በታንዛኒያ ለእስር የተዳረጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር ከ500 በላይ መድረሱ ተገለጸ
ኢሳት (ጥቅምት 18 ፥ 2009)
በታንዛኒያ በህገ-ወጥ መንገድ ገብታችኋል ተብለው በተለያዩ ጊዜያት ለእስር የተዳረጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር ከ500 በላይ መድረሱን የሃገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።
የሃገሪቱ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ከአውሮፓ ህብረት የገንዘብ ድጋፍ ጠይቃ በመጠባበቅ ላይ መሆኗ ታውቋል።
ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት በሚያደርጉት ጉዞ ታንዛኒያን እና ሌሎች የአካባቢውን ሃገራት ለመሸጋገሪያነት እየተጠቀሙ መሆኑን ዘ ሲቲዝን የተሰኘ የታንዛኒያ ጋዜጣ ዘግቧል።
በተለያዩ እስር ቤቶች የሚገኙትን እነዚህኑ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የአለም አቀፍ ስደተኞች ድርጅት ጥረት ቢደረግም ድጋፍ ሊያገኝ አለመቻሉን በታንዛኒያ የድርጅቱ ተወካይ ቃሲም ሱፊ ለመገኛና ብዙሃን አስረድተዋል።
በታንዛኒያ በተለያዩ ጊዜያት በህገ-ወጥ መንገድ ገብቷችኋል ተብለው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተጨማሪ ተመሳሳይ ቁጥር ያላቸው በጎረቤት ማላዊ እና ሌሎች ሃገራት በእስር ላይ እንደሚገኙም ታውቋል።
በማላዊ ብቻ 120 ኢትዮጵያውያን በሶስት እስር ቤቶች የሚገኙ ሲሆን፣ የህገሪቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ኢትዮጵያውያኑ በአስከፊ የጤና ችግር ውስጥ የሚገኙ በመሆኑ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ ዘመቻን እያካሄዱ ይገኛል።
ባለፈው አመት በሃገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የተቀሰቀሰውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ተለያዩ ሃገራት በመሰደድ ላይ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል።
No comments:
Post a Comment