Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, February 14, 2016

“ጎንደር ያለው ህዝባዊ አመፅ ኦሮሚያ ካለው ህዝባዊ አመፅ አይለይም” – የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋይ ዘመነ ካሴ

zemene kase
(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ)
አርበኛ ታጋይ ዘመነ ካሴ የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ፖለቲካ መምሪያ ኃላፊ የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታና ወደ ኤርትራ በረሃ የሚጎርፉ ወጣቶች ቁጥር እየናረ መምጣትን በሚመለከት ከአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ ጋር ያደረጉት አጭር ቃለ ምልልስ በፅሁፍ፡፡
===================================================
ጥያቄ
“እንግዲህ እንደሚታወቀው አርበኛ ታጋይ ዘመነ ካሴ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ኦሮሚያ አካባቢ፣ በጎንደር ፣በጋቤላና በደቡብ ከፍትኛ የሆነ ውጥረት አለ፤ግጭትአለ፤ ህወሓት ደግሞ ከቁጥጥሩ ውጭ ሆኖበታል፤ ከፍተኛ የአፈና መዋቅሩን፣ የእስር መዋቅሩን እንዲሁም ጭፍጨፋ ከዚያም ባለፈ ደግሞ ወደ ዘር ግጭት የመቀየር ስራ እየሰራ ይገኛል፤ እና ይሄን አገሪቱ ላይ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ከእኛ ትግል አንፃር እንዴት ይመለከቱታል?”
አርበኛ ታጋይ ዘመነ ካሴ
“አመሰግናለሁ! እድሉን ስለሰጣችሁኝ እና እንግዳ አድርጋችሁ ስለጋበዛችሁኝ በዚህ ጉዳይ ላይ እንድናገር፡፡
“አገር ውስጥ ያለው ቅድም በጠቀስካቸውና በአንዳንድ አሁን በይፋ ያልወጡ አካባቢዎች ያለው የህዝብና የመንግስት ትንቅንቅ በየትኛውም መለኪያና መመዘኛ ብታየው እሚያሳይህ ወይም እሚነግርህ አንድ ነገር ነው፡፡ እሱም ምንድን ነው? ብሔራዊ ጭቆናው፤ ፀረ-ጭቆና ትግል ምንም አይነት መልክ ልንሰጠው ብንችል ምንም አይነት ቀለም ልንቀባው ብንችል በተመሳሳይ አይነት ስሜት እና በተመሳሳይ አይነት ግለት በተመሳሳይ አይነት እምቢተኝነት ደረጃ እየደረሰና እየመጣ እንደሆነ ነው የሚያሳየው፡፡

“በመሰረታዊ ጥያቄ ደረጃ ጋምቤላ ያለው ህዝባዊ አመፅ ኦሮምያ ካለው ህዝባዊ አመፅ አይለይም፤ ጎንደር ያለው ህዝባዊ አመፅ ኦሮሚያ ካለው ህዝባዊ አመፅ አይለይም፡፡መሰረታዊ ጥያቄው በዛ አገር ውስጥ እንደ ሰው ሰው ሆኖ የመኖር፣ ተከብሮ የመኖር፣ እንደ ዜጋ የመኖር ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ በተለይ ላለፉት 25 ዓመታት ሰው ከሰው በታች ተዋርዶ ተቀጥቅጦ፣ ታፍኖ መፈናፈኛ አጥቶ ነው እየኖረ ያለው፤ እየተገዛ ያለው፤ የዚህ አፈና የዚህ ጭቆና ፀረ-ጭቆና እና ፀረ-አፈና ትግል በተጠናከረ ሁኔታ መልክ እየያዘ በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል እየተነሳ እና ወደ አንድ አቅጣጫ እየሔድን መሆኑ ነው የሚታየው እሱን ነው ማረጋገጥ የሚቻለው፡፡

“ከዚህ አኳያ ምን አልባት ከኛ ትግል ጋር አያይዞ ለማየት የእኛ ትግል ህዝቡን ከወያኔ አፈና ነፃ የማውጣት ትግል ነው፤ ኢትዮጵያዊያን እንደ ዜጋ እንደ ሰው ልጅ በሓገራቸው የዜግነት መብታቸው ሰውነታቸው ተከብሮ የሚኖሩበት ሆኔታ እንዲፈጠር ነው የምንታገለው፡፡ የምንታገልለትን ዓላማ ነው ሰው አንስቶ ባደገበት ማህበረሰብና ቀየው እየታገለ ያለው፤ ስለዚህ የእኛን ትግል ነው፣ ሰው እኛ የምንለውን ነው፣ ሰው በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል እያነሳ፣ እየታገለ ያለው ስለዚህ ፀረ-ጭቆና ትግል ነው የምናደርገው፡፡ ፀረ-ጭቆና ትግሎችን በየቦታው እያየን ነው፤ ይሔን ትግል እንደግፋለን! ይሄን ትግል እናበረታታለን! በተቻለን መጠን ወደ ምንፈልገው አንድ አቅጣጫ በፍጥነት ሄዶ የምንፈልገው ለውጥ እንድናይ ለማድረግ ድርጅታዊ የሆነ ስራ ይጠበቃል፤ እሱን ማድረግ እንግዲህ ከሁላችንም የሚጠበቅ ነው፤ የሚሆነውን እያደረግንም እደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡

“እነዚህ በየቦታው እየተነሱ ያሉ ህዝባዊ አመፆች በተደራጀ ሁኔታ፣ በተቀናጀ ሁኔታ በርካታ የሆኑ ፖለቲካዊ ችግሮቻችንን ፈትተን ወደ አንድ አቅጣጫ ሂደው የምንፈልገውን ሀገርና ማህበረሰብ መገንባት የምንችልበት፤ ዓላማችን ላይ እንድንደርስ በጣም በጥንቃቄ በአስተዋይነት በብልሃት መያዝ፣ መመራትና መቀናጀት ይኖርባቸዋል፡፡ እሱን ማድረግ ደግሞ በተለይ ከእኛ አይነት ሰፊ መሰረትና ሰፊ ሕዝባዊ ድጋፍ ካለው ድርጅት የሚጠበቅ ነው የሚሆነው፡፡ እንግዲህ አንተም እንደምታውቀው እሱን ለማድረግ እየተሞከረ ነው ያለው፤ አጠናክረን መቀጠል ነው ያለብን፡፡
“ከዚህ አኳያ ቅድም ያነሳህው የታፈነ ማሕበረሰብ ልጆች፣ የታፈነ አካባቢ የፈጠራቸው ወጣቶች በተለይ በዚህ ወር እንዳልከው ወደ ኤርትራ እየጎረፉ ነው ያሉት፤ ማሰልጠኛ ካምፑ በጣም ከዚህ በፊት ባልታየ ሁኔታ በምትለው ደረጃ በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች እንዳልከው ከትግራይ እስከ ሞያሌ፣ ከሞያሌ እስከ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ጎንደር፣ ጋምቤላም ጭምር ድረስ፣ ቤንሻጉልም ጭምር ድረስ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ወያኔን ለማስወገድ የሚደረገውን ትግል በተሻለ ፍጥነትና በተቀናጀ ሁኔታ በአጭር ጊዜ እንዲቋጭ በመሳሪያው በኩል የሚደረገውን ትግል ለማጠናከርና ለመደገፍ እንደ አንድ ወጣትም እንደ አንድ ዜጋም የሚጠበቅባቸውን ለማድረግ መሰረታዊ የሆነ ምክኒያታቸውን ተሸክመው ከነመሰረታዊ ጥያቄዎቻቸው ወደ ድርጅታችን እየመጡ ነው ያሉት፡፡ ማሰልጠኛ ካምፑን እንግዲህ አንተም በቅርቡ ያየህው ይመስለኛል፤ በበርካታ ወጣቶች ተሞልቷል፤ አሁንም እዚህ ወደ እናንተ ስቱድዮ እየመጣሁ ባለሁበት ሰዓት ላይ ይህንን ማረጋገጥ የሚያስችል በርካታ የሰው ኃይል ወደዚህ ወደ ኤርትራ እየገባ መሆኑን ነው እያረጋገጥኩ ያለሁት፡፡ ይህንን የሰው ኃይል አስተባብሮ ድርጅቱን ምቹ መታገያ ሜዳ አድርጎ አቀናጅቶ እምንፈልገው ሀገር መስራት ነው የሚጠበቅብን፤ ይህን ለማድረግ ደግሞ እጅግ እጅግ አስፈላጊ ክሪቲካል ወቅት ላይ የደረስን ነው እሚመስለኝ፤ የደረስን ነው የሚመስለን፡፡”
ጥያቄ
“አመሰግናለሁ አርበኛ ታጋይ ዘመነ ካሴ! አገርቤት ውስጥ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተለያዩ አገር ውስጥም ውጪም ባሉ የመገናኛ ብዙኃን በማሕበራዊ ሚዲያውም እየተገለፀ ይገኛል፤ እናም ትግሉ ጫፍ ላይ የደረሰበት ሁኔታ ላይ ነው ያለው፤ አርበኞች ግንቦት 7 ደግሞ የዚህ የትግሉ መሪ ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብም ተስፋ የሚያደርግበት ድርጅት ነው፡፡ አርበኞች ግንቦት 7 አለበት ወደ ሚባለው ቦታ በተለይም ደግሞ ወደ ኤርትራ በረሃ ለመምጣት በሚልዮን ሚቆጠር ሰው ወደ ዚህ ለመምጣት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ነው፤ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ወደዚህ ለመምጣት ጥያቄ የሚያቀርቡልን ሰዎችም ቁጥር ማስተናገድ ከምንችለው አቅም በላይ እየጨመረ ነው የሚገኘውና… ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ህወሓት ድንበሩን በከፍተኛ ሰራዊት አጥሮ ከፍተኛ የሆነ የአገሪቱን መዋለ ንዋይ እያፈሰሰ የደህንነትና የአፈና መዋቅሩንም እዚህ አካባቢ እያጠናከረ እየሰራ ይገኛል፤ ነገር ግን ሰው መምጣቱን አላቆመም፤ ያም ሆኖ አሁንም ትግሉን የእኛን ትግል ለመቀላቀል በተለይ ደግሞ የጠመንጃውን፣ የአርበኝነቱን ትግል ከህዝባዊ እቢተኝነቱ በተጓዳኝ ለመቀላቀል ለተዘጋጁ ወጣቶች እንደ ፖለቲካ መምሪያ ኃላፊነትዎ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?”
አርበኛ ታጋይ ዘመነ ካሴ
“ትግሉን እንዲቀላቀሉና የነገ ጀምበራቸው እንዳትጠልቅ መስራት ሚገባቸውን ነገር መስራት እንዳለባቸው ወይም እንዳለበት በተደጋጋሚ ጥሪ ስናስተላልፍ ቆይተናል፡፡ አሁንም እሱ በቂ ሰሚ እያገኘ ነው ሚመስለኝ በእኔ በኩል፤ ይሄንን ልል የቻልኩት ቅድም እንዳነሳሁት እንዳልከው በመሳሪያ ወያኔን የማስወገዱን ትግል የሚያግዙና በዚህ ለመሳተፍ የቆረጡና የተነሱ በርካታ ወጣቶች እየጎረፉ ነው ያሉ እስከ ዛሬ ጧዋት ድረስ፡፡ ስለዚህ በቂ ምክንያት፣ በቂ መነሻ እና በቂ የስብለት ደረጃ ወያኔን በተመለከተ ስለደረሰ በተለየ ስለወያኔ ጭቆና፣ ስለ ወያኔ አፈና እየነገርክ፣ እያስረዳህ ተደጋጋሚ ጥሪ እንደው ማድረግ የማትችልበት ደረጃ ላይ እየደረስን ይመስለኛል፡፡ ሰው፣ ወጣቱ ተረድቶ፣ ገብቶት እሱን እያደረግን እየሆነ ስለሆነ፡፡ ከዚያ ውጪ ምን አልባት ከዚህ ጋር በተያያዘ ስላለው የምለው ነገር ካለ ምለው እንዳልከው ምናልባት ከሶስት መቶ ሺህ ሰራዊት የማያንስ ሰራዊት ከኤርትራና ኢትዮጵያ ከሚዋሰኑበት ድንበር አካባቢ ወያኔ በተቻለው መጠን እያንዳንዷን እርምጃ በሰራዊት አጥሮ ከመሃል አገር ያለውን ስሜት፣ በኢትዮጵያ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያለውን ፀረ- ወያኔ ስሜት፣ ፀረ- ወያኔ አቋም ብቻ ሳይሆን በመሳሪያ ወያኔን የማስወገድ ፍላጎት እያደገ መምጣቱን እያደገ ከመምጣቱ አልፎ በተግባር መረጋገጡን ያየው ወያኔ ይሄ እንዳይሆን እያንዳንዱን ቀዳዳ ለመዝጋት ሙከራ ሲያደርግ ነው የምናየው፡፡ እንዳልከው በርካታ ቁጥር ያለው ሰራዊት አስፍሯል፤ ከጫፍ እስከ ጫፍ የአፈና መዋቅሩንም ጠለፋ ወዘተ የምትለው ከስልክ ጠለፋ እስከ ሰው መንገድ ላይ ጠለፋ በርካታ ነገር እያደረገ ነው፡፡ እንዳልከው ግን ነፃነቱን የሚፈልግ፣ ለነፃነቱ ቀናኢ አላማ ያለው የቆረጠ ወጣት ከሆነ እሱን እያለፈ በሚኖሩ ቀዳዳዎች በሙሉ እየሾለኩ መምጣት እንደሚቻልና እዚህ ያለውን የአርበኝነት ትግል መቀላቀል እንደሚቻል እያየነው የመጣነው ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ዛሬ አንተ እና እኔ እያወራንበት ያለውን ቀን ጨምሮ በዚህ ወር ያለውን አጠቃላይ የሰውን ወደ ኤርትራ በርሃ መጉረፉን ስናይ ያነን ማድረግ እንደሚቻል ነው እየተረጋገጠ ያለው፡፡ ስለዚህ ጥንቃቄ ያስፈልጋል! ይህ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ወጣቶች፣ በጣም በርካታ የሆነ ቁጥር ያለው ወጣት አንተ እንዳልከው ጥያቄ እንደሚያቀርብ አውቃለሁ፤ በየቀኑ በየት መልኩ ሊያገኙን እንደሚችሉ፣ የት ሊያገኙን እንደሚችሉ ጥያቄዎች አሉ፡፡ አንዳንዴ ከጥንቃቄ አኳያ እኛ የምናስቀምጣቸውን ፕሮሲጀሮች ጨምሮ በመጣስ ሰው መምጣት፣ ቶሎ ትግሉን መቀላቀል ፍላጎት ስላለው ሰው በራሱ መንገድ ሲመጣ ይታያል፡፡ ጥንቃቄ ያስፈልጋል! በጣም ቂመኛ ሰዎች ናቸው! በጣም ተንኮለኛ ሰዎች ናቸው! ወደ ኤርትራ የኛን ትግል ለመቀላቀል የሚመጣን ግለሰብ እጃቸው ላይ ሲገባ በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት የሚያደርጉትን የምታውቀው ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ኤርትራ በረሃ ሚደረገው ጉዞ ዛሬ ላይ ያለው የመቶዎች፣ የሺዎች ጉዞ ነገ ወደ ሚሊዮኖች ጉዞ እንደሚቀየር፣ ወደ ሚሊዮኖች ጎርፍ እንደሚቀየር ምንም ጥርጥር የለኝም የለንም፡፡ ይህንን ነገ በታሪክ ፊት ማየት የሚቻል ነው፤ ማረጋገጥ የሚቻል ነው፤ ምክንያቱም የመኖርና ያለመኖር እንደ ማህበረሰብና እንደ ሃገር የመቀጠልና ያለመቀጠል ትግል ነው እያደረግን ያለነው፡፡ ለዛ ደግሞ ሰው ከበቂ በላይ የሆነ ብስለትና ነገሮችን የመረዳት ደረጃ ላይ ስለደረሰ እሱ ይሆናል፤ እሱ ይቀጥላል፡፡

“ከዚያ በዘለለ ግን እንዳልከው የህዝባዊ እቢተኝነት ትግል በሃገር ውስጥም ይደረጋል፤ መደረግም ይኖርበታል፤ በተለያየ መጠን፣ በተለያየ አንግል፣ በተለያየ መስክ የሚደረጉ ትግሎች ይኖራሉ እየተደረጉም ነው፡፡ ዋናውና መሰረታዊ የሆነው የወያኔን እብሪት የሚያስተነፍሰው፣ የወያኔን ቅስም የሚሰብረው ብሎም 25 ዓመታት ከኖረበት ዙፋን ሊነቅለው ሚችለው አንድ አስፈላጊ የሆነ የትግል ስልት አለ፤ እሱም የመሳሪያው ትግል ነው፡፡ ያን መሳሪያ ለማንሳት ሰው ሊሽቀዳደም ይገባል፡፡ አሁን በዚህ ወር እያየነው ካለነውም በላይ መምጣትና ትግሉን መቀላቀል ያስፈልጋል፡፡ በተቻለ መጠን የመሳሪያ አጠቃቀምን ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ስለሃገራችን የምናስበውን፣ ያለንን ቀናኢ ዓላማና ራዕይ፣ ተልዕኮ ጭምር የማሳወቅ ስልጠና ይሰጣል እዚህ ኤርትራ ውስጥ እንደምታውቀው፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ኤርትራ ውስጥ ምናደርገው ስልጠናም እንደው በዚህ አጋጣሚ በሚሊዮኖችም ቁጥር ሊቀጥል ይችላል ወታደራዊም ፖለቲካዊም ስልጠና፤ ዝምብሎ የሆነ ጊዜ ላይ ዘግተኸው የምትሄደው ፕሮጀክት ስራ አይደለም፡፡ እዚህ የያዝነው ስትራቴጅካሊ የኤርትራ ህዝብ መንግስትና እኛ ኢትዮጵያዊያን ድርጅታችን የጋራ የሆነ አንድ ቋሚ ዘላለማዊ ስትራቴጅክ ኢንተረስት አለ ብዬ ነው የማምነው፤ ብለን ነው የምናምነው፡፡ እንደ ድርጅት የስትራቴጅክ ሆነ የጋራ ፍላጎት እስካለ ጊዜ ድረስ አሁን ያለንና አብረን እድንቀሳቀስ ያደረገንን ፕሮጀክት በአምስት ዓመት የምትዘጋው፣ በአሰር ዓመት የምትዘጋው አይደለም፤ የኤርትራ ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝብ እስካሉ ድረስ የሚቀጥል ነው ሚሆነው፤ ከእኛም ትግል አኳያ የጀመርነው ይሔ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሚሊዮኖቹም ይሰለጥናሉ እዚህ ኤርትራ ውስጥ፤ በፖለቲካ በወታደራዊም መስክ እና በተያያዥ ጉዳዮች አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ሺዎችም ይሰለጥናሉ፤ እሱን ነው እያደረግን ያለነው፤ እንደው እንዳልኩት ዘግተኸው በሆነ ወቅት ላይ ምትወጣው ፕሮጀክት አይደለም የሚሆነው፤ መሆንም አይገባውም፡፡ እና ሰው አሁን ያለው አበረታች የሆነ፣ አሁን ያለው ለትግል በጣም ምቹ፣ ለውጥ ምታመጣበት ወቅት፤ ማምጣትም የግድ ነው፤ ከዚህ ውጪ ሌላ አማራጭ ስለሌለ፤ በደንብ ትርጉም ያለው ወቅት እንዲሆን፣ በደንብ በአጭር ጊዜ ምንፈልገውን ነገር ምናገኝበት ወቅት እንዲሆን፣ ተጠናክሮ ወደ ኤርትራ ሚያደርገውን ጉዞ መቀጠል መቻል አለበት ነው፡፡
“ምናልባት መልዕክት ማስተላለፍ ካለብኝ ልል ምችለው በአጠቃላይ ወያኔን ማስወገድ እንዳለብን ሰው ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ መግባባት ላይ የደረሰ ይመስለኛል፤ ያ ብስለት ላይ የደረሰ ይመስለኛል፡፡ ወያኔን ለማስወገድ የመሳሪያ ትግሉ እጅግ! እጅግ! ወሳኝ እንደሆነ የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰ ይመስለኛል፤ ምናልባት በቅርብ ጊዜ በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን ያደርጉ ከነበሩ ድርጅቶች አካባቢ እየተነሱ ወደ እዚህ ወደ ኤርትራ እየመጡ ያሉ በአመራርም በአባልነትም ደረጃ የነበሩ ወጣቶች ለእዚህ ማሳያ እሚሆኑ ይመስለኛል፡፡
“በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ወያኔን ማስወገድ ሲደመር ወያኔን በመሳሪያ ማስወገድ ብቻ ሳይሆን በዚህ ወቅት የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰበት ኤርትራ ውስጥ ሆኖ ትግል ማድረግ እንደሚቻል የጋራ መግባባት ላይ የተደረሰ ይመስለኛል፡፡ ትግል ማድርግ ብቻ ሳይሆን ውጤታማም እንደሚኮን ይሄም የሚሰፈረው ታክቲካል በሆነ የአጭር ጊዜ ግብ ሳይሆን ቅድም እንዳልኩት በጣም የረጅም ጊዜ የጋራ የሆነ ስትራቴጅ ግብን መሰረት ያደረገ ጉዞን ያማከለ ስለሚሆን ከኤርትራ ተነስቶ ውጤታማ የሆነ ትግል ማድረግ እንደሚቻል ጭምር የጋራ አቋም ላይ የጋራ ብስለት ላይ ተደርሷልና ይሄንን ይዞ ይሄን ትልቅ አስተሳሰብ ለውጥና የጋራ አስተሳሰብ ይዞ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ያ እንዲሆን ደግሞ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅበትን ጠጠር ለመወርወር ድርጅታችን እሱን ማስተናገድ የሚችል ድርጅት እንደሆነ ነው ማምነው በግሌ፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወጣት ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ያለ ወጣት ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን ጉዞ እንዳያቆም ነው ምለው፡፡”

No comments:

Post a Comment

wanted officials