Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, July 3, 2015

የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲወጡ ሌላ ክስ የተመሠረተባቸው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በዋስ ተለቀቁ



የአይኤስ አሸባሪ ቡድን ሊቢያ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ላይ በፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ምክንያት መንግሥት በጠራው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ረብሻ በመፍጠር ተከሰው የተፈረደባቸው የሰማያዊ ፓርቲ አባላት፣ የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲወጡ ከማረሚያ ቤት በራፍ ላይ ተይዘው ከተመሠረተባቸው ክስ በዋስ እንዲለቀቁ ብይን ተሰጠ፡፡

የፓርቲው አባላት ሰኔ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. እያንዳንዳቸው በ5,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቄራ ምድብ ችሎት ብይን የሰጠው በወይንሸት ሞላ፣ በኤርሚያስ ፀጋዬ፣ በዳንኤል ተስፋዬና በቤተልሔም አካለ ወርቅ ላይ ነው፡፡

በተከሳሾቹ ላይ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ተሰጥቶ የነበረው፣ ሰላማዊ ሠልፉን በማወክ የተለያዩ ስድቦችን መንግሥትንና ዜጎችን በመሳደብ፣ ሥርዓቱን በማንጓጠጥና በፖሊስ አባላት ላይ ድንጋይ በመወርወር ወንጀል ተከሰው ነው፡፡

ፍርደኞቹ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፍርድ በቀረቡበት ዕለት ሁለት ወር ከአንድ ቀን በእስር መቆየታቸው በመረጋገጡ፣ በዕለቱ ከእስር እንዲፈቱ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም ፖሊስ ሌላ ወንጀል መፈጸማቸውን በመግለጽ፣ ሰኔ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. ከእስር ተፈትተው ወደ ቤታቸው ለማምራት ማረሚያ ቤት ደጃፍ ላይ ሲደርሱ ተይዘው ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል፡፡

ፖሊስ ለፍርድ ቤት ያቀረበው ክስ፣ ተከሳሾቹ ቀደም ብሎ በተከሰሱበት ወንጀል ላይ በምስክርነት ያቀረባቸውን ማስፈራራታቸውንና መዛታቸውን በመግለጽ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ክሱን ተቀብሎ ለሰኔ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. መዛታቸውን የሚያስረዱለትን ምስክሮቹን እንዲያቀርብ ቀጠሮ የሰጠ ቢሆንም፣ ፖሊስ ምስክሮቹን በተለያዩ ምክንያቶች ሊያቀርብ አለመቻሉን ገልጾ፣ ተጨማሪ ጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል፡፡

ተከሳሾቹ ግን ፖሊስ ምስክሮቹን በተሰጠው ቀጠሮ ቀን ማቅረብ እንደነበረበት ገልጸው፣ ፍርድ ቤቱ ዋስትና እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ጥያቄውን ተቀብሎ እያንዳንዳቸው በ5,000 ብር ዋስ እንዲለቀቁ ፈቅዷል፡፡ በሌላ በኩል ተከሳሾቹ ቀደም ብሎ ሰኔ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ሁለት ወራት ተፈርዶባቸው በነበረውና እስራቸውን ጨርሰው በወጡበት ክስ፣ ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ እንዳለባቸውና ሰኔ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል፡፡

ምንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment

wanted officials