Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, March 17, 2016

ድርቅ በተከሰተባቸው የተወሰኑ ክልሎች የኩፍኝ በሽታ በመዛመት ላይ መሆኑ ተነገረ


ኢሳት (መጋቢት 2 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን የድርቅ አደጋ ተከትሎ ድርቁ በተከሰተባቸው ስድስት ክልሎች መካከል በሶስቱ በምግብ እጥረት በተጎዱ ህጻናት መካከል የኩፍኝ በሽታ በመዛመት ላይ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጠ።
በምግብ እጥረት በተጎዱ ህጻናት መካከል ተከስቶ ያለው ይኸው የኩፍኝ በሽታ ለበርካታ ህጻናት ሞትን ምክንያትን ሊሆን እንደሚችል ድርጅቱ በጉዳዩ ዙሪያ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።
ባለፈው ወር በኦሮሚያ፣ ደቡብ እና ሶማሊያ ክልል መከሰት የጀመረው ይኸው የኩፍኝ በሽታ በተያዘው ወር ጨምሮ መገኘቱንና ስምንት የበሽታው ተዛማች ሪፖርቶች መገኘታቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አክሎ ገልጿል።
ከ10 ሚሊዮን ለሚበልጡና ለአስቸኳይ የምግብ እጥረት ለተጋለጡ ሰዎች መቅረብ ያለበትን የእርዳታ አቅርቦት ከተጠበቀው በላይ በመዘግየቱ ምክንያት ኩፍኝን ጨምሮ የሌሎች ተላላፊ በሽታዎች ስጋት እየሆኑ መምጣታቸውም ታውቋል።
በተለይ ባለፈው ወር የእነዚሁ ተላላፊ በሽታዎች ስርጭት ከመቼውም ጊዜ በላይ ጨምሮ የተመዘገበ ሲሆን፣ ለድርቅ አደጋ ለተጋለጡ ሰዎች የሚቀርበው እርዳታ ጎን ለጎን በሽታዎቹን የመቆጣጠር ስራ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ድርጅቱ አሳስቧል።
አለም አቀፍ የኣርዳታ ተቋማት በበኩላቸው በሃገሪቱ ያለው የእርዳታ አቅርቦት በቀጣዩ ወር የሚያልቅ በመሆኑ ተረጂዎች ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ ገልጸዋል።
አለም አቀፍ እርዳታን ከውጭ ሃገር ለማስገባት በትንሹ 120 ቀናቶች የሚፈጁ በመሆኑ ድርቁን የመከላከሉ አደጋ ከፍተኛ ችግርም አጋጥሞት እንደሚገኝ ኦክስፋም ብሪታኒያ የተሰኘው ግብረ-ሰናይ ድርጅት አመልክቷል።
ይሁንና የመንግስት ባለስልጣናት ድርቁ የከፋ ጉዳትን አያስከትልም በማለት እየተሰጡ ያሉ ማሳሰቢያዎችን አስተባብለዋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials