Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, March 9, 2016

ቻይናዊያን በሕገወጥ የችርቻሮ ንግድ ላይ በመሰማራታቸው ኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎች መስራት አልቻልንም አሉ

ቻይናዊያን በሕገወጥ የችርቻሮ ንግድ ላይ በመሰማራታቸው ኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎች መስራት አልቻልንም አሉ

Image result for ethiopia china trade relations
የካቲት ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመዲናችን አዲስ አበባ በቦሌ ሩዋንዳ አካባቢ የሚገኙ ነጋዴዎች በቻይናዊያን የሕገወጥ ንግድ ምክንያት ስራቸውን በአግባቡ ማከናወን እንዳልቻሉ ተናገሩ። ባለፉት ሶስት ዓመታት የውጭ ዜጎች በሚበዙበት በቦሌ ሩዋንዳ ለምግብ ፍጆታዎች የሚውሉ ምርቶች በማቅረብ ስራ ላይ ተሰማርተው ይሰሩ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ነጋዴዎች በሕገወጥ የቻይኖች ዜጎች አካባቢያችን ተወሮ ሱቃቸውን ለመዝጋት እየተገደዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በቦሌ ሩዋንዳ በሚኒ ማርኬት ተሰማርተው የሚገኙት ወ/ሮ ትክክል ተበጀ ሁኔታውን ሲያስረዱ ” በሰው ሀገር መንደር ውስጥ ገብቶ ጎመን፣ አሳ፣ አሳማ እና ዶሮ ዘርግቶ ይቸረቸራል እንዴ? መንደራችን ዘልቀው የሚቸረችሩ ከሆነ እኛ ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች የት ሄደን እንሰራ? አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ ከ2 መቶ ሽህ የአሜሪካ ዶላር በላይ ኢንቨስትመንት ውስጥ እንጂ ችርቻሮ ውስጥ መግባት አይችልም። ጎመን ቸርቻሪ ቻይና አጠገባችን ሱቅ ከፍቶ የገበያ ስርዓቱን ሲያፋልሰው መመልከት በእውነት አስተዳደር አለ ወይ ብለን ለመጠየቅ ተገደናል። ያላንኳኳነው የመንግስት አካል የለም ወዴት ሄደን አቤት እንደምንል ግራ ገባን?” ሲሉ በምሬት ተናግረዋል።
ወ/ሮ ትክክል አክለውም ”ቻይኖቹ እንዴት እንደሚሰሩ እያወቅን ለመንግስት ኃላፊዎች ስንናገር በከፍተኛ ምርመራ እንጂ በቀላሉ አሰራራቸውን ማረጋገጥ አንችልም ይሉናል። የንግድ ፈቃድ ተከራይተው እንደሚሰሩ በተደጋጋሚ አሳይተናል። አምስት ሱቆች በተጨባጭ ማስረጃ ተረጋግጦባቸው እንዲዘጉ ውሳኔ ተላልፎ ነበር። በሳምንቱ ግን የተዘጉት ሱቆች ተከፍተው ወደተለመደ ሕገወጥ ስራቸው ገብተዋል። ሱቆቹ እንዲከፈቱ መመሪያ የሰጠውን አካል እንኳን ማን እንደሆነ ለማረጋገጥ አልቻልንም። መንግስት ማረጋገጫ በእጁ ይዞ የዘጋቸውን ሱቆች ከወዴት የመጣ ሌላ አካል ሊከፍታቸው ይችላል? ፍትህ እስከምናገኝ ድረስ የመንግስት ያለህ እያልን እየጮህን አለን” ሲሉ አክለዋል።
“በአካባቢው ሁለት ኮንቴነር ሩዝ ሊራገፍ መጣ። ጉዳዩን ለፖሊሶች በስልክ አሳወቅን። ፖሊሶቹም በቦታው ተገኙ። ጉዳዩም ለወረዳ 2 ቀበሌ ሪፖርት ተደረገ። ቀበሌውም ሩዙን ለማራገፍ የመጡትን ሰዎች ሩዙ ወደ ሀገር ውስጥ የገባበትን ዶሴ አሳዩን ሲል ቢጠይቅም በወቅቱ ምንም አይነት መረጃ ማቅረብ አልቻሉም። የሩዙ ባለቤቱ ይጠራ ሲባል አቶ ፍትህ የተባለ ግለሰብ ቀረበ። ያለውን መረጃ እንዲያሳይም ቢጠየቅም ውክልና የለኝም የሚል ምላሽ አቀረበ። ውክልና ያላት ሊንዳ የምትባል ቻይናዊ መሆኗን ተናገረ። ሊንዳም ተጠርታ ቀርባ ውክልናዋን ለፖሊሶቹ አቀረበች። ውክልና ሰጪው አቶ ማሕመድ የተባለ ሰው ነው። አቶ ፍትህ ግን በማጭበርበሩ እስር ቤት እንዲቆይ ተደረገ። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ግን አቶ ፍትህ ከማረፊያ ቤት እንዲወጠ ተደረገ ግራ ተጋባን” ሲሉ ወ/ሮ ትክክል ያስረዳሉ።
“በማግስቱ በሁለት ኮንቴነር ውስጥ የነበረው ሩዝ ተራግፎ የተወሰነውን ከመኪናው ላይ ቻይናዋ አከፋፈለችው። ጥቆማችንም አፈር በላው። እኛ ቤት ተከራይተን እየሸጥን እነ ሊንዳ በመኪና እየዞሩ በሕገወጥ መንገድ ለቻይኖቹ ሩዝ ዘይት እና ሌሎች የስጋ ምርቶችን ያከፋፍላሉ። ይሄም አልበቃ ብሎ አጠገባችን በተከራየችው የንግድ ፈቃድ ትቸረችራለች። አንድ የቻይና ደንበኛችን ለምን ከአካባቢው ሱቆች ግዢ እንዳቆመ ስንጠይቀው በየቤታችን የምንፈልገው እቃዎችን ይመጡልናል ነበር ያለን። እኛ ግን ሱቅ ውስጥ ቆመን ቀርተናል መንግስት ባለበት ሀገር ይህ ይፈጸማል ብሎ ማን ይገምታል? ከዚህ በላይ ሕገወጥ በደል ከየት ይመጣል?” በማለት ምሬታቸውን ገልጸዋል።
አቶ ንጉሴ አበራ በበኩላቸው “ቻይናዎቹ ባልተፈቀደላቸው የችርቻሮ ንግድ ላይ በመሰማራት የንግድ ስርዓቱ በማፋለስ ላይ ናቸው። ሥራችን ሰርተን ለመንግስት የሚገባውን መክፈል እስኪያቅተን ድረስ ጉዳት አድርሰውብናል።አቅማቸው ደከም ያሉ ኢትዮጵያዊያን በማግባባት እና በስማቸው ንግድ ፍቃድ በማውጣት በሕገወጥ መንገድ ከገበያ ውጪ ሊያደርጉን ከጫፍ ደርሰዋል። አነስተኛ ጉርሻ እየሰጡ እኛንም መንግስታችንንም ለከፋ ችግር እያጋለጡ ነው የሚገኙት። ወደ ኢትዮጵያ መንግስት ካዝና የማይገባ የንግድ አሰራር ነው የሚከተሉት። ግብይት የሚፈጽሙት እርስ በእርሳቸው ነው።በስማቸው ንግድ ፍቃድ የወጣባቸው ኢትዮጵያዊያን ከግብይቱ የሚገኘውን ገንዘብ አያውቁትም።
ወደ ስራቦታውም አያደርሷቸውም። በፈለጉ ሰዓት ቻይናዎቹ ሀገር ጥለው ይወጣሉ። ዓመታዊ ሒሳባቸውን ሳያሳውቁ በገቢዎች ምርመራ ሳይደረግባቸው ሀገር ጥለው ይወጣሉ። ወይም በሌላ ኢትዮጵያዊ ስም አዲስ ፈቃድ ያወጣሉ። ገቢዎች ንግድ ፈቃዱን ተከትሎ ምርመራ ሲያደርግ ግን እዳው ለእኛው ልጆች ይሆናል። ለእኛ እንቆቅልሽ ነው የሆነብን በተጨባጭ ማስረጃ የተዘጉ ሱቆች እንዲከፈቱ ተደርጓል። ስራችን መቀጠል በማንችልበት ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው። የመንግስት ያለህ እያለን ፍትህ እስከምናገኝ ድረስ መጮሃችን እንቀጥላለን” ብለዋል።
አቶ ታጠቅ ወርቁ በበኩላቸው ”ቻይናዎቹ ንግድ ፈቃድ ሳያወጡ አየር በአየር የስጋ ምርቶች ላይ ተሰማርተዋል። እኛ ከቄራ ሥጋ ማረጃዎች እያመጣን ነው የምናከፋፍለው። ቻይኖቹ በተለይ አሳማ ከየት እያመጡ እንደሚያከፋፉሉ እንኳን አናውቅም። በትንንሽ ሚኒባሶች ስጋ ጭነው ይመጣሉ። በአካባቢያችን ለሚገኙ ለቻይና ሕገወጥ ሱቆች በፍጥነት አከፋፍለው አራግፈው ይሰወራሉ። በተደጋጋሚ ለሚመለከተው የመንግስት አካል አቤት ብለናል የተሰጠን አጥጋቢ ምላሽ ግን የለም። የሚገርመው በራሳችን ተነሳሽነት ለጤና ቢሮ ለገቢዎች ጥቆማ ስናቀርብ ቻይናዎቹ ከመቼው የእኛን መጠቆም ሰምተው እንደሚሰወሩ ሁሌም ይገርመናል። እኛ ሕግ እያከበርን እነሱ ሕግ የሚጥሱ ከሆነ እንዴት ነው ወደፊት ሰርተን ራሳችን መቀየር ምንችለው?” ሲሉ ጠይቀዋል።
በኢትዮጵያ ሕግ ንግድ ፈቃድን ለውጭ ሀገር ሰውም ሆነ ለዜጋው ማከራየትና ውክልና መስጠት አይቻልም። እንዴት በኢትዮጵያዊያን ስም የንግድ ፈቃድ የወጣባቸው የቻይና ሱቆች እንዲሰሩ ይፈቀዳል ሲሉ የህግ ባለሙያዎች ይጠይቃሉ። ቻይናዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበት ቪዛ አይነት ምን ይመስላል? የስራ ፈቃድስ እንዴት ነው የሚያገኙት? የተፈቀደላቸው የቆይታ ጊዜ ማለቅ አለማለቁን የሚከታተለው አካል ስራውን በተገቢ ሁኔታ እየተወጣ ነው? ቻይናዎቹ በምን አይነት ስራዎች ላይ መሰማራት አይችሉም? ተሰማርተው ሲገኙስ እርምጃ የሚወስደው አካልስ ማነው? ሲል ሰንደቅ ጋዜጣ ዘገባውን በጥያቄ ደምድሟል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials