በቢሾፍቱ ከተማ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው አደጋ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞን ለመቆጣጠር ሲሉ በከፈቱት የተኩስ ዕርምጃ መሆኑን መቀመጫውን በዚህ በአሜሪካ ያደረገ አንድ አለም አቀፍ ተቋም ማክሰኞ አስታወቀ።
ፍሪደም ሃውስ የተሰኘው ይኸው የሰብዓዊ መብት ተቋም የኢትዮጵያ መንግስት ድርጊቱ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ፈቃደኛ መሆን ይኖርበታል ሲል ጥሪውን አቅርቧል።
የመንግስት ባለስልጣናት ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች በበዓሉ አከባበር ስፍራ ተፈጥሮ በነበረ ግፊያና መረጋገጥ እንዳለሆነ ሲገልጽ ቆይተዋል።
ይሁንና በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫን ያወጣው ፍሪደም ሃውስ የጸጥታ ሃይሎች ለበዓሉ በታደሙ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ጥይትን ጨምሮ አስለቃሽ ጢስ በመክፈታቸው ምክንያት አደጋው ሊደርስ መቻሉን ገልጿል።
በእስካሁኑ ሂደትም ከ150 በላይ ሰዎች ሞት ማረጋገጥ መቻሉን አመልክቷል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በተለያዩ ጊዜያት የተቀሰቀሱ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር ሲሉ ከመጠን ያለፈ የሃይል ዕርምጃን ሲወስዱ እንደነበር የሰብዓዊ መብት ተቋሙ አክሎ ገልጿል።
ይኸው ድርጊት በእሬቻ በዓል አከባበር ወቅት መደገሙን የተናገሩት የድርጅቱ የአፍሪካ ዳይሬክተር ቡካሲን ፔትሮቺች ድርጊቱ በአስቸኳይ በገለልተኛ አካል ምርመራ መካሄድ እንዳለበት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
No comments:
Post a Comment