Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, October 23, 2016

ኢትዮጵያ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ስጋት #Amnesty

ኢትዮጵያ እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ስጋት

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግሥት ለስድስት ወራት የደነገገዉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወትሮም በቋፍ የነበረዉን የሰብዓዊ መብት ይዞታ ወደ ከፋ ደረጃ ሊያሸጋግረዉ እንደሚችል እያሳሰቡ ነዉ።


አውዲዮውን ያዳምጡ።04:16

አምነስቲ ኢንተርናሽናል

 አምነስቲ ኢንተርናሽናል መንግሥት የሚቀርቡበትን ተቃዉሞዎች ለማቀዝቀዝ የሚወስዳቸዉ ርምጃዎች ይበልጥ አባባሽ እየሆኑ መሄዳቸዉን ትናንት ባወጣዉ መግለጫዉ አመልክቷል። ቻተም ሃዉስ የተሰኘዉ የብሪታኒያዉ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ምርምር ተቋም ለሩብ ምዕተ ዓመት በትረ ሥልጣን ጨብጦ የሚገኘዉ ገዢ ፓርቲ ሚናዉን እና ኅብረተሰቡን የሚረዳበትን ሁኔታ ዳግም ሊያጤን ከሚገባዉ ደረጃ ላይ መድረሱን አሳስቧል።
ከ25 ዓመታት የስልጣን ዘመን በኋላ ገዢዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በምህጻሩ ኢህአዴግ፤ በጣም ወሳኝ ለዉጥ ማድረግ የሚገባዉ ወቅት ላይ ደርሷል ያላል፤ ቻተም ሃዉስ። በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ዉስጥ የደነገገዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም የሀገሪቱን ምክር ቤት ወንበሮች ከነአጋር ድርጅቶቹ የተቆጣጠረዉ ኢህአዴግ፤ በሀገሪቱ ሥርዓት ማስከበር አለመቻሉን መቀበሉን እንደሚያመለክትም ቻተም ሃዉስ ትናንት «የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከመሪዎቹ በላይ ሆኗል?» ሲል ይፋ ያደረገዉ ጽሑፍ ይዘረዝራል። ጽሑፉ አክሎም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ይፋ ባደረጉበት ወቅት፤ የምርጫ ሂደቱ ላይ ማሻሻያ እና ከተቃዉሞ ፖለቲካ ኃይሎች ጋርም ዉይይት ሊደረግ እንደሚችል ጠቁመዉ እንደነበርም ያስታዉሳል።
መረዳት የሚገባዉ ዋናዉ ነገርም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚታየዉ ተቃዉሞ የተነሳዉ የትጥቅም ሆነ ሰላማዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ በሚያደርጉ ኃይሎች ሳይሆን ከተራዉ ሕዝቡ መሆኑንም ቻተም ሃዉስ ያመለክታል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ በሀገሪቱ ተቃዉሞዉ የተባባሰዉ መንግሥት ገንቢ በሆነ መንገድ ተቃዋዉን ማስተናገድ ስላልቻለ እንደሆነ በመግለጫዉ ገልጿል። የአፍሪቃ ቀንድ ተመራማሪ አቶ ፍሰሃ ተክሉ እንዴትነቱን ይናገራሉ።
Äthiopien Protesten der Oromo in Bishoftu (REUTERS/File Photo/T. Negeri)
አምነስቲ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ የማሠር እና የተሃድሶ ርምጃዎች ከዚህ ቀደም ሲወሰዱ፤ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች በዘፈቀደ እየታሰሩ ቤተሰብም እና ጠበቆቻቸዉ በማያገኟቸዉ ሩቅ በሆኑ ወታደራዊ ጣቢያዎች እንዲታሰሩ ማድረጉን በመግለጫዉ ጠቁሟል። ለስድስት ወራት የሚዘልቀዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም እጅግ ሰፊ እና መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶችን ስጋት ላይ የሚጥል መሆኑን አመልክቷል። በአንድ ሀገር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ የመናገር፣ የመፃፍ እና መረጃዎችን በነፃነት የማግኘቱ መብት ሊገደብ እንደሚችል ያመለከቱት አቶ ፍሰሃ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ የተደረገዉ ግን ካለዉ ሁኔታ ጋር የተመጠነ አይደለም ነዉ የሚሉት። አክለዉም ካለፈዉ ዓመት ኅዳር ወር አንስቶ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚካሄደዉን ሕዝባዊ ተቃዉሞ መንግሥት በኃይል ፀጥ ለማድረግ የሚወስደዉ ርምጃ ያባብሰዋል እንጂ አይፈታዉም ብለዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ
http://www.dw.com

No comments:

Post a Comment

wanted officials