የአዲስ ድምጽ ሬዲዎ ጃንዋሪ 17.2016 3 ሰዎችን፤- 1ኛ. ዶ/ር አረጋዊ በረሄን የትግራዮች ለደሞክራሲያዊ ትብብር ሊቀ መንበር፤ 2ኛ. ዶ/ር በያን አሶቦን ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር 3ኛ/ አቶ ተክሌ የሻውን ከሞረሽ ወገኔ የአማራ ድርጅት አቅርቦ በኢትዮጵያ ጊዜያዊ ሁኔታ ላይ አወያይቷቸው ነበር። በቅድሚያ አቶ አበበ የተዋንያኑ አመራረጥ የተዋጣለት ስለ መሆኑ ያለኝን አድናቆት ልገልጽለት እወዳለሁ፤ እነሱም ለዚህ መልካም ተግባር ዝግጁ ሆነው መገኘታ
“…የዲያሰፖራው ሃይል፤ ውጭ ያለው ሃይል ውጭ ነው ያለው እንግዲህ ምከንያቱን የመለየቱ ጉዳይ የሚጠበቅብን ነው። እንዴት ነው? አሁን ደጋፊ ነን? መሪ ነን? የሚለው ጉዳይ እንግዲህ አገር ውስጥ ያለውን ትግል የሚመራው እዚያ ያለ ሃይል ነው፤ እዚያ ያለ ሕዝብ መሆን አለበት። እኛ ወይ ገብተን እዚያ መታገል አለብን ወይ ደግሞ ከፍተኛ የድጋፍ አስተወ ጽኦዋችንን መቀጠል አለብን። በሪ ሞት ኮንትሮል ትግል መምራት እንደማይቻልም ታይቷል እሱን ባን ቃጣም…” ስርዝ የኔ
ዶ/ር በያን አሶቦ
|
ቸው የሚያስመሰግን ነው።
እኔ ታዲያ ያንን ሰፊ ውይይት ለመተቸት የተነሳሁ አይደለሁም፤ ሀሳብ ልሰጥበት በርዕሰ ስላስቀመጥኩት ጉዳይ መዳረሻ የሚሆነኝን ያህል ብቻ ቀንጨብ አድርጌ ለመያዝ ነው።
አስተናጋጁ ለሁሉም ያቀረበው የጋራ ጥያቄ ፤ “ባሁኑ ሰዓት ብዙዎቻችንን እያበሳጨ ያለው በጣም በየጊዜው የተደረገ ነገር ነው፤ አዲስ ነገር አይደለም፤ ነገር ግን አሁን ለሁለትና ለሶስት ወር የቆየ ሊቆም ያልቻለ ማባሪያ የሌለው ግድያ ባገዛዙ በተለይ በኦሮሞ ክፍለሃገር የተለያየ አካባቢ ወገኖቻችን እየተገደሉ፤ እየታሰሩ፤ እየተፈናቀሉ ነው የሚገኙትና እንዴት ነው የተከታተላችሁትና የህብረተሰቡስ ጥያቄ፤ ያለውን ሁኔታ በእናንተ ዕይታ እንዴት ነው ያያችሁት?” የሚል ሲሆን፤ ተጠያቂዎቹን ተራ በማስያዝ መልስ እንዲሰጡ አደረገ። ዶ/ር በያን ጀመሩ፤ ዶ/ር አረጋዊ ቀጠሉ አቶ ተክሌ የሻው አሳረጉ።
ተጠያቂዎች የቀረበላቸውን ጥያቄ ሲያስተናግዱ የኔ ከሚሏቸው የየግል የልብ ቁስሎች እየቆነጣጠሩ የጨመሯቸው ብዙ ነጥቦች ቢኖሩም፤ በጊዜው የኦሮሞ ኢትዮጵያውያን ተማሪ ወጣቶች ላነሱት ጥያቄ የማስተር ፐላኑ እንደምክንያት ሆነ እንጂ፤ የወያኔ አገዛዝ ላለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ሲፈጽም የኖረው የተከማቸ በደል ብሶት ጋኑ ሞልቶ መፍሰሱን የሚያሳይ ምልክት ነው ነው በማለት ነበር ሶስቱም ባንድ ቃል ያሰመሩበት። ከዚህ በሁዋላም በኦሮሚያ ክፍለ-ሃገር – ክፍለ ሃገር የምለው እኔ ነኝ፤ ምከንያቱም በልጅነቴ በከብት ጥበቃ (እረኝነት) ስራ ተሰማርቼ ስሰራ ክልል የሚለውን ቃል ሲጠቀሙበት የማውቀው ለከብት ግጦሽ የሚውል የሳር መሬት ሲከለልበት ስለነበር፤ ዛሬ ወያኔ በከብት ምትክ ሰውን መከለያ ማድረጉ ስላልተመቸኝ ነው። – በሰፈነው እንቅስቃሴ ላይ ብዙ አልቆዩበትም። ከዚያ ይልቅ በመልስ አሰጣጡ ሂደት ጊዜ በአቶ ተክሌ የሻው ለመድረኩ እንግዳ የሚመስል “እንቅስቃሴውን ኢትዮጵያዊ መልክ እንስጠው” የሚል ሃሳብ ተነስቶ ስለነበር፤ እሱን የመልሱ አካል ሆኖ እንዲዋሃድ ለማለማመድ የተደረገው ውይይት ሰፋ አለና ተሳታፊዎቹን ባላሰቡት ጊዜና ፍጥነት ወደሌላ የውይይት ነጥብ ማለትም የሃገሪቱ መከራና ስቃይ ምንጭ የሆነው አጥፊ የወያኔ ሥርዓትን አደብ ማስያዝ ስለሚቻልበት የትግል ጥያቄ ጉዳይ አሸጋገራቸውና በዚያ ላይ ላደረጉት ውይይት ሰፊውን ጊዜ ሰጡት።
ብሎም ይህ ጸረ-ወያኔውን ትግል ማዕከል ያደረገው ውይይት በመጠናቀቂያው አካባቢ፤ ትግሉን ውጤታማ ለማድረግ፤ ሃቻምና፤ አምና፤ ዘንደሮ፤ ተናትም ዛሬም፤ እየተነሳ የሚጣለው የህብረት ትግል አስፈላጊነት በተለይ በአሁኑ ሰዓት ደግሞ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው! ማለት ብቻ ሳይሆን፤ ጉዳዩን ለማፋጠን ድርጅት ከድርጅት ጋር ለምሳሌ ኦዴኤፍ ከሸንጎ ጋር፤ ሞረሽ ወገኔ እንዲሁ ከሸንጎ ጋር ውይይት እያደረገ እንደሚገኝ ተበስሯል። በዚህ መሃል ግን ዶ/ር በያን – መድረኩ ሳይበርም ቢሆን፤ ልብ ብላችሁ ቨዲዎውን አዳምጡት ልክ ዲያስፖራውን ዞር ዞር ብለው የሚቃኙ ይመስላል – ለመሆኑ እኛ ማንነን? የትና ምንስ ለማድረግ ነው ሕብረት የምንፈጥረው በሚል መንፈስ የቃኙትንና የኔንም ቀልብ የሳበውን ከዚህ ጽሁፍ አናት አካባቢ በአራት ማዕዘን ማዕቀፍ ውሰጥ ያስቀመጥኳትን ሃሳብ የወረወሩት፤ ሌሎቹ ተሳታፊዎች ልብ ብለዋት ይሁን አይሁን ለጊዜው መረጃ ባይኖረኝም፤ ሃሳቧ ወደፊት በሚፈጠረው ሕብረት ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና ትጫወታለች ብዬ አስባለሁ፤ መጫወትም አለባት፤ የዚያን ጊዜ እንጠብቃት፤
ሶስቱም የውይይት ተሳታፊዎች አበክረው የዘከሩለት የትግል ዓይነት የሰላማዊ ትግል/ሕዝባዊ እምቢተኛነት መሆኑ ግልጽ የሆነውን ያህል፤ ይህ ህዝባዊ እምቢትኝት እንዴት ነው የሚገለጠው? የትስ ነው የሚካሄደው? ሲሉ በያን ያነሱትን ጥያቄ ለማጠናከር ዕውነትም ብለን፤ ለናሙና ያህል ጥቂቶቹን ብናነሳ፤- ስትራይክ፤ ቦይኮት፤ ያልተፈቀደ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ፤ አግባብ የልሆኑ ህጎችን አለመቀበል የመሳሰሉትንና ባሁኑ ጊዜም ዛሬ በኦረሚያ ክፍለሃር፤ በጎንደር አካባቢ የሚጫጫሰውን ዓይነት መሪ የሌለውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ መስመር አሲዞ፤ በእቅድና በጥበብ እንዲራመድ ለማድረግ፤ እንደገና በያን እንዳሉት በሪሞት ኮንተሮል እንደማይቻል ማን ነው አሌ የሚል?
ትብብር ትብብር! ትብብር! ትብብር! ይህ ቃል የወሬ ወፈጮዋችን እሰኪሟልጥ ከርትፈነዋል፤ ሰልቀነዋል፤ አልመነዋል ማለት ብቻ ሳይሆን፤ ባህል ሆኖናል ብል የተሳሳተ ግምት አይሆንብኝም። ከፍ ብሎ በተደረገው ውይይት ላይም ተነስቶ ሲወራ ቀደም ሲል ተደርገው ስለነበሩ ህብረቶችም በዶ/ር አረጋዊ በርሄ “የተሞከሩ ህብረቶች ነበሩ” በሚል መነሳታቸውን አዳምጫለሁ። ይህንን እኔም አረጋግጣለሁ፤ ነበሩ። ነገር ግን ታዲያ እንዲሁ ነበሩ ብሎ ማለፉ ስላልተመቸኝ የሚከተለውን ላክልበት ሞክሬአለሁ፤
ካልተሳሳትኩ ወያኔ ስልጣን ከያዘ በሁዋላ ብቻ በተቃዋሚነት የተፈጠሩትንና ነበሩ የተባሉትን ትብብሮች በዝርዝር ላስቀምጣቸው፤ የመጀመሪያው የአማራጭ ሃይሎች ምክር ቤት፤ ሁለተኛው/ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ሕብረት (ኢተፖድህ)፤ ሶስተኛው/ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ሕብረት (ኢድሃህ)፤ አራተኛው/ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት)፤ የሚባሉት ናቸው። ስለያንዳንዳቸው የሚክተልውን ላስታወስ፤
አማራጭ ሃይሎች ምክር ቤት፤- ይህ ምከር ቤት የተቋቋመው ከጅምሩ ለማቋቋም ታስቦ ሳይሆን፤ በሀገርቤትና እውጭ ባሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች ትብብር ኢህአዴግን ጨምሮ በሃገር ቤት እንዲደረግ የተዘጋጀ የሰላምና እርቅ ጉባኤ ወያኔ አሻፈረኝ ቢልም ጉባዔው ተደርጎ ሲጠናቀቅ በአጋጣሚ የተቋቋመ ድርጅት ነው። ወያኔው የሱ በጉባዔው አለመሰታፍ ብቻ ሳይሆን፤ በጉባዔው ለመካፈል ከውጭ ሰዎች እንዲገቡ ከፈቀደ በኋላ ሀገር ሲደርሱ ማሰር ጀመረ፤ በመንገድ ላይ የነበርው ጉዞወን አቋርጦ ተመለሰ፤ ይህ የወያኔ ድርጊት በሃገር ቤቱና በውጭው ባለው ሃይል በኩል ጉባኤው እኛ ካልተካፈልንበት መደረግ የለበትም የሚል ሃሳብ ተነሳና ካከራከረ በዃላ በወግ የተጣሉና እርቅ የሚሹ ሰዎች ባለመገኘታቸው ጉባኤው የእርቅና የሰላም መሆኑ ቀርቶ ድርጅት ማቋቋሚያ ሆነና አማራጭ ሃይሎች ምክር ቤትን አምጦ ወለደ። ከዚያ በኋላ በውጭውና በሃገር ቤት የነበረው ግንኙነት ሻከረና ቀልብ ያለው ግንኙነት ሳይሰፍን ሰነባበተና፤ በመሃሉ ሌላ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ሕብረት (ኢተፖድህ) የሚለው ድርጅት የማቋቋም ሂደት ተጀመረ።
የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ሕብረት (ኢተፖድህ)፦ ይህ ስብስብ ልዩ የሚያደርጉት ሁለት ጥሩ ነገሮች ነበሩት፤ አንደኛ/ እስከዚህ ጊዜ ድርስ አንዱ ወያኔ እንደምክንያት እያደርገ ነገር ያቆረፍድበት የነበረ ጉዳይ በውጭ የሚገኙ ተቃዋሚዎች በመካክላቸው ጦረኞች አሉባችው፤ ሰላማዊ አይድሉም እያለ የሚወነጅለብት ምክንያት ጦረኞቹ ለሰላም ባላቸው ፍቅር ከወያኔ ጋር ያግባባን ነበር የሚሉትን የመሳሪያ ቋንቋ እርግፍ አድርገው የተውበትና ለወያኔ የሰላም እጃቸውን የዘረጉበት ጊዜ ሲሆን፤ በሌላው በኩል ደግሞ ይህ ስብስብ አለም አቀፍ ድጋፍ የተቸረውና የት ይደርሳል የተባለም ነበር። ታዲያ ምን ይሆናል ይህም ስብስብ “የማያድግ ልጅ … እንትን ይበዛዋል” እንዲሉ፤ ችግር የገጠመው ምስረታው በተጠናቀቀ በማግስቱ ነበር። የተፈጸሙት ነገሮች አስገራሚም፤ አሳፋሪም ነበሩ፤ መጥፎ ሽታ ስላላቸው እዚህ አይነሱም እንጂ፤ ሆኖም ይህ ስብስብ ከተቋቋመ በኋላ ያንን ጉባኤ አዝጋጅቶ በነበረው “ሰላም ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ቀንድ የምርምርና የተግባር ቡድን” (Research and Action Group for Peace in Ethiopia and Horn of Africa)” በተባለው ደርጅት ድጋፍ አማካይነት ወደሃገር ቤት የሚተላለፍ ቀስተዳመና የሚል ራዲዎ ፕሮግራም ነበር። ይህም ሊሆን የቻለው ቀደም ብዬ እንደጠቆምኩት ስብስቡ ክነበረው ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ የተነሳ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ሕብረት (ኢድሃህ)፤ ይህ ስብስብ 15 የፖለቲካ ድርጅቶችን አቅፎ የተቋቋመ ሲሆን፤ ከነዚህ 15 ድርጅቶች ውስጥ 10ሩ ከውጭ፤ 5ቱ ከሃገር ቤት የነበሩ፤ የዚያን ያህል ብዛት ያለው የፖለቲካ ድርጅት አሰባስቦ የያዘ ስብስብ እስከዛሬ ታይቶ አይታወቅም። እዚህ ስብስብ ላይ ጥኢት ልቆይበት፤ የስብስቡ አመራር ሃገር ቤት የተደረገ ሲሆን፤ ይኸው አመራር በውጭ የሚገኙት አባል ድርጅቶቹ በሃገር ውስጥ ተቋቁመው እንደማንኛቸውም በሃገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች በህጋዊነት ተመዝግበው እንዲንቀሳቀሱ የሚችሉበትን ሁኔታ ከመንግስት ጋር በመነጋገር እንዲያመቻች ይደረጋል፤ በዚህም መሰረት ሁኔታው በመንግሥት በኩል አዎንታዊ መልስ ያገኘ መሆኑን ገልጾ፤ በውጭ ያሉት አባል ድርጅቶቹ ወደሃገርቤት ገብተው ህጋዊ ሰውነት አግኝተው አብረው በህብረት እንዲነቀሳቀሱ መልክት ያደርሳል፤ የውጭየዎች „ፍንከች ያባ ቢላዎ ልጅ“ አሉ። ምናልባት እውጭ ካሉት በአመራር ላይ የሚገኙና በመነግስት በኩል በቂ መተማመኛ የሌላቸው ቢሆኑ እንኳን፤ የግድ የነሱን ወደሃገር መግበት ሳያስፈልግ፤ ሃገር ውስጥ ባሉ አባሎቻቸው አማካይነት ሊመዘገቡ እንደሚችሉ ሁሉ ከሃገር ቤቱ በኩል ሃሳብ ይቀርብ ነበር። ቆየና ከሃገር ቤቱ ሃይል ውስጥ ካ5ቱ ሁለቱ ህብረቱን ትተው ወጥተው ቅንጅትን ይፈጥራሉ፤ እንዲያ እንዲያ እያለ የግንቦት 1997 ዓ.ምህረቱ የአቶ መለስ „ዕንከን የለሽ“ – በዃላ ላይ „ዕውር ሲቀናጣ በትሩን ጥሎ ፍለጋ ይሄዳል“ እንደሚባለው የሆነበት – ምርጫ ይደርስና፤ ምርጫው ይደረግና፤ ወያኔ በምርጫ ይሸነፍና፤ አሸናፊዎቹ በአሸናፊነት ወንጀል ተከሰው በተሸናፊ ወያኔ ፊት ለፍርድ ይቀርቡና፤ የተሰጣቸው ፍርድ ከአንገት መድፋት ወይም አንገት ቀና አድርጎ ቃሊቲ ከመግባት መምረጥ ነበር፤ – እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባ ነገር የተሰጠው አማራጭ ነጻና ፍትሃዊ አይሁን እንጂ ዴሞክራቲክ ነበር – ከፍርድ በሁዋላ ስለሆነው መቀጠል አሰልቺ ስለሚሆን፤ እሱን አልፌ ከዘረዘርኳቸው ስብስቦች ሂደቶች ምን እንማራለን ወደሚለው ተሻግሬ ጠቅለል ያለ ሃሳቤን ላስፍር፤
ምን እንማራለ? የማወራው ለውጭው ሃይል እንደሆነ አይዘንጋ፤ ምንም እንኳን አንዱ ከሌላው ለየት የሚልበት የራሱ ገጽታ ቢኖርም፤ ሁሉም ከሃገር ቤቱ ሃይል ጋር ከሞላ ጎደል ግለጽ በሆነ መነገድ በመገናኘት በጋራ ይሰሩ ነበር። ሁሉም የዲያሰፖራው ድጋፍ ነበራቸው፤ በወጤትም በኩል ቢሆን፤ የሚመዘነው ወያኔን ከቤተ-መንግስት አውጥቶ በመጣል ብቻ ነው ካልተባለ በስተቀር፤ በ1997 ምርጫ ከቅንጅት ቀጥሎ ብዙ መቀመጫዎችን ያገኘው ህብረቱ እንደነበረ አይዘነጋም። ያም ሆኖ ደግሞ የውጭው ሃይል ህብረቱ በተቋቋመ ጊዜ አመችውን ሁኔታ ተጠቅሞ ወደሀገር ገብቶ/በሀገር ውስጥ ተተክሎ ትግሉን አለመቀላቀሉ ትልቅ ጥቁር ነጥብ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፤ ለምን ለሚለውም ጥያቄ አንድም መልስ የሰጠ የለም። ሕዝብም „እንግዳ ሳይመጣ ሁሉ ሴት“ እንዲሉ በውጭ ያሉት የራሳችን የሚሉት በሀገር ውስጥ መሰረት የሌላቸው፤ ወይም ቢኖራቸውም ውጭ ባለውና አገር ውስጥ ባለው ሃይላቸው መካከል መተማመን