Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, March 25, 2016

ፓትርያርኩ፡- ለኢትዮጵያ የደኅንነት፣ ለምእመናን የድኅነት ሥጋት/ዲያቆን ዳንኤል

* ፓትርያርኩ፡- ለኢትዮጵያ የደኅንነት፣ ለምእመናን የድኅነት ሥጋት ****
‹የክርስቶስ አንዲት በግ መከራን ስትቀበል ከማይ እኔ የበጉ እረኛ መከራ መቀበልን እመርጣለሁ›
 
ይህንን የተናገረው ዮሐንስ አፈወርቅ ነበር፡፡ የቁስጥንጥንያዋ ንግሥት አውዶቅስያ የአንዲት ክርስቲያን ምእመንን መሬት ወስዳ ባሰቃየቻት ጊዜ ለተግሣጽ የተናገረው ነው፡፡ እንዳለው አልቀረም አውዶቅስያ ባደረሰችበት መከራ ተግዞ በዚያው ሞትን ተቀብሏል፡፡ እውነተኛ አባት ስለ በጎቹ ራሱን አሳልፎ ይሰጣል እንጂ በጎቹን ለራሱ ክብርና ጥቅም ሲል አሳልፎ አይሰጥም፡፡ ፓትርያርክ ማለት በግሪክ ‹ታላቅ አባት› ማለት ነው፡፡ የታላቅ አባት ተግባር የልጆቹን ሥራ ማፍረስ አይደለም፤ ለዚህማ አባት አያስፈልግም ሰይጣን እንጂ፤ የታላቅ አባት ሥራ ልጆቹን መክሰስ አይደለም፤ ለዚህማ ሰይጣን እንጂ አባት አያስፈልግም፡፤ የታላቅ አባት ሥራ ልጆቹን ጠርቶ መውቀስ እንጂ በር መዝጋት አይደለም፤ ለዚህማ አባት አያስፈልግም ሰይጣን እንጂ፡፡ የታላቅ አባት ሥራ ልጆቹን ማቀፍ እንጂ ማባረር አይደለም፤ ለዚህማ ሰይጣን አለ፡፡
ፓትርያርኩ እንጨት የሚሸጡ እናቶች ካወጡት የእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት ገንዘብ ግማሽ ሚሊዮን ብር እንደዋዛ በአንድ ሙሰኛ ሲነጠቅ ተኝተዋል፤ በመሐል ከተማ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የተሠሩ ሕንጻዎች በጎጆ ቤት ዋጋ በሙስና ለዐሠርት ዓመታት ሲከራዩ ተኝተዋል፤ ከመንበረ ፕትርክናቸው ሥር ባለች አጥቢያ የቤተ ክርስቲንን ገንዘብ አናስበላም ያሉ ካህናትና ምእመናን ሲባረሩ ተኝተዋል፡፡ በሕዝብ ጥያቄ ሽፋን ጽንፈኛ አቋምን በሚያራምዱ ሰዎች አብያተ ክርስቲያናት ሲቃጠሉ ይተኛሉ፤ የስልጤ ዞን ምእመናን በሃይማኖታችን ምክንያት መከራ እየተቀበልን ነው ሲሉ ይተኛሉ፤ ቤተ ክህነቱ የኑፋቄ ማኅደር ሲሆን ይተኛሉ፤ የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ሲዘጉ፣ ገዳማትና አድባራት ሲፈርሱ፣ የአብነት ትምህርት ቤቶች ሲበተኑ ይተኛሉ፤ በመሥዋዕትነት የተመሠረቱት የደቡብ አፍሪካ አብያት ክርስቲያናት በሙሰኛ አመራሮች አደጋ ላይ ሲወድቁ ይተኛሉ፣ ይሄ ሁሉ ዘለፋና ኑፋቄ በቤተ ክርስቲያን ላይ ሲዘንብ ይተኛሉ፡፡
መናፍቃንን የሚተች ጽሑፍ በኦርቶዶሳውያን ተጻፈ ሲሏቸው፤ ምእመናንን የሚያጸና ጉባኤ ሊዘጋጅ ነው ሲሏቸው፤ ሕዝቡ ወደ ቤተ ክርስቲያን እየመጣ ነው ሲሏቸው፤ ወጣቱ ትውልድ ቤተ ክርስቲያኑን ለማገልገል እየተጋ ነው ሲሏቸው፤ ዲያስጶራው ሕዝብ በእናት ቤተ ክርስቲያን ሥር ሆነ ሲሏቸው፤ ቤተ ክርስቲያንን የሚገልጥ ዐውደ ርእይ ሊዘጋጅ ነው ሲሏቸው፤ መንፈሳዊ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ሊቀርብ ነው ሲሏቸው ያን ጊዜ ብዕራቸውን ይዘው ለማገድና ለመክሰስ ይነቃሉ፡፡ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ‹ድንግል ሆይ የአንቺን ምስጋና ለመጻፍ ምንጊዜም ብእሬ ቀለም እንደያዘ ነው› ነበር ያለው፡፡ የፓትርያርኩ ብእር ግን ምእመናንን የሚያጽናና ጦማር ለመጻፍ ወይም ድንግልን የሚያመሰግን ድርሳን ለመድረስ የሚጨበጥ አይደለም፡፡ እንደ ጠንቋይ ብዕር ለማፍዘዝና ለማደንገዝ እንጂ፡፡
የፓትርያርክ ዋናው ሥራው የሀገር ደኅንነት እንዲጠበቅ ‹ዕቀብ ሕዝባ ወሠራዊታ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ› እያለ መጸለይ፤ የምእመናን ድኅነት እንዲረጋገጥም ሃይማኖት ማስተማር፣ በጎችን መሠማራትና ቀኖናን መጠበቅ ነበረ፡፡ ለቅዱስ ጴጥሮስ ‹በጎቼን ጠብቅ፣ አሠማራ› ነበር የተባለው፡፡ መጠበቅ- ከክህደት፣ ከኑፋቄ፣ ከኃጢአት ከበደል፤ ማሠማራት - በትምህርት፣ በምግባር፣ በትሩፋት፣ በአገልግሎት፣ በጽድቅ መስክ ላይ፡፡
‹ባለሞያ ሴት የሠፋችውን ወራንታ፣ ጅል ትተረትረዋለች› እንደተባለው በደኅና ጊዜ ትጉኃን አበው የሰበሰቧቸውን ወጣቶች ካልበተንኩ ብሎ እንዴት አንድ ፓትርያርክ ይነሣል፡፡ ወጣቶቹ ሊሳሳቱ፣ ሊያጠፉም ይችላሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ግን ለዚህም መንገድ ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የመንግሥት ባለ ሥልጣናት ሳይቀሩ የገዛ ልጆችዎን ያወያዩ ሲሏቸው በራቸውን ጠርቅመው የሚዘጉ ፓትርያርክ በታሪክ የሚጀመሪያው መሆን አለባቸው፡፡ በሱራፊ ነበልባል የተዘጋች ገነት ስትከፈት በፓትርያርክ የተዘጋች የቤተ ክህነት በር ልትከፈት አልቻለችም፡፡ ሰይጣንን ከእግዚአብሔር ጋር ለማነጋገር የደከሙ እነ ክርስቶስ ሠምራን የመሰሉ ቅዱሳን ባሉባት ቤተ ክርስቲያን እረኛው ከመንጋው ጋር መነጋገር አቃተው፡፡ ኢየሱሳውያንን በዐደባባይ ሳናነጋግራቸው መሄድ የለባቸውም ብለው የተሟገቱ እነ እጨጌ በትረ ጊዮርጊስ በነበሩባት ቤተ ክርስቲያን የገዛ ልጆቹን ለማነጋገር በር የሚዘጋ እጨጌ ተፈጠረ፡፡ የመካ ቁራይሾችን አሳልፈን ለጠላቶቻቸው አንሰጥም የሚሉ አበው በነበሩባት ቤተ ክርስቲያን የገዛ ልጆቹን አሳልፎ የሚሰጥ አባት መጣ፡፡
የኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት በ1972 እኤአ ካይሮ ላይ ባደረጉት ጉባኤ ከተስማሙባቸው ነገሮች አንዱ የኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳት ተልዕኮ ነበረ፡፡ እንዲህ ይላል ‹ኦርቶዶክሳውያን ጳጳሳት አምስት ተልዕኮ አላቸው፡፡ እነዚህም
1. ወንጌልን መስበክ(Preach the Gospel)
2. ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን መፈጸም(Administer the Sacraments of the Gospel.)
3. የቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ አንድነትና ቀኖና መጠበቅ(Guard the faith, unity, and discipline of the church.)
4. ለካህናትና ለምእመናን የቅድስና ምሳሌ መሆን(Be a moral example of holiness and wholesomeness.)
5. በእረኛውና በበጎች መካከል ያለውን ክፍተት ማጠበብ(Diminish the distance between bishops and their flock.)
ለመሆኑ የእኛ አባት የቱን ነው እየፈጸሙ ያሉት? ወይስ ከኦርየንታል አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር ውጭ ሆነናል?
ዐውደ ርእዩ የማይደረግበት በቂ ምክንያት ከነበረ ቢያንስ ከሳምንት በፊት መግለጥ ይቻል ነበር፡፡ ዓላማው ግን ማበሳጨት፣ ዐመጽ ማስነሣት፣ ተሥፋ ማስቆረጥና ምእመናንን ወደማይፈልጉት መሥመር መውሰድ ነው፡፡ ለዚህ ነው ፈያታዊ ዘየማን ገነት በገባባት ሰዓት ዐውደ ርእዩ እንዲዘጋ የተደረገው፡፡ የዚህች ሀገር ሰላም አይፈለገም? ምእመናን ሀገር እንደሌላቸውና መብት እንደሌላቸው ራሳቸውን እንዲቆጥሩ ይፈለጋል? ‹ለቀኑ ክፋቱ ይበቃዋል› እንዲል ሀገሪቱ ያለባት ችግር አይበቃትም? ተጨማሪ ችግር ማምረት ይፈለጋል?
