bishop-abraham-desta-main_article_image
‹‹በአእምሯችንና በልባችን ጥያቄ አለ፣ለምን ጌታ ሆይ?ለምን እንዲህ ሆነ?››
(ሳተናው) ባለፈው ወር በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን መቂ ከተማ የአካባቢው ነዋሪዎች መንግስትን ለመቃወም ወደ አደባባይ በወጡበት ወቅት የሰው ህይወት መጥፋቱ፣የሰዎች መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንና የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ ክሊኒክ መዘረፋቸውንና መቃጠላቸውን መነገሩ አይዘነጋም፡፡የተዘረፈችው ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ቄስ አብርሃም ደስታ ድርጊቱ መፈጸሙን በማረጋገጥ ስለጉዳዩ ተናግረዋል፡፡
ቄስ አብርሃም ደስታ ለአለም አቀፉ የካቶሊክ የእርዳታ ድርጅት በጻፉት ደብዳቤና ለሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ ‹‹በመቂ የሚገኘው የጥንቱና ትልቁ ቤተክርስቲያን ጥቃት ደርሶበታል፣ ጥቃቱ የደረሰበትም በምናገለግላቸው፣አብረውን በሚሰሩና ለስራችን በጣም ቅርብ በሆኑ ሰዎች ነው››ብለዋል፡፡
የመቂው ቤተክርስቲያን አገልጋይ የሆኑት ቄሱ የጥቃት አድራሾቹን ሁኔታ ሲያብራሩም ‹‹ልጆች፣ወጣቶች፣ሽማግሌዎችና ሴቶች ድንጋዩችን በመወርወር በመጀመሪያ የቤተክርስቲያኑን ንብረት አጠፉ፣ የዲያቆናትና የመጋቢዎች ማዕከልን፣ለአካል ጉዳተኞች ህክምና ርዳታ የሚሰጥ ክሊኒክም ዝርፊያ ተፈጽሞባቸዋል››ይላሉ፡፡
በቤተክርስቲያኑ ላይ ጥቃቱ ሲሰነዘር 55 የሚደርሱ ከመላው ዓለም የተሰባሰቡ ካቶሊካዊያን በመጋቢዎች ማዕከል ይሰጥ የነበረውን የነርሶች ትምህርት በመከታተል ላይ ይገኙ እንደነበር ያስታወሱት ቄሱ እንግዶቹ አደጋ ሳይደርስባቸው ለመቂ ቅርብ ወደሆነችው ሻሸመኔ መወሰዳቸውን በማውሳት ‹‹በክሊኒኩ የሚሰሩ ነርሶች ግን ህመምተኞቻቸውን ለአደጋ በማጋለጥ ጥለዋቸው ሊሄዱ ባለመፍቀዳቸው አብረዋቸው ቆይተዋል፡፡የክሊኒኩን ንብረት በሙሉ ሌላው ቀርቶ በነርሶቹ ፊት ለፊት የግል ልብሳቸውን ሳይቀር ሰዎቹ ጠራርገው ከወሰዱ በኋላ ህንጻውን በእሳት አወደሙት››ብለዋል፡፡
ነርሶቹን አንድም ሰው ሊረዳቸው አለመፈለጉን በምሬት የሚገልጹት ቄስ አብርሃም ‹‹በእግዚአብሄር ርዳታ ህመምተኞቹን በመያዝ በቅርባቸው ወዳገኙት የሻሸመኔ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን በመግባት ምሽቱን በዚያ ማሳለፍ ችለዋል፡፡እነርሱ ሁሉን ነገር አጥተዋል፣ እጃቸው ላይ የቀረው ከእግዚአብሄር በነጻ ያገኙት የዘላለም ህይወት ብቻ ነው፣ ይህንን ሊወስዱባቸው አልቻሉም››፡፡
የተዘረፉ ንብረቶችን በዝርዝር ያስቀመጡት ቄሱ ‹‹250 አልጋዎች፣700 ብርድ ልብሶች፣የልብስ ማጠቢያ ማሽኖች፣ቴሌቭዥኖች፣ጀነሬተሮች፣የኮፒ ማሽኖች፣ኮምፒውተሮች፣በሮችና መስኮቶች ሳይቀሩ ተነቃቅለው ተወስደዋል››ይላሉ፡፡
ማዕከሉ ለአንድ ዓመት ያከማቸውን (በእርዳታ ያከፋፍለው የነበረ) 26.455 ፓውንድ ጥሬ እህል ሩዝ፣ስንዴ፣ ፓስታ፣ ላሞችና ዶሮዎች መወሰዳቸውን በመጥቀስ ዝርፊያ ያልተፈጸመው በትምህርት ቤቱ ላይ ብቻ ነበር ብለዋል፡፡
በቤተክርስቲያኒቱ ላይ ጥቃት ለመፈጸሙ ምክንያቱ ምን ነበር የተባሉት ቄሱ ምክንያቱን አሁን ለመናገር ባይፈቅዱም ‹‹በአእምሯችንና በልባችን ጥያቄ አለብን፣ጌታ ሆይ ለምን ?ግን ለምን እንዲህ ሆነ ?››በማለት ምላሽ ከአምላካቸው ለማግኘት ጥያቄያቸውን ሲያገለግሉት ለቆዩት ጌታ አቅርበዋል፡፡
Damage_done_to_Church_property_in_Vicariate_of_Meki__Eth
ምንጭ ካቶሊክ ወርልድ ኒውስና ክርስቲያን ራዲዮDamage_done_to_Church_property_in_Vicariate_of_Meki__Eth