አምነስቲ ኢንተርናሽናል ኖርዌይ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ተገዢ እንድትሆን ጠየቀ
ኢሳት (የካቲት 18 ፥2008)
የኖርዌይ መንግስት በመቶዎቹ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ያለፍላጎታቸው ወደሃገራቸው ለመመለስ የያዘውን እቅድ ተከትሎ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሃገሪቱ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ተገዢ እንድትሆን አሳሰበ።
ሃገሪቱ በስደተኞች ላይ እየያዘች የመጣችውን አዳዲስ አቋሞች የተቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ኖርዌይ ለአለም አቀፍ ህግጋት ተገዢ ያለመሆን አቅጣጫ እየተከተለች እንደሆነም አስታውቋል።
ኖርዌይ ተግባራዊ ለማድረግ ያሰበችውን የስደተኞች አዲስ እቅድ ምክንያት በማድረግ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ከ500 የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን ያለፍላጎታቸው ወደሃገራቸው ለመመለስ መወሰናቸውን የኖርዌይ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንስ ስቶልተንበርግ ስደተኞችን በአግባቡ ለመለየት በሚደረገው አካሄድ ወደሃገራቸው የሚመለሱ ሰዎች እንዳሉ በቅርቡ ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይሁንና፣ ስደተኞችን ያለ-ፍላጎታቸው ወደሃገራቸው እንዲመለሱ ማስገደዱ ተገቢ አይደለም በሚል የተለያዩ አካላት በኖርዌይ መንግስት ላይ ቅሬታን እያቀረቡ የሚገኙ ሲሆን ውሳኔውም ማሻሻያ እንዲደረግበት አሳስበዋል።
በኖርዌይ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ፀሃፊ የሆኑት ጆን ፔደር ሃገሪቱ ልትነፃፀር የማይገባቸውን ሃገራት ድርጊት እየተከተለች ነው ሲሉ ተቃውሞ ማቅረባቸውን ኖርዌይ ቱዴይ የተሰኘ ጋዜጣ ዘግቧል።
“እርምጃው አስፈሪ ነው” ሲሉ የገለጹት ሃላፊው ሃገሪቱ በስደተኞች ላይ የያዘችውን ዘመቻ በአስቸኳይ እንድታጤነው ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ኖርዌይ ዜጎቿ በክልሉ እንዳይንቀሳቀሱ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያን ስትሰጥ መቆየቷ ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment