Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, October 21, 2016

የጣሊያን ጀነራል የማረኩ ብርጋዴር ጀነራል ለማ ገ/ማርያም አረፉ


የጣሊያን ጀነራል የማረኩ ብርጋዴር ጀነራል ለማ ገ/ማርያም አረፉ





(ሙሉጌታ ኃይሌ)

ብርጋዴር ጀነራል ለማ ገ/ማርያም ይባላሉ፡፡ የማይጨው ዘማች ነበሩ፡፡ በተወለዱ በ99 አመታቸው መስከረም 23 2009 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ ከማይጨው ዘመቻ ተርፈው እስካሁን በሕይወት ይኖሩ ከነበሩት የመጨረሻው እሳቸው ነበሩ፡፡

ከነፃነት በፊት ሜጀር የሚለው የወታደር ማዕርግ ያገኙ የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ሲሆኑ ከነፃነት በኋላም የመጀመሪያውየአባዲና ፖሊስ ምሩቅ ሆነው የፖሊስ ሠራዊትን ወደ ዘመናዊነት ከአሸጋገሩትአንዱና ዋናው ነበሩ፡፡

በዘመናቸው ከሚታወቁበት ታሪካቸው አንዱ፣በ1934 ዓም ጎንደር ላይ የፋሽስትን የጦር መኮንኖች ለመማረክ በተደረገው የቤት ለቤት አሰሳ ላይ በአደረጉት አስተዋፆ ነው፡፡

ከነበሩበት አሳሽ ቡድን ፊት ቀደም ብለው ከሩቅ የነጭ ባንዲራ ወደሚውለበለብበት ባንኮ ዲሮማ ጠጋ ብለው በሩን ከፍተው ቢገቡ፣የጣሊያን ከፍተኛ መኮንኖች መሠሪያቸውን መሬት ላይ አስቀምጠው ጠረጴዛ ከበው ካርታ ሲጫወቱ ያያሉ፡፡ ይሄን ሁሉ መኮንን በአንድጊዜ መማረክ ስለማይችሉ እርዳታ ለመጠየቅ በሌላ በር ሊወጡ ሲሉ፤ በአንድ ትንሽ ክፍል ውስጥ የሸዋ ገዢ የነበረውን ጀነራል ናዚን፣ቤተወደድ አስፋሐ ወ/ሚካኤል(ኤርትራዊው አስተርጎሚ) እና አቶ አሊ (የጀነራል ናዚ ልብስ አልባሽ)በአንድ ላይ አዝነው እንደተቀመጡ ይመለከታሉ፡፡ እነዚህን መማረክ እችላለሁ ብለው “እጅ ወደ ላይ”ሲሉ፣ቢትወደድ አስፋሐ “እንደ ጀነራል ናዚ አይነት ከፍተኛ መኮንን በአንተ ሳይሆን በእንግሊዝ ከፍተኛ መኮንን ነው መማረክ ያለበት”ብለውሲያንገራግሩ ወዲያው የእንግሊዝጦር ደርሶ ሁሉም አንድ ባንድ እጃቸውን ሊሰጡችለዋል፡፡

የእንግሊዝ ጦር ጄነራል ናዚን ማረከንብለው እንዳይኩራሩ በጎንደር ከተማ ለነበሩት ለልዑል አልጋወራሽ አሰፋወሰን ኃ/ሥላሴ ምርኩኞቹ በሙሉእንዲተላለፉ አድርገዋል፡፡

ይህም ስራቸው ልዑል አልጋወራሽ ከነፃነት በኃላ የሙሉ ጄነራልነት ማዕርግ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥምይሄ ሹመት ለመጀመሪያጊዜ መሰጠቱ ነበር፡፡

ለዚህ ታሪክ እውነታ ቢትወደድ አስፋሐ ወ/ሚካኤልለጀነራል ለማ በሰጡት የምስክርነት ደብዳቤ ላይ ተረጋግጦል፡፡


የጄነራል ለማ ገ/ማርያም አጭር የሕይወት ታሪክ

ጄነራል ለማ ከአባታቸው ከጎጃሙ ተወላጅ ከአለቃ ገብረ ማርያም አለምነህና ከእናታቸው ከቡልጋዋ ተወላጅ ከወ/ሮ ፋንታዬ ዘለሌ በ1910 ዓም በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር በነበረችው የኬኒያ ሞያሌ ከተማ ተወለዱ፡፡ በኪኒያ የተወለዱበት ምክንያት አባታቸው በእንግሊዝና በኢትዮጵያ መሐከል የነበረውን የወሰን ክልል አስከባሪ ስለነበሩ ነው፡፡

ጄነራል ለማ እድሜያቸው ለትምሕርት እንደደረሰ በአዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ገብተው በጊዜው ይሰጥ የነበረውን ትምሕርት አጠናቀዋል፡፡ በ1926 ዓ.ም. በውትድርና ተቀጥረው በምሕንድስናትምሕርትለሁለት ዓመት ሰልጥነው ተመርቀዋል፡፡ በ1928 ዓም የጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ ከመጀመሪያዎች እጩ መኮንኖች ጋር በመሆን በክብር ዘበኛ ጦር ውስጥ ማይጨው ዘምተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ተሸንፎ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ፣ በመርዝ የተጎዳው ሰውነታቸው እስኪአገግም ድረስ በዘመዶቻቸው ቤት ውስጥ ተሸሽገው ተቀመጡ፡፡

የካቲት 12/1929 ዓም ግራዚያኒን ለመግደል በተደረገው ሙከራ ጣሊያን ለበለጠ በቀል የቤት ለቤት አሰሳ በሚያደርግበት ጊዜ ጄነራልበለሊት አምልጠው ወደ ጎጃም ሄዱ፡፡

ጎጃም ሲደርሱ ከአርበኛው ካሳ ብሩ እና ከራስ መስፍን ስለሺ ጋር ተቀላቅለው የአርበኝነት ሥራቸውመስራት ጀመሩ፡፡

ከእንግሊዝ ሀገር ከጃንሆይ ዘንድ የተላኩትን ፀሐፊ ትእዛዝ ሎሬንዞ መብራቱን አግኝተው አብረው ወደ ቤጌምድርና ጎጃም በመሄድ የመረጃ ስራ አሰባሰበው ተመለሱ፡፡

በመቀጠልም ሱዳን ከነበረው ከእንግሊዝ ጦር መሪ ሜጀር ቼዝማን በርካታ መሳሪያ በመረከብ እራሳቸውንና የጎጃምን አርበኞችን በተሻለ መሳሪያ አስታጠቁ፡፡

መስከረም 18/1932 ዓም በእንግሊዛዊው በጀነራል ሳንፎርድ በተቋቋመው ሚሽን 101 በተባለው የመረጃ ሰብሳቢ ኮሚቴ ውስጥ ተመድበው በሚስጥር ስራ ውስጥ ገቡ፡፡ በኮሮኔል ዊንጌት በሚመራው የጌዲዮን ጦር ውስጥ ሜጀር ተብለው የ5ሺ (እጁን የሰጠ የባንዳ ምርኮኛ) ሠራዊት መሪ ሆነው እስከ ቡሬ ከተማ ድረስ የነበረውን የጣላት ምሽጎችን አስለቀቁ፡፡

“ባንዶች ሀገራችሁን እንደጎዳቹሁ ዛሬ ደግሞ የምትክሶት ጊዜ ነው” እያሉ የሠራዊታቸውን ሞራል ይገነቡ ጀመረ፡፡የዚህ ምስክርነት ማስረጃ የተገኛው ክቡር አቶ ጌታሁን ተሰማ በፃፉት ማስታዋሻ ላይ ነው፡፡

ብ/ጄነራል ለማ የኢትዮጵያ ነፃነት ከተመለሰ በኋላ በየቦታው ደፍርሶ የነበረውን ሰላም ለማስከበር በወሎ፣ትግራይና ሐረር ተንቀሳቅሰዋል፡፡



በተለያዩ ጊዜያት የሚከተሉትን የሀላፊነት ግዴታዎችንአከናውነዋል፡፡

1. ከ1941-42 ዓ.ም. የወሎ ፖሊስ ዋና አዛዥ

2. ከ1942-49 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የወንጀል ምርመራ ሐላፊ

3. ከ1949-50 የመላው ወህኒ ቤቶች(እስርቤት)አዛዥ

4. ከ1952-53 የኤርትራ ፀጥታ አዛዥ

5. ለጥቂት ጊዜ የመተሐራናወንጂ ስኳር ሀላፊ

6. ከ1953-1956 የሕዝብ ደሕንነት ዋና ሐላፊ(የኮሮኔል ወርቅነህ ገበየሁ የነበረ ቦታ)





General Lemma



የ53ቱን የመንግስት ግልበጣ መሪ የነበሩትን ጀነራል መንግስቱ ነዋይን መርምረዋል(የዚህ ሙሉ ታሪክ በአቶ ታደሰ ቴሌ ሳልቫኖ በተፃፈው ገድለ መፈንቅለ መንግስት ማግኘት ይቻላል)ከዘጠኝ ዓመት በፊት በ1942 ዓም ከጀነራል መንግስቱ ነዋይ ጋር ሆነው የቤተወደድ ነጋሽ በዛብህን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራን በጋራ አክሸፋዋል፡፡(የዚህ ሙሉ ታሪክ በአቶ በሪሁን ከበደ የአፄ ኃ/ሥላሴ ታሪክበሚለው መፅሐፍ ላይ ይገኛል) ጀነራል ለማ ከመንግስቱ ነዋይ በኋላ አራት የተለያዩ ያልተነገረላቸው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎችን አክሸፋዋል፡፡ “ኩዴታ ደጋግሞ ያከሸፈ መልሶ ኩዴታ ከማድረግአይመለስም” በሚል ብሒል ጀነራል ለማ ወደ ጋምቤላ አገር አስተዳዳሪነት እንዲዛወሩ ተደርጓል፡፡

7. ከ1956-1962 ዓ.ም. የጋምቤላ አውራጃ ገዢ ሆነው ለረዥም አመታት ሠርተዋል፡፡

በአራጃው ዘመናዊ ትምህርት ቤት እና የጤና ክሊኒክ እንዲቋቋሙ አድርገዋል፡፡

ለዚህ መልካም አስተዳደራቸው የአለፋው ዓመት የጋምቤላ ፕሬዜዳንት ክቡር አቶ ኦልኤሮ ኦፒዮ በጋምቤላ በተደረገው የብሔር ብሔረሰቦች ክበረ በዓል ላይ በክብር እንዲገኙ ጥሪ አቅርበውላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን

በሐኪማቸው ትእዛዝ መሠረት በእዚህ እድሜ በአውሮፕላን መብረር አይችሉም ተብለው ሳይገኙ ቀርተዋል፡፡

ታዋቂው የጋምቤላ የሥዕል ባለሞያ አቶ ሐሰን ኦፒዮ ለዛሬው ማንነቱ የጀነራል አሻራ እንዳለበት በአንድ ወቅት ሲናገር “ጀነራል ኒውሲክና ታይምስ የተባሉትን የእንግሊዘኛ መፅሔቶችን በረንዳቸው ላይ ቁጭ ብለው ሲያነቡ፣አንድ ቀን እንደሳቸው እሁናለሁ ብዬ እምኝ ነበር” በማለት የማይረሳውን የልጅነት ትውስታውን ገልፆአል፡፡

የጀነራል ዝና ከጋምቤላ አንስቶ አዲስ አበባ ደርሶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ታሪክ ያስረዳል፡፡ እሳቸውየጋምቤላ አውራጃ ገዥ ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባ ውስጥ ወጣቶች የጋምቤላን ተወላጅ ሲመለከቱ “ለማ!” ብለው ይጣሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡

አንዳንዶች ቃሉ ሲደጋገም ስድብ ይመስላቸዋል፡፡ ነገር ግን በጋምቤላ (በአኝዋክ፣ ኑዌር፣ ) “ለማ” ለሚለው ፍቺካለጀነራል ስም በስተቀር ሌላ ፍቺ ያለው ቃልማግኘት አይቻልም፡፡

ጀነራል ለማ በ1960 ለመጀመሪያ ጊዜ የሱዳን ስደተኞች ወደ

ኢትዮጵያ በሚገቡበት ጊዜ ላደረጉት ከፍተኛ የሰብአዊ ርሕራሄ ሥራ የዓለም ስደተኞች ድርጅት UNCHR የልዩ እውቅና ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡ ዛሬከነዚህ ሰደተኞች መሐከል አብዛኞቹ ዛሬ ኢትዮጵያዊ ለመሆን በቅተዋል፡፡የዛሬ 50 ዓመት የደቡብ ሱዳን የነፃነት ታጋዮች የመረጃ አሰባሰብና የሬዲዮን ግንኙነት የተማሩት በጀነራል መኖሪያ ቤት ውስጥ እንደ ነበር የነፃነቱ መሪ የነበሩት ጀነራል ጋራንግ ስለ ኢትዮጵያ ውለታ ሲናገሩ ጠቅሰውታል፡፡

8. ከ1962-64 ዓ.ም. በሀገር ግዛት ውስጥ የወሰን አስተዳደር ም/ሚኒስትር ሆነው ተሾመዋል

9. 1964-68 ዓ.ም. የአሰብ አስተዳደር ዋና ሀላፊ ሆነዋል፡፡

ጀነራል ለማ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር መሪዎች የተለያዩ ኒሻኖችና ሜዳሊያዎችን አግኝተዋል፡፡ ከነዚህ በጥቂቱ

1. የዳግማዊ ሚኒሊክ ሜዳይ

2. የክብር ኮኮብ ኒሻን

3. የአጥቢያ ኮኮብ ኒሻን

4. የረዥም ጊዜ አገልግሎት ኒሻን

5. የሰብአዊ አገልግሎት ኒሻን

6. ከእንግሊዝ መንግስት የተሰጠ ሁለት በአንገት ላይ የሚጠለቅ ኒሻኖች

7. ከይጎዝላቪያ ፕሬዚዳንት ማርሻል ቲቶ የተሰጠ ኒሻን

8. ከሱዳን መሪ ከጀነራል አቡድ የተሰጠ የሀገሪቱ ከፍተኛ ኒሻን

ጀነራል ለማ የዛሬ ሦስት ዓመትለቫቲካን መሪ ለፖፕ ፍራንሲስ የመጨረሻው ጸሎቴ በሚል ርእስ ደብዳቤ መፃፋቸው ይታወቃል፡፡ የዚህ ደብዳቤ ሙሉ ቃል ከዚህ ደብዳቤ ጋር ተያይዞል፡፡

ጀነራል ለማ ሕይወታቸው ከማለፉ አንድ ሳምንት በፊት ጤናቸውና አእምሮቸው የተሟላ በሽታ የማያቃቸው እድለኛ አዛውንት ነበሩ፡፡ ዘወትር እሁድ ቤተክርስቲያን የማይቀሩ፤ ወርሐዊ የእድር መዋጮ ለመክፈል ወደ ፓሊስ ክበብ እና የጡረታ ገንዘባቸውን ለመቀበል በየወሩ የሚሄዱ ነበሩ፡፡(የጡረታ አበላቸው 1300.15 ሳንቲም ሲሆን በአሜሪካን ዶላር 54 ብቻ ነው፡፡ የዛሬ 45 ዓመት የጡረታ ገንዘባቸውን ማስቀመጥ ሲጀምሩ የአንድ ዱላር ምንዛሪ 2.15 ሳንቲም ነበር፤ ዛሬ 22 ወይንም 24 ብር ሆኖል፡፡) ለጀነራል መከፈል የነበረበት አበል በአሁኑ ምንዛሬ31,200 ብር መሆን ነበረበት፡፡ ጀነራል ስለ ሆኔታው ሲገለፁ “ያልታወጀ ጦርነት በሸማገሌዎች ላይ” ይላሉ፡፡

የዛሬ አራት ወር የጀርመን ሺፐርድ ውሻቸው ወልዳ ወንዶች ቡቻላዎችን በ900 ብር፣ ሴቶቹን ደግሞ በአንድ ሺ ብር ይሸጡ እንደ ነበር ታይተዋል፡፡ ምንአልባትም በ99 ዓመት ዕድሜ ገንዘብ የሚሠራየመጀመሪያው የዓማችን ሰው ሳይሁኑ አይቀርም፡፡

እኝህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ መቶ አመት ሊሞላቸው ሦስት ወር ብቻ ሲቀራቸው በድንገተኛ ሕመም መስከረም 23 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተው መስከረም 25 ቀን በጳውሎስ ጴጥሮስ ቤተክርስቲያን አስከሪናቸው በክብር አርፏል፡፡

እንዲህ አይነት ጀግና ሲያርፉያገለገሏት ሀገራቸው የጀግና አቀባበር ልታደርግላቸው በተገባ ነበር፤ ነገር ግን የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ያለፈው ታሪኳን እና ባለውለታዎቿን እረስታ እነሱም የዛሪቱን ኢትዮጵያ እረስተው በብቸኝነት ኖረው አንድባንድ ሁሉም በየተራ ለዘላለሙ

እየተለዩን ሄዱ፡፡

ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝነሸ ተላላ

የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ


You can reach the writer at – mulugetahaile123@gmail.com

No comments:

Post a Comment

wanted officials