ችግሩ ሁሉ እየተፈጠረ ያለው በመንግሥት ስም ነው፡፡ ‹መንግሥት አዞናል፤ እገሌ የተባለ ባለ ሥልጣን ብሎናል፤ ፖሊስ እንጠራለን፤ ደኅንነት እናዛለን› ነው በቤተ ክህነቱ ዘንድ የሚባለው፡፡ እውነት መንግሥት በስሙ የሚሠራውን ያውቀዋል፤ ካወቀውስ ዝም ይላል? ቤተ ክህነቱ በሚያመጣው ዳፋ መከራ ለመቀበልስ ዝግጁ ነው? ይህ አካሄድስ ለሀገሪቱ ደኅንነት የሚበጅ ነው? ዐውደ ርእዩ እንዲዘጋ ያዘዘውስ የትኛው መንግሥት ነው? አንዱ የሚፈቅድ ሌላው የሚዘጋ ስንት መንግሥት ነው ያለው? ወይስ ‹ደብዳቤ መጻፉ አላዋጣምና ዝጋልኝ› ተብሎ እጅ የተሰነዘረለት አካል ያደረገው ነው? መጽሐፉ እንደሚል ‹የማይገለጥ የተሠወረ› አይኖርምና ዐውቀነዋልም፣ እናውቀዋለንም፡፡
የገዛ ፓትርያርካችን ለእኛ ለምእመናን ድኅነትን እንዳናገኝ ሥጋት ሆነውብናል፡፡ የታገሡትን ሁሉ ለክፋት በማነሣሣት ደግሞ ለሀገሪቱ ደኅንነት ሥጋት እየሆኑ ነው፡፡ የምእመናኑን ሥጋት ሲኖዶሱ፤ የሀገሪቱንም ሥጋት መንግሥቱ ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ከቤተ መቅደስ የተነሣ ችግር መጀመሪያው እንጂ መጨረሻው አይታወቅምና፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮች የምእመኑን የአስተሳሰብ ቅርጽ ይቀይራሉ፡፡ የሐበሻን ሥነ ልቡና ለሚረዳ ደግሞ ሲረገጥ እንደሚጠክር ጭቃ ያጠነክራሉ፡፡ ሲሞረድ እንደሚሳል ቢላዋ፣ ሲቀረጽ እንደሚሾል እርሳስ ያደርጋሉ፡፡
በዐውደ ርእዩ የሚማሩት የሚያዩት ብቻ ነበሩ፡፡ አሁን ግን ያላዩትም እንዲማሩ አድርገዋል፡፡ ሐሳብና ርእዮት ሊያስተባብረው የማይችለውን ተጠቂነት ያስተባብረዋል፡፡ ተጠቂነት ክርክርና ውይይት፣ ማስረጃና መረጃ አይጠይቅም፡፡ መጠቃቱን ያወቀ ሁሉ ራሱ ገብቶት ይተባበራልና፡፡ ምናልባትም ምእመናንን ከገድል ተራኪነት ወደ ገድል ሠሪነት ያሻግራቸው ይሆናል፡፡ ‹እዚያም ቤት እሳት አለ› አሉ አለቃ፡፡
እንደ ሶምሶን ከአንበሳ ሬሳ ማር ለማውጣት ግን በሳል አመራር ይጠይቃል፡፡ የማኅበሩ አመራርም ቢሆን ጊዜውን አይቶ የሚሣለጥ አመራር እንጂ የተቸከለ አመራር መሆን የለበትም፡፡ የፓትርያርክ ማትያስ ዘመን እንደ ፓትርያርክ ጳውሎስ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምም ዘመን እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አይደለም፡፡ አሁን የሆነው ነገር ሊሆን እንደሚችል ቀድሞ እየታወቀ ከግንቡ ጋር እስኪጋጩ ድረስ ቆሞ መጠበቅ ብልህነት አይደለም፡፡ አሁንም ‹እገሌ የተባለ ባለሥልጣንን አናግረናል፤ እገሌ የተባሉ አባት አይዟችሁ ብለውናል› እያሉ መጓዝ የሚያዋጣ አይደለም፡፡ ለጉባኤ ተሰብስቦ ‹ ለፓትርያርኩ የተጻፈው ደብዳቤ አንጀት አርስ ነው› ብሎ አጨብጭቦ የሚበተን አመራር ጊዜው ሊያልፍበት ይገባል፡፡ ከዲሚትሪ ሆቴል እስከ ፌዴራል ጉዳዮች የተደረጉትን ውይይቶች ገምግሞ አዲስ አቅጣጫ መያዝ ይገባ ነበር፡፡ የሚሰበሰብ ብቻ ሳይሆን የሚተነብይ አመራርም ያስፈልጋል፤ ካልሆነ ግን
‹ከክምር ድንጋይ ላይ ይበቅላል ደደኾ
የፈራሁት ነገር መጣ ድኾ ድኾ› የተባለው ይደርሳል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials