የሐራ ተዋሕዶ ዘገባ እንደወረደ
- ድንገተኛ ልዩ ስብሰባው የተጠራው በቋሚ ሲኖዶሱ ነው
- በፓትርያርኩና በማኅበረ ቅዱሳን ውዝግብ ላይ ይወያያል
- በዐቢይ ጾም የጸሎተ ምሕላ ጉዳይም ውሳኔ ያሳልፋል
ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ዛሬ የካቲት ፳፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ጀምሮ ድንገተኛ ልዩ ስብሰባ መቀመጡ ተገለጸ፡፡
ድንገተኛ ልዩ ስብሰባውን የሚያካሒዱት፣ በብፁዕ አቡነ ናትናኤል ሞተ ዕረፍትና ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ በዓለ ሢመት በመዲናይቱ አዲስ አበባ የተሰበሰቡ ከ25 ያላነሱ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ናቸው፡፡
ስብሰባው እንደሚካሔድ የታወቀው፣ ፓትርያርኩ በመጪው ሰኞ የሚጀመረውን ዐቢይ ጾም በማስመልከት ዛሬ ረፋድ ላይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ በተገኙበት በቅዱስ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው እንዳበቁ ሲኾን አስቀድሞ መረጃው እንዳልነበራቸው ተገልጧል፡፡
ፓትርያርኩ መግለጫውን በንባብ ካሰሙ በኋላ ከአዳራሹ ለመውጣት ተነሥተው እንደቆሙ፤ በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና በብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ ጥያቄ ተመልሰው እንዲመቀጡ መደረጉን የመንበረ ፓትርያርኩ ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ፓትርያርኩ ተመልሰው እንደተቀመጡ፣ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቡነ ማቴዎስ፣ ማእከላዊ አሠራርን ባለመጠበቅ እየተከሠቱ ስለሚገኙና እልባት ለመስጠት ስላዳገቱ ችግሮች በስፋት አስረድተዋል፡፡ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በበላይነት የሚመራው ጠቅላይ ጽ/ቤታቸው ሳያውቀው ከቅዱስነታቸው ልዩ ጽ/ቤት ለአስፈጻሚ አካላትና ተቋማት የሚወጡ ደብዳቤዎችን ብፁዕነታቸው በማሳያነት አቅርበዋል፡፡ ይህም በሥራ ግንኙነቶች ላይ ቀውስ እንደፈጠረና አለመግባባቱ በውጭ አካላት ዘንድ ሳይቀር ትዝብት ላይ እየጣለን በመኾኑ ቅዱስ ሲኖዶሱ አንድ መፍትሔ እንዲሰጠው ብፁዕነታቸው ጠይቀዋል፡፡
ማዕከላዊነቱን ስላልጠበቀ የአሠራር ችግር በማብራራት ተጨማሪ አጽንዖት የሰጡት የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ በኦሮሚያ ክልልና በአንዳንድ የአገራችን ክፍሎች ስላጋጠመው የሰላም ቀውስና ስለ ተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ሲጠይቁ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ በዚኹ መልካም አጋጣሚ በእነዚኽና ሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ተወያይቶ ውሳኔ እንዲያሳልፍ ጠይቀዋል፡፡
የብፁዕ ዋና ጸሐፊውንና የብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁን መግለጫ ያዳመጠው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ጉዳዩ በአጀንዳ ተቀርጾ እንዲቀርብለት፤ ከኹለቱ ብፁዓን አባቶች ጋር ብፁዕ አቡነ ሕዝኤልን፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስንና ብፁዕ አቡነ ያሬድን በመጨመር በአርቃቂነት ከሠየመ በኋላ ተዘጋጅቶ በቀረበለት መሠረት ከቀትር በኋላ ስብሰባውን መጀመሩ ታውቋል፡፡
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ድንገተኛ ልዩ ስብሰባው እንደቀጠለ ሲኾን በአርእስተ ጉዳይ ደረጃም፡-
- ስለ ሰላም እና ስለ ተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት፤
- በድርቁ ምክንያት ለተጎዱት ወገኖች እየተደረገ ስላለው ርዳታና ጸሎተ ምሕላ፤
- ማዕከላዊነትን ስላልጠበቁ አሠራሮችና ስላስከተሏቸው ችግሮች፤
- ከልዩ ጽ/ቤት ስለሚወጡ ደብዳቤዎችና መጻጻፎች በተመለከተ፤
- ሐዋርያዊ ጉዞን(የፓትርያርኩን የውጭ ጉዞዎች) በተመለከተ፤
የሚሉ መነጋገርያዎች እንደሚገኙበት ተመልክቷል፡፡
በሕገ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ሥነ ሥርዓት፣ በዓመት ኹለት ጊዜ ከሚደረገው የምልዓተ ጉባኤው መደበኛ ስብሰባዎች በተለየ፣ አስቸኳይና ድንገተኛ ጉዳይ ሲያጋጥም ቋሚ ሲኖዶሱ በብፁዕ ዋና ጸሐፊው አማካይነት ልዩ ስብሰባ ሊጠራ ይችላል፡፡ በሌላ በኩል ከጠቅላላ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ከግማሽ በላይ ጉባኤ እንዲደረግ በጠየቁ ጊዜ ጥሪ ሊደረግና ስብሰባው ሊካሔድ ይችላል፡፡
በስብሰባው፣ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ለሚመለከቱ አጀንዳዎች ከአባላት ከሦስቱ እጅ ኹለቱ እጅ ከተገኙ ምልዓተ ጉባኤ ይኾናል፤ በአስተዳደር ጉዳዮች ውሳኔዎች ሲተላለፉም ከግማሽ በላይ በኾነ ድምፅ የተደገፈው ሐሳብ ያልፋል፡፡
No comments:
Post a Comment