Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, March 31, 2016

ተስፋሁን አለምነህ በህይወት ባይኖር ምን ልናደርግ ነው?በዳዊት ሰለሞን if there is no Tasfahun in life


Tsefahun-Alemenehew-G7-768x576
በዳዊት ሰለሞን
የቀድሞው የመኢአድ የህዝብ ግኑኝነት ተስፋሁን አለምነህ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የነበረውን የጸና እምነት በመቀየሩ ሳይሆን መንገዱ በስርዓቱ አንጋሾች ፈጽሞ ዝግ መሆኑን በሂደቱ በመሳተፍ በመመልከቱ ስርዓቱን በሚገባው ቋንቋ ለማናገር ወደ ኤርትራ በረሃ ወርዷል፡
ተስፋሁን በተለይም መኢአድና አንድነት ባህር ዳር ከተማ አድርገውት ከነበረ ደማቅ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ በኋላ በጣም የቅርቤ የምለው ጓደኞዬ ወጥቶት ነበር፡፡ለፓርቲው፣ለፕሮፌሰር አስራትና ለአገሩ የነበረውን ፍቅር አሁን በኮምፒውተር ኪቦርድ ለመተየብም እቸገራለሁ፡፡
ወጣቱ ፖለቲከኛ ከሰላማዊ ትግል ይልቅ የብረት ትግል እጅግ ቀላሉ ስለመሆኑም ከመናገር ተቆጥቦ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡በብረት በሚምሉ ወታደራዊ ገዢዎች ፊት እንደ አስራት፣አንዱዓለም፣ናትናኤል፣እስክንድርና ብዙ ሺህዎች ባዶ እጅን በፍቅር ተሞልቶ እንደመፋለም ፈታኝ ነገር እንደሌለም አጥብቆ ይናገር ነበር፡፡
ኢህአዴጎች በብረት ተወልደው በብረት ስልጣን በመያዛቸውም ያለ ብረት የሚደረግባቸውን ትግል መቋቋምና እንዴት ሊቀርቡት እንደሚገባም ባህሪውን ስለማያውቁት በለመዱት የኃይል መንገድ ጨካኝ ሆነው መገለጣቸው ተስፋሁንን ያስቆጨውም ነበር፡፡
በኢትዮጵያ በ2007 ለሚደረገው ብሄራዊ ምርጫ ከፓርቲው ጋር ብዙ ተስፋን ሰንቆ የነበረው የህዝብ ግንኙነቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድ የምርጫ መወዳደሪያ ምልክት በመቅረብ ገዢውን ግምባር በሰላማዊ መንገድ እንዲፋለሙት ለማድረግ የቻለውን ያህል ብዙ ርቀት ተጉዟል፡፡ያሰበው አለመሆኑና ኢህአዴግም ከብረቱ ለመነጠል አለመፍቀዱን የምርጫውን ውጤት ጠቅልሎ በመውሰድ በማሳየቱ ተስፋሁንን ወደሌላኛው የትግል ጫፍ ገፋው፡፡
ተስፋሁን ኤርትራ ወርዶ በዚያ የሚገኙ የቀድሞ የትግል ጓዶቹን በመቀላቀሉ በቁርጠኛው ወጣት ድርጊት አላዘንኩም፡፡ያዘንኩትና እጅግ ያፈርኩት የትጥቅ ትግሉን በር ወለል አድርጎ በከፈተው ኢህአዴግ ነው፡፡ከተስፋሁን አጠገብ ቁጭ ብለው ኢህአዴግን በመወከል በምርጫ ወቅት የተከራከሩት የኢህአዴግ ባለስልጣናት የተስፋሁንን በረሃ መውረድ ሲሰሙ በረሃውን እጅግ ቅርብ ማድረጋቸውን በማሰብ መደበቂያ ጥፍር መፈለግ ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ፡፡ራሴን በእነርሱ ጫማ ባስቀምጠውም ይህንኑ ለመናዘዝ የምደፍር ይመስለኛል፡፡
እርግጥ ነው ስርዓቱ ስልጡኑን የፖለቲካ መንገድ በጉልበቱ ዘግቶ ካበቃ በኋላም ቢሆን በተስፋሁን ካምፕ ተሰባስበው የነበሩ ስልጡኖችን ‹‹በምትፈልጉት ቋንቋ አናግራችኋለሁ ፣ወንድ ከሆናችሁ ጫካ አትወርዱም››እያለ የወንድ የሚለው መንገድ እርሱን ብቻ አራት ኪሎ የሚያደርሰው መስሎት ብዙዎችን ገፍቷል፡፡ብርሃኑ ተ/ያሬድና ሌሎችም በሰፊው መንገድ ለመሄድ መነሳታቸውን እዚህ ማስታወስ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
