የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ – ምናባዊው አጥር ለምን አስፈለገ [መላኩ ወልደስላሴ- ከአትላንታ]
እንደሚታወቀው የብሄራዊ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው በህዝብ ህይወት ጤናና ደህንነት ላይ የተጋረጠ አደጋ ሲያጋጥምና ያንንም በተለመደው በመደበኛው የህግ ማስከበር ስርአት መቆጣጠር አይቻልም ተብሎ ሲታመን ነው።ከዚህ በፊት ያልነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተለመደው የመደበኛው የአስተዳደር ቅኝት በተለየ መልኩ እንዲተገበሩ የሚደነግጋቸው ጉዳዮችን ይዘረዝራል።ልብ ማለት የሚገባን ከተለመደው የመደበኛው የአስተዳደር ቅኝት በተለየ የሚለውን ቃል ሲሆን ምንም አዲስ ለውጥ የማያመጣ ከሆነ አዋጁ ትርጉም አይኖረውም።
ህንዶች ካስተናዷቸው የአስቸካይ ጊዜ አዋጆች አንዱ ከጁን 1975 እስከ ማርች 1977 ለሃያ አንድ ወራት የቆየው በጠቅላይ ሚንስትሯ ወይዘሮ ኢንድራ ጋንዲ የተደነገገው በይዘቱ ለየት ያለ ነበር።ያም አዋጁ የወጣው ህንድ በራሷ የውስጥ የፖለቲካ ቀውስ በተነሳ ችግር ውስጥ በነበረችበት ጊዜ መታወጁ ነው።የኢንድራ ጋንዲም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚከተሉት አበይት ይዘቶች ነበሩት።
- ነፃው ፕሬስ ላይ እቀባ /ሲንሰርሺፕ ማድረግ
- የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን ማሰር
- የክልሎችና የፓርላም ምርጫዎች ወደፊት ላልተወሰነ ጊዜ ማሸጋገር
- አዳዲስ ህጎች ማውጣት
- መሃይምነትንና ድህነትን ለመዋጋት ብሎም የሃገሪቱን የእርሻና የኢንዱስትሪ ምርት ለማሳደግ ባለ ሃያ ነጥብ ፕሮግራም መንደፍ
- ሀገሪቱን በአዋጅ መምራት
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ህንድ ውስጣ ገደብ የለሽ ነፃ ፕሬስ ነበረ፣ፍርድ ቤት ከፖለቲካ ተፅእኖ ነፃ ነበር፣ታዋቂ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ቀርቶ ማንም ሰው ከህግ ውጪ አይታሰርም አይንገላታም ነበር፣በሁሉም ደረጃ ያሉ የክፍላተ ሃገራትና የማእከላዊ መንግስት የፓርላማና ሌሎች ምርጫዎች ጊዜያቸውን ጠብቀው ትክክለኛና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ይካሄዱ ነበር፣ከህግ አውጪው ክፍል ውጪ ህጎች በዘፈቀደ አይወጡም ነበርና በአስቸኳዩ አዋጅ ምክንያት ኢንድራ ጋንዲ ከፍተኛ ትችትና ተቃውሞ የደረሰባት አዋጁ በፊት የነበሩ መብቶችን በማገዱ ነበር።
ወደሀገራችን ሁኔታ ስንመለሰ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የሆኑት አቶ ጌታቸው አምባዬ እንደገለፁት በህገ መንግስቱ አንቀፅ 93 መሰረት ህገ መንግስቱ አደጋ ላይ ሲወድቅ የሚለውን በመጥቀስ በተለመደው የህግ ማስከበር ስርአት የተፈጠረውን አደጋ ለመከላከልና ሁኔታውን ለመቆጣጠር አዋጁ መውጣቱንና ይህም ህገ መንግስታዊ መሰረት እንዳለው በመግለፅ ጀምረዋል።ጠቅላይ አቃቤ ህጉ እንደገለፁት በንኡስ እንቀፅ ሁለት መሰረት ዝርዝር ስልጣኖች ያሉት አስፈፃሚ ኮማንድ ፖስት መፈጠሩን ሲያስረዱ አያይዘውም የገለፁት የአዋጁ ይዘት በሚከተለው ሊጠቃለል ይችላል።
ወንጀሎች
- ማንኛውም ሁከት ብጥብጥና በህዝቦች መሃከል መጠራጠርና መቃቃርን የሚፈጥር ይፋዊ ይሁን የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግ።
- ፅሁፍ ማዘጋጀት ማተምና ማሰራጨት ትእይንት ማሳየት በምልክት መግለፅ ወይም መልእክትን በማናቸውም መንገድ ለህዝብ ይፋ ማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተግባራዊ በሚሆንባቸውና ለህዝብ ይፋ በተደረጉ ቦታዎች ላይ እነዚህን መፈፀም ።
የኮማንድ ፖስቱ ስልጣን
- ማናቸውንም የመገናኛ ዘዴዎች እንዲዘጉ ማድረግ መቻል።
- ስብሰባና ሰልፍ የማድረግ ጉዳዮችን ሊያግድ ይችላል መደራጀትንና በቡድን መንቀሳቀስን ሊከለክል የሚችልበት ሁኔታም በአዋጅ ውስጥ ተቀምጧል
- የህዝብን ሰላምና ፅጥታ በማደፍረስ ላይ ተግባር ላይ ተሳትፏል ተብሎ በሚጠረጠር ማንኛውም ሰው አለፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝ መቻሉ።
- ወንጀል የተፈፀመባቸው ወይም ሊፈፀምባቸው የሚችሉ እቃዎችን ለመያዝ ሲባል ማናቸውንም ቤት የብርበራ ትእዛዝ ሳይወጣ መበርበር ማንንም ሰው ማስቆምና መፈተሽ መቻሉ
- የሰአት እላፊ ተፈፃሚ የሚሆንበትን ቦታ ይወስናል ተግባሪዊ የሚሆንባቸውን ቦታዎች ተግባራዊ ያደርጋል
አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚያስከትላቸው ቅጣቶች
አቃቤ ህጉ አዋጁ ተግባራዊ የሚሆንበት ጊዜ ስድስት ወር እንደሆነና እንደሁኔታው ሊያጥር ወይም ሊረዝም መቻሉን ገልፀው ማንኛውም ሰው ማንኛውም ዜጋ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቀመጡ እርምጃዎችን የማክበርና የመተባበር ግዴታውን ካልተወጣ የሚከተሉት ቅጣቶች እንደሚከተሉ ገልፀዋል።
- የኮማንድ ፖስቱን ወይም የህግ አስፈፃሚዎችን አለመተባበረ እስከ ሶስት አመት የእስር ቅጣት እንደሚያስከትል
- አዋጁን በቀጥታ ተላልፎ መገኘት እስከ ስድስት ወር እስር የሚያስቀጣ መሆኑን አስረድተዋል።
ከህንድ በተለየ ሁኔታ አዋጁን አነጋጋሪ ያደረገው ከህግ ውጪ ህዝብ በአደባባይ በጥይት እየተቆላ ባለበት ሁኔታ ልክ እስካሁን የተደረገው የህዝብ ጭፍጨፋ በህገ መንግስቱና በፍርድ ቤት ትእዛዝ መሰረት እንደተከናወነ በማስመሰል ካሁን በሁዋላ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጇል መባሉ ነው።ህወሀት የሚሊቴሪ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነቱን ያሰፈነው ከፋፍለህ ግዛ የሚባለውን የአስተዳደር ዘይቤ እየተጠቀመ በመሁኑ ነው እይተባለ፣ ለማስረጃም የመንግስት የኮሚኒኬሽን ሚንስትር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ራሳቸው እሳትና ጭድ እያሉ የሃገሪቱን ሁለት አውራ ብሄረሰቦች የሚያፋጅ ሃሳብ በአደባባይ እየተናገሩ ማንኛውም ሁከት ብጥብጥና በህዝቦች መሃከል መጠራጠርና መቃቃርን የሚፈጥር ይፋዊ ይሁን የድብቅ ቅስቀሳ ማድረግን ወንጀል ነው ብሎ እራሱ መንግስት አዋጅ ሲያወጣ እነ አቶ ጌታቸው ምን ቅጣት ደረሰባቸው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።