ያረፈው ኃይሉ ነው እንጂ ኃይሉስ አብሮን አለ።
ጌታቸው ኃይሌ
የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት መሪ አቶ ኃይሉ ሻውል አመራሩን ለመሰሉ መሪ አስረክቦ በአማካሪነት እስኪነጋ ይቆያል ብለን ስንጓጓ፥ የፖለቲካው ሌሊት ሊነጋ ጥቂት ሰዓቶች ሲቀሩት አረፈ። አንድ ትልቅ ዛፍ ወደቀ። ሆኖም፥ ምንም ዓይነት ሞገድ የማያነቃንቀው የራእዩ ኃይል አብሮን ስላለ እንጽናናለን። ብናዝን፥ ነግቶ በብርሃን ሳይመላለስ ስለቀረ ለሱ ነው እንጂ፥ መሰሉንም በመከራ የተፈተነውን አቶ ማሙሸት አማረን ኮትኩቶ ተክቶልናል።
ኃይሉ ተራ ሰው አልነበረም። ብዙዎች በወያኔ ፊት ከእምነታቸው ወጥተው ሲፍረከረኩና የተሰጣቸውን አሜን ብለው እጅ ነሥተው እግር ስመው ሲሄዱ፥ ኃይሉ ሻውል “የጥንቷ አንድ ኢትዮጵያ በጥንቱ አንድነቷ ትኖራለች ብሎ ተሟገተ፤ በሕዝብ ዳኝነት በምርጫ 97 ረታ። ባለ ጠመንጃው ረታሁ አለ።
ኃይሉ ሰው በሚያስፈልግበት ጊዜ አምላክ ለሕዝብ ለሀገር ከሚልካቸው ጀግኖች አንዱ ነበር። በዓሥራ አምስተኛው ምእት ዓመት የአፄ ዘርአ ያዕቆብን አገዛዝ የተጋፈጡት አባ እስጢፋኖስ፥ “ኃይለኛና ጨካኝ ገዢ ሲነሣ፥ ግትር ተቃዋሚ ይነሣበታል” ያሉት በኛ ዘመን በኃይሉ ሻውልና በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም፥ በኃይሉ ሻውልና በመለስ ዜናዊ ሲደርስ አየን። የደርግ መሪ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የሾማቸው ሁሉ ሲሰግዱለት፥ ኃይሉ “በተሰጠኝ ኃላፊነት አትግባ” ብሎ እንደገሠጸው አብረውት የነበሩ ይመሰክራሉ። መለስ ዜናዊ፥ ኢትዮጵያን በጎሳና በነገድ ከፋፍየና አጋጭቼ በዳኝነት እገዛታለሁ ብሎ ሲነሣ፥ ኃይሉ ሻውል፥ እኔ እያለሁ አታደርገውም ብሎ እስከ ዕለተ ሞቱ ተሟገተ። እነሆ ዛሬ የኃይሉ ኃይል ለሁለተኛ ጊዜ ሲረታ እናያለን። ሕዝቡ “አንድ ነን” ሲል በሀገሪቱ ዳር እስከ ዳር አስተጋባ።
መለስ ዜናዊና ደጋፊዎቹ በአማራው ላይ ሲዘምቱ፥ ዘመቻው በኢትዮጵያ አንድነት ላይ መሆኑ ለፕሮፌሰር ዓሥራት ወልደየስ ወዲያው ታየውና የመላው አማራ አንድነት ድርጅትን አቋቋመ። መለስም ዓሥራትም “አማራ” ይበሉ እንጂ በሁለቱም አእምሮ ውስጥ ያለው የኢትዮጵያ አንድነት ነበር። ወምበዴው አንድነትን ለመግደል፥ ሐኪሙ አንድነትን ለማዳን። ሁለቱም ደጋፊ አገኙ፤ መለስ ጥቅም ፈላጊዎችን እነ እንትናን ሲያገኝ፥ ዓሥራት የግል ጥቅሙን የሚሠዋ ኃይሉ ሻውልን አገኘ። የኢትዮጵያ አንድነት አሸነፈ።
የመላው አማራ አንድነት ድርጅት መሠረቱ የኢትዮጵያን አንድነት ለመጠበቅና የዜጎቿን ሁሉ እኩልነትና መብት በሕግ ፊት ለማስከበር መሆኑ በሕገ ድርጅቱ ውስጥ ግልጽ ቢሆንም፥ በስምና በመልክ ብቻ ለመፍረድ የሚቸኩሉ ድርጅቱን እውነትም አማርኛ ተናጋሪውን በሥልጣን ላይ ለማስቀመጥ የተቋቋመ ድርጅት አደረጉት። አቶ ኃይሉ ሻውል የአመራሩ ጥሪ ሲደርሰው የድርጅቱን እውነተኛ ገጽታ ግልጽ ለማድረግ ድርጅቱን የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ብሎ ጠራው። በዚህም ብዙዎችን ስቦና ድርጅቱ የቅንጅት መሠረትና ግድግዳ ሆኖ በምርጫ 97ድል ነሣ።
ያረፈው ኃይሉ ሻውል ነው እንጂ የጀግንነት ኃይሉስ ለትግል አርአያነት አብሮን አለ። ያረፈው ኃይሉ ባንዲራ ዝቅ ብሎ ይከበርለት፤ ሕያው የኃይሉ ራእይ፥ መጽሐፋችን “አገሪቱን ያላንዳች ቸር ሰው
አያስቀራትም” እንደሚለው፥ በአቶ ማሙሸት አማረ መሪነት ይቀጥል። ባለቤቱን፥ ልጆቹን፥ ዘመዶቹንና ወዳጆቹን እግዚአብሔር ያጽናቸው። ነፍሱን በቴዎድሮስ፥ በዮሐንስ፥ በምኒልክ፥ በኃይለ ሥላሴ ድንኳን ያኑርልን።

No comments:
Post a Comment