እነተስፋሁን የመረጡት መንገድ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳዝን አይደለም፡፡በኢትዮጵያ የሚገኘው ስርዓት ዋነኛው የትጥቅ ትግል ሰባኪ ነው፡፡እውነቱን ለመናገር ማዘን የሚገባን ፈጽሞ ዝግ በተደረገው መንገድ አምባገነኑን ስርዓት ለመታገል የሚነሱ ፍጹም ሰላማዊያን ዜጎችን ስንመለከት ነው፡፡ላለፉት 25 ዓመታት በተናጠልም ይሁን በቡድን ተሰልፈው ህግና ህጋዊነትን ተስፋ አድርገው የተነሱ ዜጎች ተስፋ ባደረጉበት ህግ ተጠልፈው ከመንገድ ቀርተዋል፡፡
የስርዓቱ ጅቦችም ከብዕር፣ከወረቀትና ከመግለጫ ጋር ያገኟቸውን ነፍጥ አልባዎች በጭካኔያቸው ከልባቸው የሰላማቸውን እርግብ ለመግደል ወረቀት የማይችለውን በደል አድርሰውባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሰላማዊ ትግል በበኩሉ በየዓመቱ የሚነሱለትን አብሪዎች በጨለማ እያስዋጠ እንደገና ወደመጀመሪያው ይመለሳል፡፡ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ፡፡በዚህ መንገድ ለማለፍና ህዝብን የስልጣን ባለቤት ለማድረግ አንዳች ቡዳ የበላቸው ወጣቶች፣ዕድሜ ጠገቦችና የቀድሞው ትውልድ ቅሪቶች መስዋዕትነታቸውን የሚለካላቸው አካል ሳያገኙ እንኳን ሲላቸው አገር አልባ፣ህይወት አልባ፣ነጻነት አልባ ሆነው ይደበዝዛሉ፡፡
ተስፋሁን በዚህ እንዲታሰብና ‹‹አንድ ትንታግ ወጣት ፖለቲከኛ ነበር››እንዲባልለት ባለመፍቀዱ ገዢው ግምባር ወደከፈተው የትግል መስመር ወጣ፡፡ጤነኛ አእምሮ ያለው አካልስ በተስፋሁን የትግል ምርጫ እንዴት ቂም ሊቋጥር ይችላል? እረ እንዴት ተስፋሁንን ከተራራ ላይ እንደወደቀ ስባሪ ሊቆጥረውስ ይዳዳዋል?
አገር ወዳድና ልበ ሙሉ የነበረው ተስፋሁን ኤርትራ ከወረደም በኋላ ረዘም ላሉ ወራቶች በፌስ ቡክ አካውንቱ  ይጠቀም ስለነበር የወዳጅነታችንን መነጋገራችን አልቀረም ፡፡ለትግል ወርዶ በማህበራዊ ገጹ ስለመጠቀሙ ስጠይቀውም ‹‹ገና ስልጠና ባለመጀመሩ እንዲጠቀም እንደተፈቀደለት ይነግረኝ ነበር፡፡ከማህበራዊ ድረ ገጽ ሳጣውም መጥፋቱ ስለሌሎች ነገሮች እንዳስብ አላደረገኝም፡፡
የሆነስ ሆነና ተስፋሁን ተገድሏል ወዘተ የሚሉ ድምጾችን በማህበራዊ ድረ ገጾች መመልከቴ አልቀረም፡፡ይህ ጥያቄ በተነሳ ቁጥርም ለምን ይሆን ሰዎቹ ስለተስፋሁን ለማወቅ የተጨነቁት የሚል ጥያቄ ውጥር ያደርገኛል፡፡ተስፋሁን እንዳሉት (አያድርግበትና)ተገድሎ ቢሆን እነዚህ ጠያቂዎቹ ምን ሊያደርጉ ነው?ተስፋሁንን መፈለጋቸውን ይነግሩናል እንጂ ለምን እንደፈለጉት አንዳቸውም እንኳን እስካሁን አልነገሩንም፡፡
ተስፋሁን በእኔ እምነት ቢገደልም በህይወት ቢኖርም ተጠያቂው ኢህአዴግ ነው፡፡ይህን ትንታግ ወጣት ሻዕቢያ ገደልኩት ቢለኝ እንኳን በተከሳሾች ወንበር ልናቆመው የሚገባን ገዳይ ኢህአዴግ እንደሚሆን ይሰማኛል፡፡በህይወት ኖሮም ዘመኑን በበረሃ ቢያሳልፍ ለዚህ ተጠያቂ መሆን ያለበት ወታደራዊው ስርዓት ነው፡፡
እናም የሚሻለው ተስፋሁንና ሌሎች ብዙ ሺህዎችን ‹‹ውለድ››ብለን ኢህአዴግን እንጠይቀው፡፡ከሚያውቁት ኢህአዴግ በማያውቁት ሻዕቢያ ወደምትመራው ኤርትራ ያመሩት እኛ እዚህ ቁጭ ብለን ስለሻዕቢያ ማሰብ የምንችለውን እነርሱ ማሰብ ባለመቻላቸው አይደለም፡፡ከሁለቱ መጥፎዎች አንዱን መጥፎ በመምረጣቸው እንጂ፡፡
ሌላው የተስፋሁን ፈላጊዎች አጥብቀው የፈለጉት ዜና ‹‹ሞቱን››ይዞላቸው ቢመጣ እንኳን ይህ የተስፋሁንን መንገድ ስህተተኝነት ሊያሳያቸው አይችልም፡፡ብዙ ተስፋሁኖች እኮ በረሃ ሳይወርዱ በስርዓቱ ተገድለዋል፡፡እናስ የእነርሱ መሞት ሰላማዊ ትግል እንደማይሰራ ማሳያ ሊሆን ነው?
በተረፈ ተስፋሁንን አሳዩን ያላችሁ ሰዎች ‹‹ለምን ተስፋሁንን ማየት እንደፈለጋችሁ›› ንገሩን እስኪ፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials