ታደሰ ብሩ
በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የትናትና ንግግር ውስጥ “ … ይህ የባርነት አዋጅና የአዋጁ ባለቤት ህወሓት/ኢህአዴግ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ መንገዶች “መሠረተ-ልማቶች” ሳይሆኑ መሠረተ-ጥፋቶች ናቸው፤ አውራ ጎዳናዎች አስጠቂዎቻችን ናቸው” የምትል ዓረፍተ ነገር አገር አለች።
“የተከበሩ” ኮካዎች “እንዴት አንድ የኢኮሚክስ ባለሙያ መሠረተ ልማቶችን መሠረተ ጥፋቶች ናቸው” ይላል ብለው እንደሚንጨረጨሩ እገምታለሁ።
“መሠረተ-ልማቶች” “መሠረተ-ጥፋቶች” ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያዊያን ያስተዋወቀው (እኔ እስከማውቀው ድረስ) ነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ ነው። የነጋድራስ ገብረሕይወትን ያህል የሕዝብ አስተዳደርና የኢኮኖሚ ግኑኝነትን የተረዳ ምሁር እንኳንስ ያኔ ዛሬም መኖሩ አጠራጣሪ ነው። ከዛሬ 93 ዓመታት በፊት በ1916 ዓም በታተመው “መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር” በተሰኘው መጽሀፉ ውስጥ “መሠረተ-ልማቶች” “መሠረተ-ጥፋቶች” ሊሆኑ እንደሚችሉ ውብ በሆነ አገላለጽ ተንትኗል።
ነጋድራስ ገብረሕይወት በመጀመሪያ የአጴ ሚኒሊክ በኋላም የአጴ ኃይለሥላሴ ባለሟል ሆኖ ለፈጣን ልማት የታገለ ቢሆንም እንኳን ለሕዝቡ ደህንነት የሚጨነቅ መንግሥት በሌለበት አገር ውስጥ ዕውቀት አይሰፋፋም፤ ዕውቀት በሌለበት ደግሞ መሠረተ ልማት ቢስፋፋ ጥፋትን እንጂ ልማት አያመጣም በማለት በጣም ጠንካራ ቃላትን ተጠቅሞ ይተቻል።
በቅድሚያ የመንግሥት ሥራ ምን መሆን እንዳለበት የገለፀበትን ለ 93 ዓመታት ሰሚ ያጣ አንቀጹን ላስቀድም
“በእያንዳንዱ መንግሥት የሚያድሩ ብዙ ልዩ ልዩ ነገዶች ይኖሩ ይሆናል። ስለሆነ መንግሥት አንዱን ነገድ አጥቅቶ ሌላውን ነገድ ለመጥቀም ሥራው አይዶለም። አስተካክለን ካሰብን ዘንድ መንግሥት መቆሙ ለሕዝቡ ሁሉ ጥቅም ነው። መንግሥት ሕዝቡን ሁሉ በትክክል ለመጥቀም ካላሰበ መንግሥት በዙፋኑ ሊቆም አይችልም። ላንዱ ነገድ ወይም ለጥቂት ሰዎች ብቻ ማድላት ለመንግሥት የሚገባ ሥራው አይደለም።” ገጽ 14
ቀጥሎ ስለ መሠረተ ልማቶች ወደሰጠው ትንተና ልለፍ።
ነጋድራስ ይህን መጽሀፍ በፃፈበት ወቅት (ከሞተ በኋላ ነው የታተመው) የጅቡቲ- አዲስ አበባ የምድር ባቡር ግምባታ እና የአቢሲኒያ ባንክ መቋቋም የዛሬውን ህዳሴ ግድብና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ያህል በሥርዓቱ ባለስልጣኖች የሚወደሱ እንደነበሩ መገመት ይቻላል። ነጋድራስ ግን እነዚህ ፕሮጀክቶት ሳይቀር በሚከተለው መንገድ በድፍረት ተችቷቸዋል።
“ዕውቀት በሌለው ሕዝብ አገር መንገድና የምድር ባቡር ቢሠራ ሕዝቡ እንዲደኸይ ያፋጥናል እንጂ፤ አይጠቅመውም። ጥቅሙ ከርሱ ጋር ለሚገበያዩ ዐዋቂዎች ሕዝቦች ነው” ገጽ 75
“የሚበላውንና የሚለብሰውን ያጣ ድኻ የተወለደበትን አገር የሚወድበትን ምክንያት ያጣልና ያገሩ መንግሥት ቢበረታ ለሕዝቡ ማሠልጠኛ የሚሆነውን ነገር ሁሉ የምድር ባቡር በፍጥነት ሲያመላልስ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ርስ በርሱ ሲለዋወጥና ባንኩም በሰበሰበው ገንዘብ ሲረዳ፤ የኢትዮጵያ መንግሥትም ሕዝቡን ለማሠልጠን ቢነሳ ማለፊያ አጋዦች ይሆኑት ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህ ሐሳብ ከሌለው ግን የምድር ባቡርና ባንኩ ወዳገራችን አመጣጣቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ መቃብር ለመማስ እንደሆነ ጥርጥር የለውም።” ገጽ 127 -128
=====
NB: የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ለነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ የክብር ዶክሬት ሰጥቷል። እኔ መቀሌ ዩኒቨርስቲ ከሰጣቸው የክብር ዶክሬቶች ተገቢ የምለው ብቸኛ የክብር ዶክሬትም ይህ ነው።
No comments:
Post a Comment