አል አህራም የተባለው የግብጽ የመረጃ መረብ እንደዘገበው ግብጽ በኢትዮጵያ በመገንባት ላይ የሚገኘውን ግድብ ለመከታተል ያስችላት ዘንድ ቀደም ብላ ሳታላይት ተከላለች:: ግብጽ በተተከለው ሳታላይት አቅም ደስተኛ ባለመሆኗ ግድቡን በተመለከተ የተሻለ መረጃ ያቀብለኛል ያለችውን አዲስ ሳታላይት መትከሏን የአገሪቱ የሳታላይት ባለስልጣናት ይፋ አድርገዋል፡፡
በኢጂሳት የተተከሉት ሳታላይቶች የግድቡን ሁኔታ የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ሲያቀርቡ መቆየታቸው የሚታወቅ ቢሆንም የግብጽ የህዋ ሳይንስ ብሄራዊ ባለስልጣን ምክትል ፕሬዘዳንት አላ አል ዲን አዲሱ ሳታላይት በጣም ዘመናዊ የሆኑ ካሜራዎች የተገጠሙለት በመሆኑ ግድቡንና በወንዙ አካባቢዎች የሚካሄዱ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን ያቀርባል” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚያመነጭ የምትናገርለት ግድብ ግማሽ ያህሉ መጠናቀቁን መንግስት እየገለጸ ባለበት በዚህ ወቅት ግብጽ በበኩሏ ግድቡ ወደ አስዋን ግድብ ይገባ የነበረውን አመታዊ የውሃ መጠን ይቀንሳል የሚል ስጋት ገብቷታል፡፡
ኤል ዲን ሳታላይቱ የሁለት ወራት ሙከራ ካደረገ በኋላ ሙሉ ለሙሉ በመጪው ሰኔ ወር ስራውን ይጀምራል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡የግድቡን መጠን፣ውሃ የመያዝ አቅም፣ውሃ የሚለቅበትን ሁኔታና ኮንጎ በናይል ወንዝ ላይ ለመስራት ያቀደችውን ግድብም የተመለከቱ መረጃዎችን ያቀርባል ተብሎለታል፡፡
ሳተላይቱ ለግብጽ ግድቡን በተመለከተ አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ በመሆን እንደሚያገለግል የሚናገሩት ባለስልጣናቱ ምናልባት በተስማማንባቸው ጉዳዩች ዙሪያ ግድቡ የማይሄድ ከሆነም ወደአለምአቀፍ ፍርድ ቤቶች ከሄድን ከሳታላይቱ የምናገኘው መረጃ ማስረጃ ሊሆነን ይችላል ማለታቸውን አል ሃራም ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያ ግብጽ ተከለቻቸው ስለሚባሉ ሳታላይቶች እስካሁን የሰጠችው ምንም አይነት አስተያየት የለም፡፡
No comments:
Post a Comment