታ የሚባል ቃሉም ስለሌለ አይፈረድባቸውም፡፡
በጣም ደስ የምትለዋ የወያኔ የኩምክና ቃል ማለትም አባባል ደግሞ ይቺውና – “ስለሆነም ይህን አጋጣሚ በመጠቀም የህብረተሰቡን ባህል ማስተዋወቅ እንዲቻል…” – “ይህን ወርቃማ አጋጣሚ በመጠቀም …” ብለው ቢያሻሽሉት ደግሞ ወርቅ ነበር፡፡ “የሞኝ ፍቅር ሆድ ይገትር” የሚባለው እውነት ነው፡፡
ግን ግን ይህ ጊዜ – ይህ አጃኢበኛ ዘመን – ይህ የቁጭበሉ ጩልሌዎች ዘመን ያልፍ ይሆን? ፈራሁ፡፡
ጭፍን ታዛዦች ንብረቶቻችንን ሁሉ እንዳያዘርፉን ፈራሁ፡፡ ከሦስት ሺህ ዓመታት በላይ በፈጀ የታሪክ ሽመና ዘመን ያፈራናቸው ቅርሶቻችንና የትውልድ አሻራዎቻችን በነዚህ የኢትዮጵያ አይሲሶች ተሰብስበው እንዳይወድሙብን በጣም ፈራሁ፡፡ ትግራይ ውስጥ መከማቸታቸው በራሱ – እስካልወደሙ ድረስ – ምንም አይደለም – ጊዜው ሲደርስ ወደየመጡበት ይመለሳሉና፡፡ የአክሱም ሐውልትስ ከሩቅ ሀገር ከጣሊያን መጥቶ የለምን? ከጠፉና ከወደሙ ግን መቼም አይገኙም፡፡ ያን ነው መጠንቀቅ፡፡ ዋስትና ደግሞ የለንም፡፡
ይህን የዘረፋ ዘመቻ ለማክሸፍ በተለይ ሀገር ውስጥ ያለውና በቅርሶቹ አካባቢ የሚገኘው ዜጋ ትልቁን ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡ የታሪክ ተጠያቂነትና ኃላፊነትም እንዳለበት ማወቅ አለበት፡፡ ዛሬ ቁጭ ብሎ በሚያዘርፈው ቅርስ ነገ እሱ ባይኖር ትውልዱ ይጠየቅበታል፤ ያፍርበታልም፡፡ የጣሊያን ባንዳዎችና ልጆቻው ዛሬ ድረስ የሚወቀሱትና የሀፍረት ሸማ ተከናንበው ቀጥ ብለው የማይሄዱት አባቶቻቸው በሠሩት መጥፎ ሥራ ምክንያት ነው፤ እርግጥ ነው የአሁኑን ሀገራዊ ሥልጣን የያዙት እነሱ ስለሆኑ ለጊዜው ሀገራችን በነሱ ቁጥጥር ሥር ናትና የኛ ድምፅም ሆነ ኃይልና ጉልበት ተደብቋል፤ ተደብቋል ማለት ግን እስከወዲያኛው ጠፍቷል ማለት እንዳልሆነ ሊሠመርበት ይገባል – ኃይልና ጉልበት ለተወሰነ ጊዜ ይደበቃል እንጂ አይጠፋም – የአንዱ ኃይል አንዴ ይገናል ሌላ ጊዜ ይደክማ፤ የወር ተራ ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉም በጥሞና ሊያስብበት የሚገባው ትልቁ ቁም ነገር ግና ማንም ቢሆን ጊዜ የሚሰጠውን ዕድል አላግባብ በመጠቀም ጠላት ማፍራትና በዑደታዊ የቂምበቀል አዙሪት መዘፈቅ የሌለበት መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያ እንዲህ እንደሆነች አትቀርምና ሁሉም በሠፈረው ቁና እንደሚሠፈር ተረድቶ ከአሁን በኋላ ሌላ አሳፋሪ የታሪክ ስህተት ላለመሥራት እያንዳንዱ ዜጋ መጠንቀቅ ይገባዋል፡፡ ይህ እውነት፣እውነት ነው፡፡
ይህን የወቅቱን የወያኔ የቅርስ ዘረፋ ግን በጥርሳችንም በጥፍራችንም ታግለን ማክሸፍ ይኖርብናል፡፡ ትግሬዎች በተለይ በዚህ ዘመቻ ግምባር ቀደም መሆን ይገባችኋል ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምን ቢባል የዚህ ዘረፋ ቀጥተኛ ተጠቂ እናንተ ናችሁ፡፡ ዘረፋውን የሚያካሂዱት በዋናነት የሕወሓት አባላት ቢሆኑም ቅርሱ የሚገኘው በእናንተ ጓዳ ውስጥ መሆኑ በራሱ ትልቅ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል መገመት ይገባችኋል፡፡ እርግጥ ነው – በዕንቁላልነቱ ያልቀጣችሁት (ምናልባትም ያልቀጣነው) ሕወሓት ከአሁን በኋላ የናንተንና “የኛን” ቀርቶ የፈጣሪን ተግሣጽና ምክር ሊሰማ አይችልም – ያዳቆነ ሰይጣን – አንዳንዴ – ሳያቀስ አይለቅም፤ ሕወሓት በጀመረው የጥፋት ጎዳና ተጉዞ ወደማይቀርለት ከርሠ መቃበር ይወርዳል እንጂ ከጥፋቱ በጭራሽ አይመለስም፡፡ የትግራይ ሕዝብ ግን ቀሪ ነውና፣ የኢትዮጵያም አንዱ ሀብት ነውና ከነዚህ የጠፉ ልጆቹ/”ቻችን” ራሱን በተቻለው ፍጥነት መነጠል ይኖርበታል፡፡ ሁለት ነገር በአንዴ ሊወደድ አይችልምና ከሌላው ሕዝብ ጋር በአንድ ልብ በመታገል እነዚህን የታሪክና የሕዝብ ምስጦች ማስወገድ ይገባል፡፡ በታሪክ ጉዞ “ረፈደ” የሚባል ወቅት እምብዝም የለም፤ “ጨርሶ የለም” ማለት ግን አይደለም – የሰይጣን ጆሮ ይደፈን እንጂ አለ፡፡ ሦርያን እንይ፤ ሶማሊያን እንመልከት – እነዚህ ዕድለቢሶች እየተሰቃዩ ያሉት ረፍዶባቸው ነው፡፡
እንኳን ከፎከረ ከተወረወረ የሚያድነው እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ከዳግም ሞት ይሠውራት፤ ወያኔንም  በክፉ ሥራችን ምክንያት – እደግመዋለሁ – በክፉ ሥራችን ምክንያት እርሱ እንዳመጣብን እርሱው ይገላግለን፡፡ አዎ፣ ክፉ ነን፡፡ ከቤታችን ጀምረን እስከአደባባይ ለሰው የማንመች፤ ከምቀኝነት ያልጸዳን፣ የሰው ማደግ የሚያናድደን፣ የጓደኛችን መሻሻል በቅናት የሚያበግነን፣ በየጠንቋዩና በየመጣፍ ገላጩ ቤት ለሰውኛ ሰይጣናት እየተጎናበስን ለብዙዎች ሞትና ጉስቁልና አንጡራ ሀብታችንን የምናፈስ… የክፉ ክፉዎች ነን፡፡ እንደጠባያችን መክፋት ወያኔም ሲያንሰን ነው የሚያስብሉን ግለሰብኣዊና ማኅበራዊ የክፋት መገለጫ አመለካከቶቻችንንና ድርጊቶቻችንን ዘርዝረን መጨረስ አንችልም፡፡ እርግጥ ነው ሁላችንም አይደለንም – ቢሆንም ጥቂት አይደለንም፡፡ አስደንጋጩ እውነት ደግሞ ቁጥራችን እየቀነሰ ከመሄድ ይልቅ አሁን አሁን በተለይ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መጥቶ እንደዲዮጋን በጠራራዋ ፀሐይ ላይ ፋኖስ ጨምረን ብንፈልግም ደህና ሰው ማግኘት እያቃተን ነው፡፡ ለማንኛውም ቻው፡፡  ግን  – የምልህ ነገር እውነቴን ነውና አትናደድ፡፡ ዝርዝር ኪስን ብቻ ሣይሆን ኅሊናንም እየቀደደ ተቸገርን እንጂ አውሎ የሚያሳድር ገመናችንን ልነግርህ በቻልኩ፡፡ ቻው በድጋሚ፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials