በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቆጠራ ቤቶችን በህገ ወጥ መንገድ ሲገለገሉ የተያዙ ከ60 በላይ ሰዎች ክስ ሊመሰረትባቸው መሆኑ ተነግሯል።
በቆጠራው ቁልፍ በመስበር እና አጠገብ ያሉ ሰው አልባ ቤቶችን መሃል ላይ ያለ መለያ ግንብን አፍርሶ በመቀላቀል በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ 60 ቤቶች ተገኝተዋል።
እስካሁን ከተቆጠሩት 44 ሺህ ቤቶች መካከል በ1 ሺህ 239 ሰው አልባ ቤቶች መገኘታቸውም ተነግሯል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ይድነቃቸው ዋለልኝ፥ በህገ ወጥ መንገድ ቁልፋቸው ተስብሮ በግለሰቦች እጅ የተገኙ 60 ቤቶች መገኘታቸውንና ግለሰቦቹም በቁጥጥር ሰር መዋላቸውን ተናግረዋል።
በዚህ መንገድ ቤትን ከመንግስት ዘርፈው ይኖሩ የነበሩ ግለሰቦች ለህግ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ እንደሚደረግም ሃላፊው አስታውቀዋል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በሚመቻቸው መንገድ ከፋፍለው የሚጠቀሙ የቤት ባለቤቶች ተጠያቂ እንደማይሆኑ የገለጹት ሃላፊው፥ ከዚህ ውጭ የጋራ መተላለፊያ ኮሪደር ላይ አጥርን ጨምሮ ሌሎች ግንባታዎችን ያካሄዱ ግን ይጠየቃሉ ብለዋል።
በእስካሁኑ ሂደት ሁለት እና ከዚያ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በስማቸው ይዘው የተገኙ ሶስት ግለሰቦች መኖራቸው ተደርሶበታል ነው ያሉት አቶ ይድነቃቸው።
በዚህም እስካሁን ከሶስቱ ግለሰቦች በስተቀር ሌሎች ሁለት እና ከዚያ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በስማቸው ይዘው የተገኙ ሰዎች የሉም ያሉት ሃላፊው፥ እንዲህ ያለው ድርጊት ግን ሊኖር እንደሚችል እና በቀጣይ መሉ ቆጠራው ከተከናወነ በኋላ መረጃው በመረጃ ቋቱ ውስጥ በሚገባበት ጊዜ ለዚህ ሲባል በተዘጋጀ ሶፍት ዌር እንደሚጋለጥ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
በቆጠራ ሂደቱ ህብረሰተቡ በጥቆማ ቤቱን በማስቆጠር ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፥ ቆጠራውን ለሚያከናውኑ ባለሙያዎች ቤቱን ከመከራየታቸው በስተቀር ያከራየቸውን ሰው የማያውቁ ተከራዮች በብዛት መገኘታቸው በሂደቱ እየገጠመን ያለ ችግር ብለው ጠቅሰውታል።
በእስካሁኑ ቆጠራ አስፈላጊ የሆኑ ውሎች የተፈፀመበት፣ የባንክ ክፍያ የተፈፀመባቸው ሰነዶችን ማቅረብ ያልቻሉ ጥቂት ጊዜ የተሰጣቸው ግለሰቦች ስነዶቹን በአጭር ጊዜ ወስጥ ካላመጡ ቤቶቹ በህገ ወጥ መንገድ እንደተያዙ እንደሚቆጠርም አስጠንቅቀዋል።
ሰነድ የጠፋባቸው የቤት ባለቤቶች ካሉም በየክፍለ ከተሞች በሚገኙ የቤት አስተዳደር ፅህፈት ቤቶች እና ቅድመ ክፍያውን በፈፀሙበት የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ ሰነዶቹን ዳግም በማውጣት ለቆጠራ ባለሙያዎች እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል።
ቢሮው ከዚህ በኋላ የቤት ቆጠራው የሚካሄድባቸው የቦሌ፣ ንፋስ ሰልክ ላፍቶ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ኮልፌ እና የካ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ሳይቶች ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤት ባለቤቶችም የታደሰ መታወቂያን ጨምሮ አስፈላጊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነዶችን ከወዲሁ አሟልተው መጠበቅ እንዳለባቸውና ቆጠራው እስከ መጋቢት 20 ብቻ እንደሚካሄድም አሳውቋል።
ቆጠራው ከተጀመረ ሁለተኛ ሳምንቱን የያዘ ሲሆን፥ በአንድ ወር ከግማሽ ጊዜ ወስጥ ይቆጠራሉ ከተባሉት 102 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ወስጥ የ42 በመቶው ቆጠራ መጠናቀቁንም ተገልጿል።
በቆጠራው መርሃ ግብር መሰረት ከ5 ሺህ በታች የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባላቸው ክፍለ ከተሞች የሚካሄደው ቆጠራ የፊታችን አርብ ይጠናቀቃል።
ባለፉት አስር ቀናት በተካሄደው ቆጠራ የአራዳ ክፍለ ከተማ ያሉ ቤቶች ቆጠራ የተጠናቀቀ ሲሆን፥ በቂርቆስ፣ ልደታ፣ ጉለሌ፣ የካ እና አዲስ ከፍል ከተሞች የሚገኙ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቆጠራም እስከ አርብ ይጠናቀቃል።
ከ5 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚገኙባቸው ክፍለ ከተሞች ቆጠራ እስከ መጋቢት 20 እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል።
ኤፍ.ቢ.ሲ
No comments:
Post a Comment