Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, October 8, 2016

መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ !! ከአርበኛ ኤፍሬም ማዴቦ !!

መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ !!
ከአርበኛ ኤፍሬም ማዴቦ !!
ስድስተኛ፤ ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍል አብራኝ የተማረች ሰላማዊት ነገደ የምትባል ቆንጆ ልጅ ነበረች። ሰላማዊት ስትስቅ ከሩቅ የሚታይ ስርጉድ፤ የደስ ደስና አንዴ ካዩት አመት የሚናፍቅ ፈገግታ ያላት ዉብ ልጅ ናት። ሰላማዊትን እንኳን ያያት ያገኛትም አይጠግባትም። ሰላማዊት ሁለመናዋ ቆንጆ ሆኖ ጸባይዋ ግን . . . አቤት “ያንተ ያለህ” የሚያሰኝ ነዉ። ሰላማዊት “ቂጧ” አንድ ቦታ አርፎ የማይቀመጥ፤ ከአዋቂዉም፤ ከህጻኑም፤ ከአስተማሪዉም ከተማሪዉም ልክ እንደ እሳት እራት ካገኘችዉ ጋር ሁሉ የምትላተም በጥባጭ ልጅ ነበረች። ብቻ ምን አለፋችሁ ሰላማዊት “ከፈሷ” ጋር የተጣላች ደብረ በጥብጥ ልጅ ነበረች። ት/ቤት ዉስጥ በቀን ቢያንስ ሁለቴ ወይም ሶስቴ እየተከሰሰች ዳይረክተራችን ቢሮ መሄዷ አይቀርም። እኔም እንደ ሰላማዊት ዕብድ ባልሆንም ዳይረክተራችንን በየቀኑ ከሚጎበኙ ተማሪዎች ዉስጥ አንዱ ሰለነበርኩ ከሰላማዊት ጋር በየቀኑ እንገናኝ ነበር። የምንማርበት ካቶሊክ ሚሺን ት/ቤት ሰላማዊትንና እኔን የታገሰን ሁለታችንም በትምህርት ጎበዞች ስለነበርን ብቻ ነዉ እንጂ . . . . እንደ ጠባያችንማ ቢሆን ሳምንትም አንቆይ። ሰላማዊት የሰፈሬ ልጅ ስለነበረች ቤተሰቦቼም ያዉቋታል። አባቴ የትምህርት ጉብዝናዋን ሰለሚያዉቅ ይወዳታል፤ እናቴ ግን እቺ “ሰላም የሌላት” ልጅ ወይ ስሟን አለዚያም ጸባይዋን ካልቀየረች እንኳን ቤቴ ልትገባ አጥሬን እንዳታይብኝ ባይ ነበረች። አዎ ሰላማዊት በእናቶቻችን አነጋገር “መጥኔ ይስጥሽ” የምታስብል በጥባጭ ልጅ ነበርች። የሰላማዊት ወላጆች የልጃቸዉ የወደፊት ይታያቸዉ አይታያቸዉ ለግዜዉ የሚታወቅ ነገር የለም – ለልጃቸዉ ያወጡላት ስም ግን የ”መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ” ትክክለኛ ምሳሌ ነዉ።
አይዟችሁ ዛሬ የማወራችሁ ስለ ልጀነት ጓደኛዬ ስለ ሰላማዊት አይደለም። ደሞ ባወራስ! ሰላማዊት በጥባጭ እንጂ ሌባ፤ “ደብረ በጥብጥ” እንጂ “አገር በጥብጥ” አይደለችም። ለሁሉም ዛሬ የማወራችሁ በኮሚቴ አገር ስለሚመሩ፤ በኮሚቴ አገር ስለሚዘርፉ፤ በኮሚቴ ስለሚዋሹና በኮሚቴ ወገኖቻችንን ስለሚገድሉ ሰዎች ነዉ። እነዚህ የኮሚቴ ሰዎች ሁሉም መልካም ስም የተሸከሙ ነገር ግን ዉስጣቸዉም ዉጫቸዉም አስቀያሚ የሆኑ ሰዎች ናቸዉ። አንዳንዶቹን ስማቸዉን እየጠቀስኩ ብጽፍ ደስ ይለኝ ነበር ግን . . . ይቅርብኝ! ኧረ ይቅርብኝ ምነዉ እቴ!! ይልቅ እነዚህ አስቀያሚ ሰዎች በአምሳያቸዉ ስለፈጠሯቸዉ “ስማቸዉ መልካም” ስራቸዉ ግን አስቀያሚ ስለሆኑ ድርጅቶች አንድ. . . ሁለት ልበላችሁ። ለመሆኑ “አገር መከላከያ ሚኒስቴር” እየተባለ ህዝብን ስለሚያጠቃዉ፤ “ዕምባ ጠባቂ” እየተባለ ድፍን አበሻን ስለሚያስለቅሰዉ፤ “ደህንነት” መ/ቤት እየተባለ በዜጎች ላይ ሰቆቃ ስለሚፈጽመዉና “ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሺን” እየተባለ ህዝብ በየአደባባዩ በአልሞ ተኳሾች ሲገደልና በጅምላ ሲታሰር ኢትዮጵያ ዉስጥ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃና አያያዝ ተሻሽሏል እያለ ስለሚያዉጀዉ በድን መስሪያ ቤት ታዉቁ ኖሯል?
ካላወቃችሁ እስኪ በመጀመሪያ ይህንን “ኢሰመኮ” የሚባል ድርጅት ላስተዋዉቃችሁ። ኢሰመኮ ማለት ሰዉ ሲገደል ትንኝም አልተገደለም፤ ሰዉ ሲታሰር የታሰረ የለም፤ ሰቆቃ ሲፈጸም ኧረ በፍጹም እያለ የሚሸመጥጥ ወያኔ ሰራሽ ድርጅት ነዉ። ይህ የ”ኢሰመኮ” ማንም ሰዉ የሚያዉቀዉ የመዝገበ ቃላት ትርጉሙ ነዉ። ዬኔ ችግር ትርጉሙ ላይ አይደለም። ለመሆኑ “ኢሰመኮ” የሰሜን ኮሪያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ነዉ ወይስ የኢትዮጵያ? በመብት ረገጣ አንደኛና ሁለተኛ ናቸዉና – የሁለቱም ሊሆን ይችላል . . . የማን መሆኑም ብዙ አያሳስበኝም ። ግን ህወሓቶች ኢሰመኮ እያሉ በጥሩ ድርጅት ስም ከሚረግጡን ለምን አንዱኑ “መብት መርገጥ ህጋዊ ነዉ” እያሉ እዉነቱን እየነገሩን አይረግጡንም? እየቀለድኩ እንዳይመስላችሁ! የምሬን ነዉ። ኢሰመኮ ማለትኮ ኦሮሚያ ዉስጥ ከ500 በላይ ሰላማዊ ዜጎች በአግዓዚ ሲጨፈጨፉና ከአስር ሺዎች በላይ ሲታሰሩ – ጸጥታ አስከባሪዎች የወሰዱት እርምጃ ህጋዊ ነዉ ያለ ግዑዝ ድርጅት ነዉ። አዎ! ግዑዝ ድርጅት! እስቲ አሁን ኢትዮጵያ “ቅርጫ ቦርድ” ወይም የ “አገር ዉስጥ አጥቂ ሚኔስቴር” ነዉ እንጂ “ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሺን” የሚባል ድርጅት ምን ያደርግላታል? ይገርማል . . . እየገደሉ ማዘን!
በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴና በደርግ ዘመነ መንግስት የመከላከያ ሰራዊት ትልቁ ስራ አገርን ከጠላት መከላከል ነበር- ለዚህም ነበር መስሪያ ቤቱ የ”አገር መከላከያ ሚኒስቴር” እየተባለ የሚጠራዉ። የዛሬዉ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “ቀኃስ” ዩኒቨርሲቲ እየተባለ በሚጠራበት ወቅት ወይም የዛሬዎቹ ነብሰ ገዳዮች የዚህ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በነበሩበት ግዜ ዩኒፎርም የለበሰ ምንም አይነት ወታደር የዩኒቨርሲቲዉን መግቢያ በር አልፎ ወደ ገቢዉ አይገባም ነበር። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ በየክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ዉስጥ ተማሪዉን፤ ወታደሩን፤ አስተማሪዉንና ነጭ ለባሹን መለየት አስቸጋሪ ነዉ። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጊቢያቸዉ ዉስጥ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ እዚያዉ ግቢያቸዉ ዉስጥ ገብቶ የሚገድላቸዉ ወታደሩ ነዉ። ኦሮሚያ ዉስጥ ዘጠኝ ወር ሙሉ ባዶ እጃቸዉን “መብታችን ይከበር” እያሉ የሚጮሁ ወጣቶችን የገደለዉ ወታደሩ ነዉ። ዛሬ ጎንደር፤ ጎጃም፤ ኮንሶና አጋዴን ዉስጥ ሰላማዊ ዜጎችን ያለ ርህራሄ የሚጨፈጭፈዉ አገርንና ህዝብን የመጠበቅ ህገ መንግስታዊ አደራ የተሸከመዉ ወታደሩ ነዉ። የሚገርመዉ ባለፈዉ ሚያዚያ ወር ከባዕድ አገር ድንበር ተሻግረዉ የመጡ መሳሪያ አንጋቾች ጋምቤላ ዉስጥ ወገኖቻችንን ጨፍጭፈዉ በሰላም ወደ መጡበት ሲመለሱ ዝም ብሎ እንዲመለከት የተደረገዉም ይሄዉ የኢትዮጵያ ተብዬዉ ወታደር ነዉ። ለመሆኑ ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ ወታደር የማን ወታደር ነዉ? የኢትዮጵያ ወይስ የህወሓት? የአንድ ፓርቲ ጥቅምና ፍላጎት አስከባሪ ወይስ የአገር ዳር ድንበር አስከባሪ? መልሱን የራሱን ወገን ለሚጨፈጭፈዉ ወታደር እተዋለሁ። ወታደሩን ያቀፈዉን ትልቅ አገራዊ ተቋም ግን በቀድሞ ስሙ የ”አገር መከላከያ” ሚኒስቴር ብዬ መጥራት ስለሚቀፈኝ . . . . ”አገር ዉስጥ አጥቂ” ሚኒስቴር ብዬ ሰይሜዋለሁ። የሚስማማ ካለ አሜን ይበል። በኔ በኩል አሜን!
መቼም ኢትዮጵያ ዉስጥ በህወሓት ዘመን ተፈጥሮ የኢትዮጵያን ህዝብ የማያጠቃ ተቋም አለ ለማለት ያዳግታል። መከላከያዉ አገርን ከጠላት መከላከል ሲገባዉ በየመኖሪያ ሰፈሩ እየገባ ህዝብን ያጠቃል። ፍርድ ቤቶች ለተበደለና ለተገፋ ፍርድ መስጠት ሲገባቸዉ ይባስ ብለዉ የተበደለዉንና የተገፋዉን ያጠቃሉ። ዘንድሮማ ምን የማንሰማዉ ጉድ አለ- እስር ቤቱም “ማረሚያ ቤት” መሆኑ ቀርቶ ማጥቂያ ቤት ሆነኮ! ፋሺስታዊዉ የወያኔ ስርዐት ቂሊንጦ እስር ቤት ላይ የፈጸመዉ ናዚ መሰል አረመኔያዊ ድርጊት ስርዐቱ እያሰበ የሚዉለዉና የሚያድረዉ የኢትዮጵያን ህዝብ በብዛት የሚገድልበትን ዘዴ እየፈለገ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። ወያኔ ቂሊንጦ እስር ቤት ዉስጥ የፈጸመዉ ወንጀል አንዴ ተፈጽሞ ያበቃ ወንጀል ሳይሆን ተከታታይ ወንጀል ነዉ። የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆቹ የታሰሩበት እስር ቤት በእሳት ተቃጥሎ ማን ሞተ ማን ተረፈ፤ እስር ቤቱ እንዴት ተቃጠለ ለምን ተቃጠለ ምንም ነገር ሳይነገረው ሳምንት ቆየ። ከሳምንት በኋላ አባትና እናት ልጃቸዉ በህይወት እያለ “ልጃችሁ” ሞቷልና ቅበሩ ተብለዉ ስሙን እንኳን የማያዉቁትን የሌላ ሰዉ ልጅ “ልጃችን” ብለዉ ቀበሩ። ሳጥን ከፍተሽ የልጅሽን ሬሳ ካየሽ ድራሽሽ ይጠፋል የተባለች እናት ሌሊት ላይ አላስችል ብሏት መቃብር ቆፍራ ቀን የቀበረችዉን የልጇን አስከሬን ስትመለከት ልጇ የሞተዉ በእሳት ተቃጥሎ ሳይሆን ደረቱን በጥይት ተደብድቦ ነዉ። እነዚህን የሰዉ ልጅ አዕምሮ በፍጹም ሊቀበለዉ የማይችላቸዉን አረመኔያዊ ወንጀሎች የፈጸሙት የአገራችን ክርስትና መሰረት በሆነችዉና የ“ጽላተ ሙሴ” ማረፊያ ናት እየተባለ በሚነገርላት ትግራይ ዉስጥ የተወለዱ ሰዎች መሆናቸዉን ስናዉቅ . . . . እራሳችንን በሁለት እጃችን ይዘን “እግዚኦ መሀረነ ክርስቶስ” ከማለት ዉጭ ሌላማ ምን የሚባል ነገር አለ?
አንድ ሰሞን የአረብ አገር መሪዎች ተሰበሰቡና የ”እርሻ ቦርድ” እናቋቁም ብለዉ ዉይይት ጀመሩ። በዉይይቱ መሀል ግራ የገባቸዉ የኩዌቱ መሪ ተነሱና እኛ የሚያመርት መሬት የለንም “እርሻ ቦርድ” ምን ያደርግልናል ብለዉ ገና ንግግራቸዉን ሳይጨርሱ የሳዑዲዉ ንጉስ ቱግ ብለዉ ተነሱና . . . አቦ ቁጭ በል! ኢትዮጵያ እንኳን የገንዘብ ሚኒስቴር አላት ብለዉ አዳራሹን በሳቅ ሞሉት። እኚህ ንጉስ አልሰሙ ይሆናል እንጂ ዛሬ ኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድም አላት። እግዜር ያሳያችሁ ሳሞራ የኑስንና አባ ዱላ ገመዳን የመሳሰሉ ቅልብ በሬዎች ባሉበት አገር ዉስጥ “ቅርጫ ቦርድ” እንጂ “ምርጫ ቦርድ” ምን ያደርጋል? ደግሞስ የምርጫ ቦርድ ስራ የድምጽ መስጫ ሳጥኖችን ሰብስቦ ድምጽ እየደመሩ አንድን ፓርቲ በየአምስት አመቱ አሸናፊ ማድረግ ከሆነ እንኳን “ምርጫ ቦርድ” ድምጽ መስጫ ሳጥንስ የልማት ግዜያችንን ከማባከን ዉጭ ምን ያደርግልናል? የምርጫ ቦርድ ስራ ፍትሀዊ ምርጫ ማዘጋጀትና አገራችን ዉስጥ የመድበለ ፓርቲ ስርዐት እንዲለመልም ማድረግ ነዉ። ምርጫ ቦርድ አሁን እየሰራ ያለዉ ግን ህወሓት ያጎበጣቸዉን ፓርቲዎች እየገደለ መቅበርና ህዝብ በምርጫ የሚሰጠዉን ድምጽ እየደመረ ለወያኔ/ኢሀዴግ መስጠት ነዉ። አዎ ምርጫ ቦርድ ድምር ይወዳል፤ ደግሞም ደምሮ ደምሮ መቶ ካልሞላለት ደስ አይለዉም። ወይ ጉድ “መቶ” ሲባል አንዲት ቀልድ ብጤ ትዝ አለችኝ። ሂሳብ እየወደቀ አባቱ ሁሌ የሚጮሁበት ልጅ አንዴ ሂሳብ ተፈትኖ መቶ አገኘና አባቱጋ እየሮጠ ሄዶ . . . አባዬ . . . አባዬ ሂሳብ መቶ አገኘሁ ብሎ ይነግራቸዋል። ጆሯቸዉን ማመን ያቃታቸዉ አባቱ . . . ዘንድሮ “ምርጫ ቦርድ” ፈተናም ማረም ጀመረ እንዴ ብለዉ ሚስታቸዉን አሳቋቸዉ።
ሌላዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ስሙና ስራዉ በፍጹም የማይገናኝ መስሪያ ቤት የአገር ዉስጥ ደህንነት መ/ቤት ነዉ። የዚህ መ/ቤት ስራ የኢትዮጵያን ህዝብ ደህንነት መጠበቅና ጸረ ኢትዮጵያ ሴራዎችን ተከታትሎ ማምከን ነዉ። የወያኔዉ ደህንነት መስሪያ ቤት ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ደህንነት ጉዳዩ አይደለም። የሱ ስራ ህዝብን መሰለልና የህዝብን ልጆች እያነቁ መግደል ነዉ። አዎ! የኢትዮጵያን ህዝብ መሰለል የወያኔ ደህንነት መ/ቤት ዋና ስራ ነዉ . . . . ደሞ አቤት የጆሮ ጠቢዉ ብዛት! ኢትዮጵያ ዉስጥ ህዝቡ ጆሮ ጠቢዉን እየፈራ እንኳን ከጓደኛዉ ከራሱ ጋር ማዉራት ካቆመ ሰነበተኮ! ለመሆኑ በወያኔዉ ደህንነት መ/ቤትና በኢትዮቴሌኮም መካከል ምንም ልዩነት እንደሌላ ታዉቁ ኖሯል? የደህንነት መ/ቤት ስራዬ ብሎ ይሰልላል፤ ኢትዮቴሌኮም ስራዉን ትቶ ይሰልላል . . . ሁለቱም ሰላዮች ናቸዉ። ኬንያ ቴሌኮም የኬንያ ገበሬ የገበያ ዋጋንና የአየር ንብረትን በእጅ ስልኩ መከታል እንዲችል ባደረገበት ዘመን ኢትዮቴሌኮም ግን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እያወጣ በአገር ዉስጥና በዉጭ አገሮች የራሱን ዜጎች ይሰልላል። የኬንያ ቴሌኮም ዉጤታማነት የሚለካዉ ለምን ያክል ኬንያዊ ዘመናዊ የስልክ አገልግሎት ሰጠ ተበሎ ነዉ። የኢትዮቴሌኮም “ልማታዊነት” የሚለካዉ እየሰለለ ቂሊንጦ በሚልካቸዉ ዜጎች ብዛት ነዉ። ለዚህ ይመስለኛል ዶ/ር ደብረ ጽዮን ተገምግመዉም አያዉቁም ይባላልኮ! ማን አፍ አዉጥቶ ይገምግማቸዉ . . . የእሳቸዉ የስለላ ዉጤት ነዋ ቂሊንጦን የሞላዉ። ደግሞስ ቂሊንጦ ቢሞላ ባይሞላ ምን ችግር አለበት፤ ካልሞላ ዶ/ር ደብረጽዮን አሉ፤ ሲሞላ ደግሞ . . . ጨካኝ ልብ፤ክብሪትና ቤንዚን አለ። የዛሬዋ ኢትዮጵያ ደግሞ የሶስቱም ችግር የለባትም . . . በተለይ የጨካኝ ልብ!
ከህወሓት ነገሮች ሁሉ የሚገርመኝ የፈለፈላቸዉ ድርጅቶች ብዛት ነዉ። እርግጠኛ ነኝ የአንዳንዶቹን ድርጅቶች ስም ድርጅቶቹን የፈጠረዉ ፓርላማም የሚያዉቅ አይመስለኝም። ዕምባ ጠባቂ፤ ይቅርታ ቦርድ፤ ሙስና ኮሚሺን ወዘተ . . . አቤት ብዛታቸዉ! “የማያድግ ልጅ ምኑ ይበዛል” ይሉ ነበር አባቶች ሲተርቱ። እስቲ እግዜር ያሳያችሁ ካልጠፋ ስም እንስራ ሙሉ ዕምባ የሚያስለቅስን ድርጅት “ዕምባ ጠባቂ” ብሎ መሰየም ምን የሚሉት ጉድ ነዉ? በስመ አብ! አንድ ሰዉ ባንክ የሚሄደዉ ገንዘብ ሊያወጣ ወይም ሊያስገባ ነዉ። ባንክ ማለት ደግሞ ወይ ገንዘብ ተቀብሎ ጠባቂ ነዉ አለዚያም አበዳሪ ነዉ። ለመሆኑ ዕምባ ጠባቂ ድርጅት ስራዉ ምንድነው? እኔ እንደሰማሁት ዕምባ ጠባቂ ድርጅት ለጉዳይ ሄዶ ሳያለቅስ የተመለሰ ሰዉ የለም። ታዲያ ምነዉ ይህንን አለስሙ የሚጠራ ድርጅት ወይ “ዕምባ ባንክ” አለዚያም “አስለቃሽ ጪስ” ብለዉ ቢጠሩት። እዉነቱን ለመናገር ይህ ድርጅት በትክክለኛ ስሙ “ዕምባ ባንክ” ፤ የስራ አመራር ቦርዱ ደግሞ “አስለቃሽ ጪስ” ተብለዉ ቢጠሩ ለአገርም ለወገንም የሚጠቅሙ ይመስለለኛል። “አስለቃሽ ጪስ” ያስለቅሳል “ዕምባ ባንክ” ዕምባ ያጠራቅማል። አትልፋ! የስም መቀያየር ዋጋ የለዉም እንዳትሉኝ! እኔ ከ“ዕምባ ጠባቂ” ሺ ግዜ “ዕምባ ባንክ” ይሻለኛል፤ ሌላ ቢቀር ዘመድ ሲሞትበት ዕምባ ጠብ ለማይለዉ ለእንደኔ አይነቱ ሰዉ ዕምባ ያበድራል።
አምላኬን የምወድ ክርስቲያን ነኝ። አዎ የአባቴን ገዳይም ቢሆን ይቅር ማለት የሚችል ልብ ያለኝ ክርስቲያን ነኝ። ይቅር ካልተባባልን የወደፊቷን ኢትዮጵያ ማየት እንደማንችልም በሚገባ የምረዳ ሰዉ ነኝ። ግን በይቅርታ ስም አገርና ህዝብ ሲበደል ማየትም መስማትም አልፈልግም። “በደላችንን ይቅር በለን እኛም የበደሉንን ይቅር እንደምንል” መለኮታዊ ትዕዛዝ ናት። እቺን መለኮታዊ ትዕዛዝ ነብሰ ገዳዮች የራሳቸዉ መጠቀሚያ ሲያደርጉ አንገቴን ደፍቼ አልመለከትም። የአገር ሽማግሌዎች፤ ቄሶችና ፓስተሮች በይቅርታ ስም የነብሰገዳዮች ተላላኪ ሲሆኑ ማቅለሽለሽ ብቻ ሳይሆን ዉስጥ አጥንቴ ድረስ እየገባ ያመኛል። በኔ እምነት ይቅርታ የሚጀምረዉ ከራስ ነዉና የህወሓት መሪዎች ስለ “ይቅርታ ቦርድ” ከማዉራታቸዉ በፊት እያንዳንዳቸዉ ቢያንስ መንፈቅ ሱባኤ ገብተዉ በየወንዙ፤ በየተራራዉና በየአደባባዩ ገድለዉ ለቀበሯቸዉ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎች ፈጣሪያቸዉንና የሟች ቤተሰቦችን ይቅርታ መጠየቅ አለባቸዉ። ይህንን ካደረጉ ብቻ ነዉ “ይቅርታ ቦርድ” የሚባለዉ እነሱ የፈጠሩት ተቋም ተቀባይነት የሚኖረዉ። ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ “ይቅርታ ቦርድ” የሚባለዉ ተቋምና ተቋሙ ዉስጥ ያሉት ፍጹም የወያኔ አሻንጉሊት የሆኑ ተላላኪ ግለሰቦች ግን ከይቅርታ ጋር የሚያገናኛቸዉ ምንም ነገር የለም። በተለይ ፓስተር ዳንኤል ገ/ስላሴን የመሳሰሉ ትዕዛዝ የምቀበለዉ ከፈጠሪዬ ብቻ ነዉ የሚሉ ነገር ግን የነብሰ ገዳዮችን ትዕዛዝ እየተቀበሉ ያለ ምንም ጥፋት የታሰሩ ሰላማዊ ዜጎችን አሳሪዎቻችሁን ይቅርታ ካልጠየቃችሁ እያሉ ሲጨቀጭቋቸዉ ስመለከት ኢትዮጵያ እዉነትም የነአቡነ ጴጥሮስና የነቄስ ጉዲና ቶምሳ አገር ናት እንዴ እያልኩ እራሴን እንድጠራጠር ያደርገኛል። ፓስተር ዳኔልን የመሳሰሉ እንኳን ለፈጠሪ ለገዛ ሂሊናቸዉም የማይገዙና ወያኔ ሂዱ ሲላቸዉ ወዴት ብለዉ የማይጠይቁ ሆዳም ግለሰቦች የቤተ ክርስቲያን “Pastor” ተብለዉ ከሚጠሩ የህወሓት “Patter” ተብለዉ ቢጠሩ የሚያምርባቸዉ ይመስለኛል። ፓስተር እስኪ ያስቡበት . . . ፈጣሪም የሚወደዉኮ ሰዉ እራሱን ሲመስልና እራሱን ሲሆን ነዉ! አሜን ነዉ ፓስተር? . . . አሜን!
ሌላዉ ህወሓት ያንን አስቀያሚ ፊቱን በዲሞክራሲ ለመሸፈን ሲል ብቻ የፈጠረዉ ተቋም ፓርላማዉ ነዉ። በአለም ዉስጥ የማያስብ፤ የማይወያይ፤ ህግ የማያወጣና ምንም አይነት ዉሳኔ የማይወስን ግዑዝ ፓርላማ ቢኖር አዲስ አበባ ዉስጥ ያለዉ የወያኔ ፓርላማ ብቻ ነዉ። ስለ ወያኔ ፓርላማማ ባላወራ ደስ ይለኛል . . . . . ደግሞስ ይህ ሲሰበሰብም ሳይሰበሰብም የሚተኛ እንቅልፋም ፓርላማ ምን የሚወራ ነገር አለዉ? እኔማ ፓርላማዉን ባሰብኩ ቁጥር ትዝ የሚለኝ አባዱላ ገመዳ ብቻ ነዉ። መቼም አባዱላ ሲወለድ ስም ያወጣሁለት እኔ ብሆን ኖሮ ከ”አባ ዱላ” “ዱላዉ” ስለሚሻለኝ “አባ”ን አስቀራት ነበር። የወያኔ ፓርላማ ተረት የሚተረትበት ቤት ነዉ ሲባል በተደጋጋሚ እሰማለሁ። በፍጹም የማልስማማበት አባባል ነዉ። ተረት የሚተርተዉኮ የሚያስብ ሰዉ ነዉ፤ የሚተረተዉም ለሚሰማ ሰዉ ነዉ። የወያኔ ፓርላማ የሚያስብም የሚሰማም ሰዉ የለበትም- ይልቅ ለእናንተ መስማት ለምትችሉት ወገኖቼ ተረት ብጤ ልንገራችሁ – ተረት አበዛሁባችሁ አይደል? አይዟችሁ! እኔ ሰለማስብ እናንተም ስለምትሰሙ ነዉ። አንዴ ኢትዮጵያ ዉስጥ ማየትና መስማት የተሳናቸዉ ሰዎች ጉዳያችን በፓርላማ ካልታየልን አሉና ጉዳያቸዉን ይዘዉ ፓርላማ ሄዱ። አራት ኪሎ ደርሰዉ መንገድ ሲያቋርጡ ያየ አንድ ባለታክሲ አንዱን ማየት የተሳነዉ አቤቱታ አቅራቢ ዬት ነዉ የምትሄዱት ብሎ ጠየቀዉ። ፓርላማ ብሎ መለለት። ለምን አለዉ? ጉዳያችንን ለፓርላማ ልናሰማ . . . እነማናችሁ እናንተ? እኛ ማየትና መስማት የተሳነን ኢትዮጵያዊያን ነን። እንዴ! የኢትዮጵያ ፓርላማ ከመቼ ጀምሮ ነዉ ማየትና መስማት የተሳናቸዉን ሰዎች ጉዳይ ማየት የጀመረዉ . . . . ፓርላማዉ እራሱ እኮ “ማየትና መስማት የተሳነዉ” ፓርላማ ነዉ ብሎ ባለ አቤቱታዉን አሳቀዉ።
ወያኔ ደርግን አሸንፎ አዲስ አበባ ሲገባ የረባ ቅያሪ ልብስ ያልነበራቸዉ እነ ስብሐት ነጋ፤ አባይ ጸሀዬ፤ መስፍን ስዩም፤ አባይ ወልዱና ጓደኞቻቸዉ ዛሬ የሚነዱት መኪና “ቤንትሊ” እና “ሮይስሮልስ” ነዉ። የሚኖሩባቸዉ የተንጣለሉ ቪላዎች ዉበትማ እንኳን በየቀኑ እላዩ ላይ ቤቱ የሚፈርስበት ደሃዉ ኢትዮጵያዊ እነሱንም ይገርማቸዋል። እነዚህ ሰዎች በገቢያቸዉ ልክ ቢኖሩ ኖሮ የሚኖሩባቸዉን ቪላዎች እንኳን ሊኖሩባቸዉ በአይናቸዉም ማየት የማይችሉ ሰዎች ናቸዉ። እነዚህ የለየላቸዉ ዘራፊዎች ከስራ መልስ . . . ስራ እንኳን የላቸዉም . . . ከወሬ መልስ ለሁለተኛ ዙር ወሬ ሲሰበሰቡ የሚጠጡትን መጠጥ ስም እንኳን እኔ እነሱም አያዉቁም። የህወሓት ስራ አመራር ኮሚቴ አባል ሆኖ አዉሮፓና አሜሪካ ቪላና የባህር ማዶ ባንክ ሂሳብ የሌለዉ ሰዉ የለም። አዲስ አበባ ዉስጥ ትላልቆቹ ህንጻዎች የሚጠሩት በወያኔ ጄኔራሎች ስም ነዉ። መሬት የሚሰጠዉ ለእነሱ ብቻ፤ አለችሎታቸዉ ብድር የሚያገኙት እነሱ ብቻ፤ ህንጻ መስራት የሚችሉትም እነሱ ብቻ ናቸዋ። እነዚህ በጣት የሚቆጠሩ የህወሐት ባለስልጣኖች ከኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ባለፉት ሀያ አምስት አመታት የዘረፉት ገንዘብ 100 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ስራ ሳይሰራ እየተኛ ቢዉል ሰላሳ አመት ይኖርበታል። እንግዲህ ይታያችሁ እነዚህ ወስላቶች አገራችንን እንደዚህ ሙልጭ አድርገዉ ከዘረፏት በኋላ ነዉ ትናንሹን ሌባ ለመቅጣት “ሙስና ኮሚሺን” የሚባል ከሌባ ሌባ እየመረጠ የሚቀጣ ድርጅት የፈጠሩት። አቶ ሃይልዬን በስኳር መላስ አልጠረጥራቸዉም ነበር፤ ግን ከ”አህያ” ጋር ዉለዉ እቺን ስኳር መላስ ተማሩ መሰለኝ እየመረጡ የሚያስሩት “ሌባ ላመሉ ዳቦ ይልሳል” አይነቱን ትናንሹን ሌባ ነዉ። እዉነቱን ለመናገር ኢትዮጵያ ዉስጥ “ሙስና ኮሚሺን” መቋቋም አልነበረበትም – ከተቋቋመም ስሙ “ሙስና ከማና” ነዉ መሆን የነበረበት፤ አማርኛ ለማይገባቸዉ ለነፕሮፌሰር ሳሞራ ደግሞ “ስርቂ እንተኮይኑ ከማና” መባል ነዉ ያለበት . . . . ኡወ ፕሮፌሰሬ ስርቂ ከማሁም!
ኢትዮጵያ ፍትህን ሳያዛባ ህዝብን በእኩልነት ያሰተዳደረ መንግስት ኖሯት አያዉቅም። ሁሉም መንግስታት ዜጎችን አላግባብ አስረዋል፤ ገርፈዋል፤ ገድለዋል። የኃይለ ስላሴ ስርዐት የኢትዮጵያን ገበሬ እንደ ዕቃ የባላባቶች ንብረት ያደረገ ፊዉዳል መንግስት ነበር። ደርግም . . . እንደ ስሙ ደብድብ፤ ርገጥ ግደል ስርዐት ነበር። ሆኖም ቅድመ ህወሓት የነበሩት መንግስታት ሌላ ቢቀር በኢትዮጵያ አንድነትና ዳር ድንበር ከባዕዳን ጋር አይዋዋሉም። ቅድመ ህወሓት መሪዎቻችን ኢትዮጵያን “አገሬ ኢትዮጵያ” ወይም “አገራችን ኢትዮጵያ” እያሉ ነበር የሚጠሯት እንጂ “እቺ አገር” እያሉ አይጸየፏትም። ዛሬ ኢትዮጵያን “እናት አገሬ ኢትዮጵያ” እያለ በአለም ዙሪያ ለኢትዮጵያና ለህዝቦቿ ጠበቃ የቆመዉ ዕድሜዉ አርባና ከአርባ በላይ የሆነዉ ኢትዮጵያዊ የአገር ፍቅርን እንደ ምግብ እየበላ ያደገዉ በቀሀስና በደርግ ዘመነ መንግስት ነዉ። በእነዚህ ሁለት ስርዐቶች ወቅት በተለይ በሀይለ ስላሴ ዘመን ኢትዮጵያዊ በየሄደበት ይከበር ነበር።
በደርግና በኃይለ ስላሴ ዘመን የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች የኢትዮጵያና የዜጎቿ ጥቅም ማስጠበቂያ ቦታዎች እንጂ የህወሓት አባላት መሰብሰቢያና የጥላቻ ዘፈን መዝፈኛ መድረኮች አልነበሩም። ኢትዮጵያዊያን በአምስትና ስድስት መቶዎች ሲገደሉና የኢትዮጵያ ህዝብ በቅዱስ ዮሐንስ ጥቁር ለብሶ ሀዘን ሲቀመጥ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ይህንን ሀዘን ይጋራሉ እንጂ ጭራሽ ሞታችንና መከራችን ያስደሰታቸዉ ይመስል የአንድን ዘር የበላይነት እያወጁ ጮቤ አይረግጡም! በዋሺንግተን ዲሲዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዉስጥ “ትግራዋይነት ክቡር መንነት” እየተባለ ሲጨፈር ያ በወጣትነቱ አድር ባይ ዛሬም አድር ባይ የሆነዉ ግርማ ብሩ ቁጭ ብሎ ይመለከት ነበር። ይህ ህይወቱን ሙሉ ለሆዱ ብቻ የኖረ አድር ባይ አልገባዉም እንጂ ኦሮሚያ ዉስጥ ዘጠኝ ወር ሙሉ የሱን ወገኖች የጨፈጨፉት እነዚያ “ትግራዋይነት ክቡር መንነት” እያሉ ሲጨፍሩ የነበሩትና የትግራይን ህዝብ ከተቀረዉ ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ለማጋጨት ሆን ብለዉ የተነሱ የህወሓት አባላት ናቸዉ ።
ኢትዮጵያ ሁለቱ የአለማችን ትልልቅ ሀይማኖቶች ክርስትናና እስልምና ከሺ አመታት በላይ ጎን ለጎን የኖሩባት አገር ናት። እነዚህ በስነ ምግባር የታነጹ መልካም ዜጎችን የሚያፈልቁ ተቋሞች ዛሬ የህወሓት ስልጣን ማስጠበቂያ ተቋሞች ሆነዋል። የኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” የማይዋጥላቸዉን ዜጎች ቃሊቲና ቂሊንጦ የሚልኩ የህወሓት ማጥቂያ መሳሪያዎች ናቸዉ። ዩኒቨርሲቲዎችና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ገዢዎቹ ያሰቡለትን ብቻ የሚያስብ ደካማ ትወልድ የሚፈጥሩ የፕሮፓጋንዳ ተቋሞች ናቸዉ። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲን አዉቀዋለሁ፤ ማወቅ ብቻ ሳይሆን የዚህ ዩኒቭርሲቲ ኩሩ ተመራቂ ነኝ፤ ይህ ዩኒቨርሲቲ እኔን “እኔ” ያደረገ ምርጥ የአገራችን ተቋም ነበር፤ እንደዛሬዉ ከጫካ የመጡ ተፈራ ዋልዋና በረከት ስምኦንን የመሳሰሉ በወጉ 12ኛ ክፍል ያልጨረሱ ደናቁርት እነ ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትንና እነ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘዉዴን ቁጭ አድርገዉ ታሪክ ለማስተማር ከመሞከራቸዉ በፊት!
ዛሬ ኦሮሚያ፤ ጎንደር፤ ጎጃም ፤ ኮንሶ፤ ኦጋዴን፤ ቢኒሻንጉል፤ አፋርና ጋምቤላ ዉስጥ “እንዳሰኛችሁ ትገድሉናላችሁ” እንጂ ካሁን በኋላስ ለ”ህወሓት አንገዛም” እያሉ ለፍትህና ለእኩልነት ውድ ህይወታቸዉን የሚሰጡት የኢትዮጵያ ወጣቶች ከሰሞኑ በረከት ስሞኦን፤ አባይ ጸሐዬና እነዚያ ሁለት አሻንጉሊቶች “EBC” ላይ ቀርበዉ የነገሩን አይነት “መልካም አስተዳደር” ስለጎደላቸዉ ብቻ አይደለም። የኢትዮጵያ ወጣት የአንድ ዘር የበላይነት እንዲጠፋ ይፈልጋል፤ የኢትዮጵያ ወጣት ነጻነት፤ ፍትህ፤ እኩልነትና ዲሞክራሲ በተረጋገጡበት አገር ዉስጥ መኖር ይፈልጋል፤ የኢትዮጵያ ወጣት ዬትም ቦታ ይወለድ ወይም ከየትኛዉም ዘር ይወለድ የወደፊት ዕድሉ በችሎታዉና በባህሪይዉ እንጂ በዘሩ እንዲመዘን አይፈልግም። ለዚህ ነዉ ይህ ወጣት ዛሬ በአራቱም ማዕዘን ባዶ እጁን እስካፍንጫቸዉ ከታጠቁ የአግዓዚ ነብሰ ገዳዮች ጋር ፊት ለፊት የሚጋፈጠው። የኢትዮጵያ ህዝብ ለነጻነትና ለእኩልነት የሚያደርገዉ ትግል ክፉኛ ያስደነገጠዉ ዕብሪተኛዉ ስዩም መስፍን የመንና ሊቢያ ዉስጥ የደረሰዉ ቀዉስ ኢትዮጵያም ዉስጥ መድረሱ አይቀርም ብሎ የአዞ ዕምባ እያነባ የሱንና የጓደኞቹን ምኞት ነግሮናል። ወይ አቶ ስዩም ! . . . ይህ ያነበበዉን እንኳን የማይረዳ ጅላጅል የባድሜ ጉዱን የረሳን መስሎታል። ኢትዮጵያን የመን፥ ሶሪያና ሊቢያ ወደ ተጓዙበት መንገድ የሚወስዳት ስዩም መስፍን የገነባዉን ዘረኛ ስርዐት ዘለአለማዊ ለማድረግ የሚደረገዉ የጅምላ ግድያና ጭፍጨፋ ነዉ እንጂ ይህ ዕብሪተኛ ሊነግረን እንደሞከረዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱና ለነጻነቱ የሚያደረግዉ ትግል አይደለም። የኢትዮጵያ ወጣት በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረዉ የመብት፥ የነጻነትና የዲሞክራሲ ትግል እነ መስፍን ስዩም “EBC” ላይ ቀርበዉ ስለደነፉ የሚቆም ትግል አይደለም። አባይ ጸሐዬ፤ ስዩም መስፍን፤ ሳሞራ የኑስና አባይ ወልዱ የሚገነፍሉ ድስቶች ናቸዉ . . . . እነዚህ ጡንቻ እራሶች አልገባቸዉም እንጂ “የሚገነፍል ድስት” የሚያበላሻዉ እራሱን ነዉ! ቸር ይግጠመን!!!
አፍሬም ነኝ ከአርበኞች መንደር
ebini23@yahoo.com

No comments:

Post a Comment

wanted officials