Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, March 25, 2016

በማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ ታገደ

በማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ ታገደ

በማኅበረ ቅዱሳን የተዘጋጀው ዐውደ ርእይ ታገደ
ገና ከማለዳ እናት ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ለማገልገል ዓላማ ሰንቆ ወገቡን ታጥቆ የተቋቋመው ማኅበረ ቅዱሳን ከጥቂት ዓመታት ወዲህ የተቀናጀ በሚመስል ጥቃት እየተገፋ ይገኛል፡፡ ሰሞኑን እንደ ሽውታ ሰምተናት ግን አልፋ የሄደች የምትመስል ዜና ነበረች፡፡ የእርሷ ዜና አንዱ ግልባጭ ይኸው ዛሬ በድራማ መልክ ብቅ ብሎ ከዐውደ ርእዩ ይልቅ ገዝፎ ይታያል፡፡
ዛሬ በቁጥር ኤማ/1089-520-21/08 በቀን 14 መጋቢት 2008 ከኤግዚቢሽን ማዕከልና የገበያ ልማት ድርጅት የወጣው ደብዳቤ እንዲህ ይነበባል፡፡
በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ለማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት
ጉዳዩ፣ በነገው ዕለት የሚከፈተው ኤግዚቢሽን መሠረዙን ስለማሳወቅ
በኢግዚቢሽን ማዕከልና በማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት መካከል በተፈጸመው ውለታ መሠረት የጽ/ቤቱ ኤግዚቢሽን በነገው ዕለት እንደሚከፈት ይታወቅ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከፈቃድ ጋር በተያያዘ ያልተሟላ በመኾኑ በታሰበው መልኩ ዝግጅቱን ለማካሄድ አስቸጋሪ ኾኖ ተገኝቷል፡፡ ለተፈጠረው ክፍተትም ኤግዚቢሽን ማዕከሉ አዘጋጆቹንና ተሳታፊዎችን ከፍተኛ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡
በቀጣይ አስፈላጊ የኾኑ ፈቃዶች ሁሉ ሲሟሉ ተለዋጭ ፕሮግራም በማዘጋጀት አስፈላጊውን አገልግሎት ሁሉ እንደምንሰጥም በታላቅ አክብሮት እንገልጻለን፡፡
ከሰላምታ ጋር
(የማይነበብ ፊርማ)
ታምራት አድማስ
ዋና ሥራ አስኪያጅ
ማናኛውም አካል ውለታ ከመፈጸሙ አስቀድሞ የተዋዋዩን አካል ሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጥ ግዴታው ነው፡፡ በዚህ ደረጃ በርካታ ውለታ በመፈጸም የሚታወቀው የዐውደ ርእይ ማዕከል ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ውል ሲዋዋል ማረጋገጥ የሚገባውን ሁሉ ሳያረጋግጥ ነበረ ለማለት አይቻልም፡፡ አሁን ዛሬ በአሥራ አንደኛው ሰዓት በሕዝብ ላይ በደልና ግፍ የሚፈጽም ማስታወቂያ ማውጣት ምን ያኸል አሳዛኝ እንደኾነ መገመት አይከብድም፡፡
ከበርካታ አውራኅ ልፋት እና ድካም በኋላ፣ የስንት ወንድሞች እና እኅቶች እንቅልፍ ለምኔ ተጋድሎ በኋላ፣ ስንት እና ስንት ወጪ ከወጣ በኋላ፣ በርካታ የመግቢያ ትኬቶች ለተመልካቾች እንዲሠራጩ ከተደረገ በኋላ ሊከፈት ሰዓታት ብቻ የቀሩትን ዐውደ ርእይ በአስራ አንደኛው ሰዓት ሠርዣለሁ ማለት ከአጥንት ሥር ዘልቆ የሚሰማ ሕማም ነው፡፡ ይኽንን ታላቅ ዐውደ ርእይ ለማካሄድ ማኅበረ ቅዱሳንን እና የቤተ ክርስቲያን አለኝታ የኾኑ ምእመናን የከፈሉት መሥዋዕትነት እንዲህ በአንድ ብጣሽ ወረቀት ይቅርታ እንጠይቃለን በማለት ብቻ እንደዋዛ የሚሸኝ አይደለም፡፡
ከውሣኔው በስተጀርባ እነማን እንዳሉ እርግጠኛ ለመኾን ብዙ ልፋትን አይጠይቅ ይኾናል፡፡ የዚህ ውሣኔ መራራ ገጽታ ግን ከተባዳዮቹ ልቡና በምንም ላጲስ እንደማይጠፋ ሊታወቅ ይገባዋል፡፡ ብዙ የማባበያ ቃላት ሊሠነዘሩም ይችሉ ይኾናል፡፡ ዓላማን በማባበያ ማሰናከል ግን ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም፡፡ ትናንት በኢቤኤስ ይተላለፍ የነበረውን መንፈሳዊ መርሐግብር እንዲታገድ ተደረገ፡፡ ዛሬ ደግሞ አደባባይ ላይ የወጣው ዐውደ ርእይ ታገደ፡፡ ዝቅ ብሎ ከባት የተጀመረው ወደ አናት እያደገ መምጣቱ የመጨረሻ ግቡን ያመላክታል፡፡ እናስ መጨረሻው ወዴት ነው?
ዐውደ ርእዩ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ድርሻቸውን ዐውቀው በተሰጣቸው ጸጋ ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ የማነቃቃት ዓላማ ነበረው፡፡ ይኽም አንዱ የቤተ ክርስቲያንን ሥራ ለማገዝ እንጂ ሌላ ቅንጣት ታክል ጉዳይ የለበትም፡፡ የቴሌቪዥን መርሐ ግብሩም ቃለ ወንጌልን ለማሠራጨት እንጂ ሌላ አጀንዳ አልነበረውም፡፡
የማይታሠረውን ቃለ እግዚአብሔር ለማሠር መሞከር አዲስ ምንፍቅና ይኾናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደነገረን “የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሠርም” ፪ጢሞ ፪፥፱። ለዚህ ደግሞ ምንም ዓይነት ቦታ የለንም፡፡ በዚህ ቢታገድ እግዚአብሔር በወጀብ እና በዐውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው እና በሚከፍትበት ይከፍተዋል፡፡ ቅስማችንን ለመስበር ታስቦ ከኾነ ያበረታናል እንጂ አንገታችንን እንደማንደፋ እልፍ ጊዜ እልፍ ልንነግራችሁ እንወዳለን፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ስደክም ያን ጊዜ ኃይለኛ ነኝ” ያለውን እያሰብን ከድካም ወደብርታት ከምንሸጋገር በቀር ከዓላማችን ዝንፍ አንልም፡፡ ፪ቆሮ ፲፪፥፲።
የሚኾነውን ባናውቅም የታሰበውን እናውቃለንና አንደነግጥም፡፡ አሁንም ግን ሥራችንን በቅንነት እንቀጥላለን፡፡ በዚህ ጉዳይ ሀዘን የሚሰማችሁ ወንድሞች እና እኅቶች በማዘን ሰይጣንን እና ተልእኮ አስፈጻሚውን ከማስደሰት ይልቅ በተሻለ ሥራ እና መንፈሳዊ ቆራጥነት ወደፊት እንጋደል፡፡ ከዚህም የሚበልጥ መከራ ቢመጣ ወደ ኋላ አንመለስምና፡፡ እንባችንን የሚያብሰውን እግዚአብሔርን ተስፋ በማድረግ እንደበረታን እንቁም፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials