በኢትዮጵያ እስረኞች አጥንትን ቀስ በቀስ በሚያፈርስ መርዝ እየተጠቁ መሆኑን ታውቁ ኖሮዋል? – አ.ከ (ከአዲስ አበባ)
ከጥቂት ዓመታት በፊት የግንቦት ሰባት መሪዎች እና አባላት መታሰራቸው ይታወሳል።ብዙዎቹ ቃሊቲ የሚገኘው እስር ቤት ነበሩ።በእስር ቤት እያሉ በደረሰባቸው ያልታወቀ ሕመም ምክኒያት ሕይወታቸውን ያጡ መሪዎችም ነበሩ።ታዲያ አንዴ ከሜክሲኮ ወደ ሃያሁለት በታክሲ ተሳፍሬ ስሔድ በግምት የሃያ ዓመት ዕድሜ ያለው ልጅ ታክሲው ውስጥ ገብቶ አጠበጌ ተቀመጠ።
ታክሲው ሞልቶ መሔድ ሲጀምርም ወንድሜ ይቅርታህን የታክሲ ትከፍልልኛለህ ብሎ ጠየቀኝ።ዞር ብዬ ያየሁት ይህን ሲል ነበር።ድንጋጤ እና መሸማቀቅ ይነበብበት ነበር።ልቤ በጣም አዘነለት።ምን ሆነህ ነው? ከዬት ነው የምትሔደው፤ወዴት ነው የምትሔደው ብዬ ጠየኩት።እርሱም ከቃሊቲ እስርቤት ዛሬ መለቀቄ ነው አለ።ለምን ታሰርክ እንዴትስ ተለቀክ ስለው የቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ እንደነበረ እና ከመንገድ አፍሰው ወደ እስር ቤት እንደጣሉት ነገረኝ።የግንቦት ሰባት አባል እና ደጋፊ ናችሁ ብለው ቀን ከለሊት ሲገርፉን፤ሲያስርቡን፤መዓት መከራ ደርሶብናል፤እንደምታዬው አእምሮዬ እራሱ ልክ አይደለም።ነገር ግን በጣም ጤነኛ ልጅ ነበርኩ ብልህ አታምነኝም፤ድሮም ትንሽ እብድ ነገር ነበርክ ብለህ ብታስብ አይገርመኝም አለ።
ፍርድቤት የሚባል ነገር አይተን አናውቅም።መጀመሪያ ላይ ቤተሰብ እንዲጠይቀን ተፈቅዶላቸው ይጠይቁን የነበረ ሲሆን በኋላ ግን ተከለከሉ።ቤተሰቦቼን በአይኔ ካየሁ ሁለት ዓመት ሊሆነኝ ነው አለ።ከዚያም ወዲያው ስለራሱ ትቶ ሁላችንም ስለምናውቃቸው እና በግንቦት ሰባት ሰበብ እስርቤት ተጥለው ስለነበሩ መሪዎች ይነግረኝ ጀመር።እነአቶ እከሌ እኛ ጋ ነው ታስረው የነበሩት።እንላላካቸውም ነበር።ምንም እንኳን እነርሱ እንደ እኛ ወደውጪ ብዙውን ግዜ እንዲወጡ ባይፈቀድላቸውም ፀሐይ እንዲሞቁ በሚያወጡዋቸው ሰዓት እየተላላክን የሚፈልጉትን እንገዛላቸው ነበር።ከቆይታ በኋላ እነ አቶ እንትናን እና አቶ እንትናን ከሌሎች ለይተው ሌላ ክፍል ውስጥ አሰሩዋቸው።በኋላም እይናችን እያየ ሰውነታቸው መፈራረስ ጀመረ።አፍንጫቸው፤ጆሮዋቸው፤አይናቸው ጣታቸው የስጋ ደዌ እንደያዘው ሰው ይፈራርስ ጀመር።አንድቀን ሊልኩኝ ሲጠሩኝ በድፍረት ምን ሆናችሁ ብዬ ስጠይቅ እንደፍሊት ያለ መርዝ እየረጩዋቸው መሆኑን ነገሩኝ።መድሃኒቱንም እድሜ ለቻይና እናንተን የማሰናበቻ ቀላል መንገድ ተገኘ እያሉ ይፎክሩብናል፤ይስቁብናል፤የውሸታቸውን ሆስፒታል ይወስዱናል።ለቤተሰባችን ታመዋል ብለው ይነግራሉ ብለው ነገሩኝ አለ።
ከዚያስ በኋላ ስለው ቀስ በቀስ መንቀሳቀስ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደረሱ።በሚያስጠላ ሁኔታ ሰውነታቸው እየፈራረሰ ስለነበረ መሸፋፈን ጀመሩ።መጀመሪያ ወደዚያ ክፍል ከገቡት መካከልም እነ አቶ እንትና ሞቱ።ታመው ሞቱ ተብሎ ሲነገር ሰማን አለ።
ቤተሰብ እንዳያያችሁ ለምን ተከለከለ ብዬ ስጠይቀው፤ምክኒያቱን አላወቅንም ነበረ።በኋላ ግን ቤተሰባችን እንዳያዬን ከከለከሉ በኋላ ምግብ ያመጡልን ጀመረ አለ።ምግባቸውን መብላት ስለቀፈፈን የበላን እያስመሰልን እንደፋ ነበረ፤ወደውጪ የመውጣት እድል ስናገኝም የሌሎች እስረኞችን ትራፊ እንበላ ነበር።ከቆይታ በኋላ ግን ምግቡን እንድንበላ አስገድደው እንቢ ስንል የሆነ መርፌ ወጉን።ቀስ በቀስ ሰውነታችን እየደከመ ሔደ፤ቀስበቀስ አእምሮዋችንም እየጨለመ ሲሔድ ይታወቀን ጀመር።አንዳንዶቹ ልጆች ከሌሎቻችን በበለጠ መልኩ እንደ እብድ የለየላቸው ሆኑ።ታመውነው እያሉ ሆስፒታል ይወስዷቸዋል።የአእምሮ ጭንቀት ነው እያሉ የስነልቦና ጠበብት መጥተው እንዲጎበኟቸው ያደርጉ ነበር።ከዚያ አውጥተው መንገድ ላይ ይጥሏቸዋል።ስንቶቹን ቤተሰብ እንዳገኛቸው እግዚአብሔር ብቻ ያውቃል አለኝ።
ሰፈሩን ያውቅ እነደሆነ ስጠይቀው በጣም ደስ አለው።አዲሳባ ሃያሁለት ተወልጄ ያደኩ መሆኑን እና ቦሌ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እንደነበርኩ ነግሬህ ቤቴን እንደማውቅ ስትጠይቀኝ ችግሬ በጣም ገብቶሃል ማለት ነው አለኝ።እስከ ቤተሰቡ ቤትም ሸኘሁት።ያ ልጅ ምን ላይ እንደደረሰ አላውቅም።ነገር ግን እግዚአብሔር በጥበቡ ካልደረሰለት በስተቀር በሕይወት አለ ብዬ አልገምትም።
ይህ ነገር ወደአእምሮዬ የመጣው ትላንት የአሜሪያ ድምፅ ሬድዮን ዜና ስከታተል አንድ ቸው ብሔሩ ኦሮሞ የሆነ ኮማንደር በሰበታ የታሰሩ ልጆችን በተመለከተ የአጋዚ አዛዦች ስብሰባ ጠርተውን ለታሰሩት ልጆች ከምግብ ጋር መርዝ እንድንሰጣቸው መመሪያ ተላልፎልናል ብለው በመቆርቆር ሲናገሩ ስሰማ ነው።ከምንም ግዜ በላይ አሁን አደጋ ላይ መሆናችን አሳሰበኝ።በየእስር ቤት የታጎሩ የኦሮሞ እና የአማራ ልጆች እጣ ፈንታ ይሔው የተባለው መርዝ መሆኑ እረፍት ነሳኝ።
አሁን ሊበሉን ተነሱ ማለት ነው።አሁን ቤተሰብ ለልጆቹ መድረስ ይኖርበታል።ልጆቹ በእጁ እንዲገቡ እስኪያደርግ ድረስ ቤተሰብ መተኛት የለበትም።ይህ እንዲሆን ደግሞ ቤተሰብ ሚስጥሩን መረዳት ይኖርበታል።
ይህ ዜና እንዲሰራጭ ማድረግ አንዱ የመከላከያ መንገድ ሊሆን ስለሚችል እባካችሁ ለዚህ ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ዘገባችሁን አጠናክሩ።ወደ ሕዝቡ ሊደርስ በሚችልበት በማንኛውም መንገድ ይህ ዜና ይሰራጭ።እውነት መሆኑን ማመን ቢያቅታችሁም እንኳን በማሰራጨታችሁ የምትጎዱት ነገር ግን የለም።
No comments:
Post a Comment