እንደምንሰማው ከሆነ ኦህዴድ እራሱ ሌላውን በሄረሰብ ከኦሮሞ ብሄርሰብ ማጣላቱን ተያይዞታል እየተባለ ነው።
ፅሁፍ ማዘጋጀት ማተምና ማሰራጨት ትእይንት ማሳየት በምልክት መግለፅ ወይም መልእክትን በማናቸውም መንገድ ለህዝብ ይፋ ማድረግ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ካሁን በሁዋላ የተከለከለ ነው ማለት እስካሁንስ መቼ ተፈቅዶና ያስብላል።በተለያዩ የኦሮምያና የአማራ አካባቢዎች ኢትዮጵያውያን የተተኮሰባቸው በዚሁ አይደለም እንዴ።እስካሁን የማይከለከል ተግባር ከነበረ ይህን ተላልፈው የግድያ፣የድብደባና ፣የማሰር ወንጀል የፈፀሙ መች ለፍርድ ቀረቡ ብሎ መጠየቅም አግባብ አለው።ይህ ማለት ግን አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምንም ትርጉም የሌለው ነው ማለት ሳይሆን የሚከተሉት እንደምታዎችን አሉት።
- ሆነ ብሎ የህዝብን ጥያቄ ጠምዝዞ መረዳት ህወሀት/ ኢህአድግ እራሱ ያወጣውን ህገ መንግስት አያከብርም ሲባል የህገ መንግስት ጥሰቱ የሚጀምረው ገዢው ፓርቲ ከህጉ ውጪ ፓርላማውን መቶ በመቶ መቆጣጠሩ እንጂ ግድያዎችን ፓርላማው በመጀመሪያ ያፅድቅ ወይንም አያፅድቅ አይደለም። ፓርላማውና ህወሀት/ ኢህአዴግ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው። መልሱ ያለው የፓርላምውን ህዝባዊነት ማሳየት ላይ ነው። ማንኛውንም የመንግስት እርምጃ የፓርቲው የአንድ ሳንቲም ገፅታ በሆነው ፓርላማ በመፅደቁ ወይም አለመፅደቁ ለህዝብ ብዙ ትርጉም የለውም።ህዝብ እያለ ያለው ህወሀት እጁን ይሰበስብ ፣አንድ ሰው አንድ ድምፅ የሚለው ዲሞክራሲያዊ መርህ ይተግበር ፣የህግ የበላይነት ይረጋገጥ ሲሆን የዚህ ማሳያው በመጀመርያ አሁን ያለው ፓርላማ የኢትዮጲያውያንን የአመለካከት ብዝሃነት የማያነፀባርቅ መሆኑን መዋጥና የህዝብ የተለያዩ አመለካከቶች ውክልና ያለው ፓርላማ እንዲኖር በአስቸኳይ መንቀሳቀስ ነው። የጀርመኗ ወሮ መርክል ከፓርላማው ፊት ለፊት ቀርበው መነጋገር እምቢተኛ የሆኑት በዚሁ ጉዳይ ነው።
- ሃላፊነትን ማውረድ ባይቻል ተጠያቂነትን ማስፋት.እየተመለከትን ያለነው እራሳቸውን ከህግ በላይ ያደረጉ የህወሀት ባለስልጣናት ሁሉን እንደፈለጉ ካቦኩና ጋግረው ካሳረሩ በህዋላ የራሳችሁን ህገ መንግስት አታከበሩም የሚለው በጆሯቸው እልፍ ሲል ታድያ ምን ችግር አለው ፓርላማው የኛ ሎሌ አይደል እንዴ የሚል ተራ ብልጠት ውስጥ ሲገቡ ነው።ህሳቤው የተሰራ ወንጀልን ለማስተሰረይ ፕርላማውን እንደ ፀበል ለመጠቀም የተደረገ ሙከራ ነው። ሀምሳ ሎሚ ለሃምሳ ሰው የሚል አባባል አለ ግን ሃምሳ ወንጀል ለሃምሳ ሰው የሚለውን እስካሁን አልሰማሁም።ፓርላማው የህዝብ መጠቃት ጥቃቱ የሆነ ፣መንግስት የወሰደውን የሃይል እርምጃ ህጋዊነት የሚሞግት ፣መንግስትን ጥፋተኛ ሆኖ ካገኘ ጠቅላይ ሚንስትሩንና ካቢኔውን ሊሽርና ለፍርድ ሊያቀርብ የሚችል የአመለካከት ብዝሀነት ያለው ጥርሳማ የሀገሪቱ ከፍተኛ ስልጣን መሆኑ ሳይረጋገጥ ዝም ብሎ እጅ ማጨብጨብ ለተፈፀመው የህዝብ ፍጅት ተጠያቂነት እነደእሳት እራት ዘሎ በመግባት እራሱን አየተሰራ ላለው ወንጀል ተጠያቂ አድርጓል።በሃገሪቱ በተለያዩ ቦታዎችም የግድያ ትእዛዞችን ያስተላለፉት ገዳዮች አሁን ሙሉ የፓርላማውን አባላት ጭምር ለወንጀሉ ተጠያቂ በማድረጋቸው የሰሩትና የሚጠየቁበትን የወንጀል መጠን አይቀንሰውም ከተጠያቂነትም ሊያመልጡ እይችሉም።ለመሆኑ ያ ሁሉ እልቂት ህዝብ ላይ ሲወርድ ፓርላማው የት ነበረ ።ከራሱ ህዝብስ የበለጠ ሌላ አስቸኳይ ስብሰባ የሚያስጠራ ጉዳይ አለውን።
- የህዝብን ጥያቄ በሀይል ለመጨፍለቅ ከመሞከር አለመታቀብ አሁንም እየተመለከትን ያለነው እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ አመፅ ልዩ ኮማንድ ፖስት በማቋቋም በሃይል ለመጨፍለቅ የሚደረግ ሙከራ ነው። ግድያውን፣ድብደባውንና እስራቱን እየፈፀመ ያለወ አግአዚ የሚባለው ሰራዊት ይሁን፣ሌላ ሚሊሽያ ሃይል ወይም ምናምን ፖስት ለህዝብ ግድያ ግድያ ነው።ጭፍጨፋውን እንዴትና በየትኛው ሃይል እንፈፅመው የሚለው የህወሀት ፊታውራሪዎቹ የውስጥ አሰራር ነበር።ያን ህዝብ አወቀው አላወቀው መንገድ ላይ ፊት ለፊት የሚገናኙት እስናይፐር ተኳሽና ዱላ ያልያዘ ሰላማዊ ተቃዋሚ ህዝብ ናቸው።የህዝብ አመፁን መፍታት የሚቻለው ሰላማዊውን የህዝብ ጥያቄ በፍጥነት በመረዳት ፈጣን መልስ በመስጠት ነው።ህዝብም ከፕሮፌሰር መስፍን እስከ ጄኔራል ፃድቃን ሁሉም የየበኩሉን አስተያየት እየሰጠ ነው።እኔም በበኩሌ ‘Rock Bottom Benchmark for the comprehensive Renewal of TPLF/EPRDF’ የምትል መጣጥፍ ወርውሬ ነበር።የኔ ሃሳብ እንደፕሮፌሰር መስፍን መሆን ያለበት ብዬ ሳይሆን ከህወሀት /ኢህአዴግ ባህሪ አንፃር ጥልቅ ተሃድሶ አደርጋለሁ ካለ ይህ ጥልቅ ተሃድሶ ቢያንስ ቢያንስ ሊያመጣ የሚገባው ለውጥ ብዬ የምጠበቀውን ነበር። ምን እናድርግ ከተባልኩ ግን የፕሮፌሰር መስፍን መፍትሄ ፍቱን መድሃኒት ይሆናል።ግን ህወሀት /ኢህአዴግ ያን ያህል ይሄዳል ብዬ አልጠብቅም።ከዚህ ሁሉ የህዝብ እልቂትም በሁዋላ የህዝብን ጥያቄ በሃይል መጨፍለቅ ይቻላል ብዬ አላምንም።
- አምቢተኛ የመከላከያና የፖሊስ ሃይላትንና ሌሎችን መክሰሻ እስካሁን ከተለያዩ የዜና ምንጮች የምንሰማው በመከላከያና በፖሊስ ሰራዊትና በአንዳንድ መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ ያሉ በህዝብ ላይ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በመቃወም ስርአቱን አናገለግልም እያሉ መሆናቸው እየተደመጠ ነው።የነዚህ ሰዎች አቋም በነፃ ፍርድ ቤት ቢታይ የሚተላለፉት ህግ አለ ተብሎ ሊቀጡ አይችሉም። ህዝብ ላይ መተኮስ ህገ መንግስታዊ ሊሆን ስለማይችል። አሁን ግን በዚህ ጊዜያዌ አዋጅ የአሰራሩ ተባባሪ አልሆኑም ወይንም አሰራሩን ተቃውመዋል በሚል በየትኛውም ፍርድ ቤት እየቀረቡ ከሶስት እስከ ስድስት አመት ሊፈረድባቸው ይችላል። ከዚህ መለስ የህዝብ እምቢተኝነት አፈናው ሃይል የሚፈልገውን ለማድረግ እስካሁን ያጋጠሙትን ችግሮች ከግንዛቤ በማስገባት በራሱ እምነት በልዩ ልዩ የመንግስት መስርያ ቤቶች የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠርና በይበልጥ ለመንቀሳቀስ የሚያስችሉትን ድንጋጌዎች ለማካተት ያስችለዋል።
- ምናባዊ የፍርሃት አጥር ህዝብ ላይ መጫን የአምባገነን መንግስታት ዋና መሰረት ህዝብን ማስፈራራትና ያቺንም የፍርሃት ድባብ በመጠቀም ህዝብ መንግስትን እንዳይጠይቅ ፣ሃሳቡን እንዳይገልፅ፣የመብት ጥያቄ እንዳያነሳና መንግስት እየቸረቸረ የሚሰጠውን መብት ብቻ እሺ እርሶን ሺህ አመት ያኑርዎ እያለ እንዲቀመጥ ማድረግ ነው። የአዋጁም አላማ ህዝብን አስፈራርቶ ማቆም ነው።አሁን በአብዛኛው የኦሮምያ የአማራና አንዳንድ የደቡብ ኢትዮጰያ አካባቢዎች የምንመለከተው የነበረው የፍርሃት ድባብ መሰበሩን ነው።አቶ ሃይለማርያም ለመከላከያው የሰጡት የነፃ እርምጃ ሙሉ ስልጣንም ተቃውሞውን አልገታውም።በዚህ ሁኔታ ከዚህ በፊት ከነበረው የተለየ ምንም አዲስ ነገር የማይጨምር አዋጅ ማውጣት ምናልባት ተጨማሪ የስነ ልቦና ጫና በህዝብ ላይ በመፍጠር ምናባዊ የሆነ አዲስ የፍርሃት አጥር በህዝብ ስነ ልቦና ላይ ለመጫን የታሰበ ይመስላል።ከዚህ በፊት በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ ሲወሰድ ያየነው ከፍተኛው እርምጃ ግድያ ነበር አሁን ደግሞ አዋጁ ከፍተኛው ቅጣት የስድስት አመት እስራት ነው ብሎናል። እስር አሉን አቶ አቃቤ ህግ ከዛስ በሁዋላ የሚመጣው የእስር ቤት ቃጠሎ ጌታው። ስድስቱ አመት ቃጠሎውን ህሳቤ ያደረገ ነው እንበል።
- የሰው ህይወት መጥፋትና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለአለም አቀፍ ማህበሩ እንደምታው. የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ በራሱ የሰላምና የመረጋጋት ችግር እንዳለና ለኢንቨስትመንት አመቺ ሁኔታ አለመኖሩን ያሳያል።ያም ሆነ ይህ ለኢትዮጰያውያን ከኢትዮጲያውያን ህይወት የበለጠ ምንም ነገር ጭራሽ እይኖርም።የሰው ህይወት መጥፋት አሁንም ችግሩን በሃይል ለመፍታት የሚኬደው አካሄድ ህዝቡን የበለጠ ያነሳሳዋል መንግስትንም በአለም አቀፉ ማህበረሰብ ያለውን ተቀባይነት ይሸረሽረዋል።
በቅርቡ በኢሬችው በአልና በሌሎች የሃገራችን አካባቢዎች በግፍ ለተገደሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጠበቃ ሆነን መቆም ይኖርብናል። የሞቱት ለግል ጥቅማቸው ሳይሆን ለህዝብ ብለው መሆኑን ልብ እንበል።ህዝባዊ አመፅ በሃይል ሊቆም እንደማይችል ልብ ያለው ልብ ይላል።
ኢትዮጲያ ለዘላለም ትኑር
መላኩ ወልደስላሴ
ከአትላንታ
No comments:
Post a Comment