Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, March 12, 2016

አርቲስት ኤፍሬም ታምሩ ተከሰሰ !


Efrem Tamiru

አርቲስት ኤፍሬም ታምሩ “ለቀይ ዳማ ” ሙዚቃ የዜማ ደራሲ ክፍያ ሳይከፍል ሙዚቃውን ለህዝብ አቅርቦታል በሚል ክስ ተመሰረተበት።
ከሳሽ ወይዘሮ ቤተልሄም ማስረሻ የሙዚቃው ዜማ ደራሲ ልጅ ሲሆኑ፥ አርቲስት ኤፍሬም ታምሩ ለፈጠራው ስራ እና ህግ በመጣሱ 170 ሺህ ብር እንዲከፍል ክስ አቅርበውበታል።
የከሳሽ ወላጅ አባት አርቲስት ማስረሻ ሽፈራው፥ በ1977 ዓ.ም ታትሞ በወጣው የሙዚቃ አልበም ”ቀይ ዳማ” ወይም “የድንገት እንግዳ” ለተባለው ሙዚቃ ደራሲ መሆናቸውን የክስ መዝገቡ ያስረዳል።
ከሳሽ አባቴ በህይወት ባይኖርም ይህ መብቱ ግን በውርስ ለእኔ ተላልፎ እያለ ተከሳሽ የቅጅ እና ተዛማች መብቶችን ሳያከብር ከፈቃዴ እና ከእውቅናዬ ውጭ የህግ ጥበቃ የተደረገለትን የሙዚቃ ስራ እንደገና በመዝፈን በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን እንዲለቀቅ አድርጓል በማለት ነው ክሳቸውን ያቀረቡት።
ከዚህ ባለፈም አስቀድሞ የሰራቸውን ስራዎች በድጋሚ እንደሚሰራ በማስታወቅ እና ዘፈኑን ለማስታወቂያ ስራነት በማዋል ከፍተኛ ጥቅም አግኝቶበታል በማለት ከሳሽ፥ ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 6ኛ ፍትሃ ብሄር ችሎት ክሳቸውን አቅርበዋል።
በመሆኑም ተከሳሽ ለዜማ ደራሲው ፍቃዱን አግኝቶ ቢሆን ኖሮ ሊከፍለው የሚገባውን 30 ሺህ ብር እንዲሁም የከሳሽን ፈቃድ ሳያገኝ በህግ ጥበቃ የተደረገለትን መብት በመጣስ ለደረሰብኝ የሞራል ጉዳት አርቲስቱ 140 ሺህ ብር ይክፈለኝ ሲሉም ለፍርድ ቤቱ የዳኝነት ጥያቄ አቅርበዋል።
በወይዘሮ ቤተልሄም ማስረሻ በኩል ክስ የተመሰረተበት አርቲስት ኤፍሬም ታምሩ፥ ከሳሽ ከሟች አባታቸው አዕምሯዊ ንብረቱ በውርስ የተላለፈ መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ የላቸውም በማለት የመጀመሪያ መቃወሚያውን አቅርቧል።
አርቲስቱ ከሳሽ መብታቸውን መጠየቅ የነበረባቸው ወላጅ አባታቸው ካለፉ እስከ ሶስት አመት ባለው ጊዜ ቢሆንም፥ ክሱን ያቀረቡት ከ13 አመት ከ6 ወር በኋላ መሆኑ ግን ክስ የማቅረብ መብታቸው በይርጋ የታገደ ነው በማለት መቃወሚያውን ለችሎቱ አቅርቧል።
በተጨማሪም ከሳሽ ክስ ለማቅረብ የተረጋገጠ መብትና ጥቅም (vested interest) የላቸውም በማለትም ነው አርቲስቱ መቃወሚያውን ያቀረበው።
ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው ፍርድ ቤቱ፥ መዝገቡን መርምሮ በመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ለመጋቢት 27 ቀን 2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል።
ምንጭ፣ ኤፍ ቢ ሲ
የካቲት 29 /2008ዓ.ም
አዲስአበባ

No comments:

Post a Comment

wanted officials