(ሳተናው) የጀርመን ፓስፖርት የያዙ ሰዎች አለምን የጓዳቸው ያህል ሊመለከቷት ይችላሉ፡፡እጁ ላይ ያለው የኢትዮጵያ ፓስፖርት ከሆነ ግን እንደጀርመኖቹ ነገ ስፔን ሄጄ የባርሴሎናን ኳስ ወይም ደቡብ አፍሪካ ወረድ ብዬ የጥቁሮቹን ቀዬ ፕሪቶሪያን ጎብኝቼ ልመለስ አይሉም፡፡የብዙ ኢትዮጵያዊያንም የተለያዩ አገራትን የማየት ህልምም እጃቸው ላይ የሚገኘው ፓስፖርት እርባና ቢስ በመሆኑ ተኮላሽቶ ቀርቷል፡፡
ዛሬ ረቡዕ አመታዊው የአገራት የፓስፖርቶች ደረጃ ይፋ ሲደረግም የእኛው ፓስፖርት ከአለማችን አስር እርባና ቢስ ፓስፖርቶች ተርታ ተሰልፏል፡፡ፓስፖርቶቹ እርባና ቢስ የሚሰኙት በነጻ ያለ ቪዛ ጣጣ ወደተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የመውሰድ አቅማቸው እየተመዘነ ነው፡፡የቪዛ ሪስትሪክሽን ኢንዴክስ ባወጣው ሪፖርትም ኢትዮጵያዊያን ከእርባና ቢሱ ፓስፖርታቸው የተነሳ የሚያቀርቧቸው የቪዛ ጥያቄዎች በአብዛኛው ተቀባይነት አያገኙም በማለት ወርፉብናል፡፡
እንደ ኢንዴክሱ ከሆነም በአለማችን ያለቪዛ በዛ ወዳሉ አገራት ይገቡና ይወጡ ዘንድ ፓስፖርታቸውን ባሳዩ ቁጥር አረንጓዴ የሚበራላቸው አውሮፓውያን ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በምትገኝበት ምርጥ አስር እረባና ቢስ ፓስፖርት ያላቸው አገራት አፍጋኒስታን፣ኢራቅ፣ሶሪያ፣ኤርትራ፣የመንና ሶማሊያን የመሳሰሉ አገራት ናቸው፡፡
ሄንሌይ እና ፓርትነርስ የተባሉ በህግ ባለሞያዎች የተቋቋሙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ካለፉት 11 ዓመታት ጀምሮ የአለማችንን አገራት የፓስፖርት ደረጃዎች ሲያወጡ ቆይተዋል፡፡በዘንድሮው ዓመት የ104 አገራትን የፓስፖርት ደረጃ ሲያወጡም ኢትዮጵያን በ97 ደረጃ ላይ ከኤርትራ ጋር ዕኩል ነጥብ ሰጥተው አስቀምጠዋታል፡፡
የቪዛ ጉዳይ አገራት በሚኖራቸው ግኑኝነት ፣የጸጥታ ጉዳይ፣መሟላት ከሚገባቸው የቪዛ ፎርማሊቲዎች አንጻር ሊቀሉ ወይም ሊከብዱ እንደሚችሉ የሚናገሩት ድርጅቶቹ ከ218 አገራት የጀርመንን ፓስፖርት የያዙ ሰዎች በ177ቱ ያለምንም የቪዛ ጣጣ ጉዟቸውን ማድረግ እንደሚችሉ በማተት ኢትዮጵያዊያን ግን ወደ 37 አገራት ብቻ መሄድ ይችላሉ ብሏል፡፡
Useless-passports_01
http://www.middleeasteye.net/news/arab-countries-visa-passport-restrictions