ባለመኖር ይሆናል የሚል መላ ምቱን አዚሞ ነው የቀረው። እድሉ ግን አምልጧል። አንባቢ የራሱን ሃሳብ ይስጥበት፤ እንደኔ ግን ወደፊት በውጭ ያሉ ድርጅቶች ከሁኔታዎቹ ብዙ ሊማሩባቸው የሚችሉ ነገሮች ስላሉ ነገ እኔን አንዱ ወይም ሌላው ሁኔታ ቢገጥመኝ እንዴት ነው የማስተናግደው ብሎ ለማሰብ ይረዳዋል ብዬ አምናለሁ። በመጨረሻም ታዲያ ከዚህ በላይ ያመላከትኳቸው በውጭና በግቢ መካከል የነበሩ ግንኙነቶች ከ1997 በዃላ ተቋርጠው ቀርተዋል፤ ለምን? ለዚህ ጥያቄ የዚያን ጊዜ በኢትዮጵያ የነበረውን ሁኔታ ከዚያ ወዲህ ካለው ጋር ማገናዘብ ለሚችል ሁሉ በቀላሉ መልሱን ማግኘት የችላል። ከሁሉም እጅ ይጠበቃል፤ ይህንን እዚህ ላይ ሸብ ላድርግና በአዲስ ድምጽ ራዲዎ በሶስቱ የድርጅት ተወካዮች ቀን የማይሰጠው ተግባር በመባል ውይይት ወተደረገበት፤ ከአድማጭ ጋር በተደረገ ጥያቄና መልስ ዳብሮ፤ የተግባራዊነቱን ከፍተኛ ሃላፊነትም አዋያዩንና ተዋያዮቹን ተሸካሚ አድርጎ፤ ወደተጠናቀቀውና የብዙዎችን የልብ ትርታ ወዳናረው፤ የአጣዳፊው ትብብር ጥያቄ ልለፍ፤
በውይይቱ ተሳታፊዎች የተነሳው አጣዳፊው ትብብር፤- ይህ ትብብር ተቃዋሚዎች የሚቃወሙትን ሃይል በሚገባ አውቀው የሚያቅዱት፤ የሚተልሙት፤ የሚቋጠሩት የሚፈቱት እርምጃ ሁሉ በዚያ ሃይል ላይ እንጥፍጣፊም እንኳን ቢሆን ተጽእኖ ለማሳደር የሚችል መሆን አለመሆኑኑን በማመዛዘን የተቀናጀ መሆኑ መረጋገጥ ይኖርበታል። ሌላው ከዚህ ተለይቶ የማይታየው ጉዳይ ደግሞ፤ የሚፈጠረው ትብብር ምንም ያህል ቅንጅቱ ቢያምር፤ መተማመን ከሌለ፤ ጊዜው የሚባክነው በውስጥ ፍትጊያ ስለሚሆን፤ አመርቂ ስራ ለመፈጸም አይቻልም። ለመተማመን ደግሞ ልዩነት ይታይባቸዋል የሚባሉ ጉዳዮች ላይ ትልቅ ትንሽ ሳይሉ አፍረጥርጦ በማውጣት፤ በማይፈልጉትና በሚፈልጉት ጉዳይ ላይ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ አለመኖሩን ማረጋገጥ ይገባል፤ ለዚህ አሰራር ጠቃሚ ይሆናሉ በማለት ካለኝ ልምድ ተነስቼ በቅድሚያ ሊጤኑ ይገባል የምላቸውን አካሄዶች እንደሚቀጥለው ለማቅረብ ሞክሬአለሁ፤ የትግሉ መነሻ በደልን መቃ
ወም ነው። በደል ደግሞ አድራጊና ፈጣሪ አለው። ዛሬ በሃገራችን በደል ፈጻሚ ነው የተባለውና ሕዝብ የሚማረርበት አንድ መጥፎ ስርዓት አለ። ታዲያም ይህ ሥርአት የሚጠራበት ስም ብቻ ሳይሆን፤ የሥርዓቱ አራማጅም ስም ሳይቀር አደናቃፊ ሚና ይኖራቸዋል የምላቸውን እንደሚከተለው አቅርቤያቸዋለሁ፤
1ኛ/ የሥርዓቱ መጠሪያ፤- አንዱ አፋኝ አምባ ገነን ሥርዓት ነው ሲለው፤ ሌላኛው ዘረኛ ሥርዓት ነው ይለዋል። በጉዳዩ ብዙ የማይጨነቅ ሰው ታዲያ፤ ኤዲያ! ያንንም አልከው ያንን ሁሉም ጸረ-ዴሞክራሲ ነው ተወኝ በማለት ሊሸኘው ይሞክራል። ነገሩ ግን እንደሱ አይደለም። በሁለቱ መካከል ትልቅ ልዩነት አለና።
ካጭሩ እንጀምር፤- – ዘረኛ ሥርዓት በተፈጥሮው ጸረ-ዴሞክራቲክ ነው።
– ጸረ-ዴሞክራቲክ ሥርዓት ሁሉ ግን ዘረኛ አይደለም። ይህ ዋናና የመጀመሪያው ልዩነት ሆኖ፤ ከሁለቱ ስርዓቶች ጋር የሚደረገውም የትግል ግብ-ግብ የተለያየ ነው። አጠር አጠር እያደረግሁ ሌሎች ልዩነቶችንም ላመላክት፤
ድርድረ፤- በአምባገንን ስርዓቶቸና በተቃዋሚዎቻቸው መካከል የሚደረገው ትንቅንቅ ከሁለቱ አንዳቸውንም በአሸናፊነት የሚያወጣቸው ሆኖ ሲያገኙትና መውጫ ሲያጡ፤ ወይም በሌላ ምክንያት ወደርድር መጥተው ጉዳዩ መፍትሄ እንዲያገኝ ይሆናል። ድርድር አድራጊዎቹ ማንኛቸውም ቢሆኑ የሚያገኙት ድርድሩ ያስገኘላቸውን እንጂ፤ የሚፈልጉትን እንደማያገኙ አውቀውም ነው ወደድርድር የሚመጡት፤ በተለመደው አነጋገርም ሰጥቶ መቀበል በሚለው መርህ መመራትም ማለት ነው።
ከዘረኛ ስርዓት ጋር ግን ለመደራደር እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ከላይ እንዳልኩት ድርድር ሰጥቶ መቀበልን ስለሚጠይቅ፤ ዘረኝነት ይሕንን መርህ በስራ ላይ ለማዋል የሚያስችል አይደለም። ከዘረኝነቱ ይህን ያህሉን ልተውልህ ይህን ያህሉን ተውልኝ አይባልም። ምክንያቱም ዘረኝነት ወደር የማይገኘለት አገርና ሕዝብ የሚያጠፋ በሽታ በመሆኑ ከምድረ ገጽ መጥፋት ያለበት ስለሆነ ነው – መናለባት ተግደዶ ይደራደር ይሆናል ቢባል እንኩዋን፤ የሚሰጠው እንጂ ምንም የሚቀበለው ነገር ስለማይኖር፤ ትልቅ የባልሞት ባይ ተጋዳይነት ጥፋት ከማድረስ ስለማይቆጠብ አስቸጋሪነቱን ልመገመት የሚቻል አይደለም። – ለድርድር አይመችም የምለው፤ አንድ ዘረኛ ድረጅት መቆሚያውና የጀርባ አጥንቱ ዘረኝነቱ ነው። ያ ከተነካበት ፈረሰ ማለት ነው። ስለዚህም ነው መለስ ዜናዊ በ2002ቱ ምርጫ ጊዜ የራሱን ጋዜጠኞች ሰብስቦ ጠይቁኝ በማለት ባደረገው ድራማ ላይ እንዴት ነው ስልጣን መካፈል ስለሚባለው ምን አስተያየት አለህ ተብሎ ሲጠየቅ “ይህ ማለት እኮ የኔ ፐሮግራም ስራ ላይ እንዳይውል መደናቀፍ ማለት ነው። እኔ እንደዚሕ ያለውን አላደርግም። ከተሸነፍኩ ጥየ መሄድ ብቻ ነው።” ሲል መልስ የሰጠው። ከሰወየው ሳልርቅ የኢትዮጵያ ገዢ ሆኖ እያለ እሱ አላኮራውም። “ትግሬ ወርቅ ነው ከዚህ ዘር በመወለዴ እኮራለሁ” ነበር ያለው። ይህን ማነው የጤና ነው ብሎ የሚወስደው? ይህ ሰው እኮ ለምሳሌ እናቱ ወይም አባቱ አንደኛቸው ከወላይታው፤ ከኦሮሞው፤ ወይም ከጉራጌው ወዘተ… – ከአማራው መቸም አይሞከርም – ቢሆኑ ኖሮ አጋም ስር እንደበቀለ ቁልቋል ሲያለቅስ የኖረ ይሆን ነበር ማለት ነው። እዚህ ላይ መጠንቀቅ ያለብን “ወርቅ” የሚሏት ቃል በጌጥነቷ ብቻ ሳይሆን እንደተጠቃሚው ሌላም የምትታወቅበት ሙያ ስላላት ግጭት እነዳትፈጥረ ነው። በመጨረሻም እንግዲህ ከሁለቱ ስሞች በየትኛው ስም የሚጠራውን ነው የምንታገለው የሚለውን ማሰብ ግድ ይላል፤ ስለ ሥርዓቱ መጠሪያ ጉዳይ በዚህ ላብቃና ወደስርዐቱ አራማጅ መጠሪያዎች ልሻገር፤
ስለገዥው ፓርቲ መጠሪያ
ሀ. ወያኔ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ጥቅም ላይ የሚውል። ተቃዋሚ የትግራይ ተወላጆች የማይጠቀሙበት፤ ሌሎችም
ሲጠቀሙበት ባይሰሙ ፈቃዳቸው የሚሆን፤ አንዳንዶቹ በአጼ ሃይለስላሴ መንግሰት ጊዜ አምጾ የነበረውን ገራገሩን ወያኔ ካሁኑ ከፉው ወያኔ ጋር መቀላቀል ይሆናል የሚል ስጋት እነዳላቸውም የሚጠቁሙ አሉ፤ አብዛኛው የሚጠቀምበት ግን ይህን ያህል የይዘት ልዩነት ያመጣል አያመጣም ብሎ ሳይሆን፤ በጣም የተለመደና ቀላልም በመሆኑ ብቻ ነው፤
ለ. ኢሕአዴግ በሃገር ቤት የሚገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጀቶች፤ በገዢው ፓርቲና አገልጋዮቹ ጥቅም ላይ የሚውል፤ ከላይ የጠቀስኳቸው ተቃዋሚ የትግራይ ተወላጆችም የሚፈቅዱት፤
ሐ. ወያኔ/ኢሕአዴግ፤ የወያኔ የበላይነት የጎላበት ሆኖ ሌሎቹም ተለጣፊዎቹ ሚና እንዳላቸው ለማሳየት በሚፈልጉ፤ ወይም
ደግሞ ከሁለቱ ባንዱ ቢጠራ ለውጥ የለውም ለማለት በሚፈልጉ፤
መ. የትግሬ ሕዝበ ነጻነት ግንባር/ ሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ሃርነት ትግራይ፤ በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች/ግለሰቦች በማለዋወጥ ስራ ላይ የሚውል፤ ህዝባዊ ወያኔ የሚለው አልፎ አልፎ ካልሆነ፤ ብዙ አይሰማም። የትግራይ ሕዝብ ነጻነት ከማለት ይልቅ በእንግሊዝኛው ቲፒ ኤል ኤፍ ቢባል ደስ የሚላቸው የትግራይ ተወላጆችመ አሉ።
ማሳሰቢያ.- ከዚህ በላይ ስለ አጠራሩ ያቀረብኩት እንዲሁ ከመሬት ተነስቼ ሳይሆን፤ አንዳንድ ካጋጠሙኝ ሁኔታዎች ተነስቼ ነው። በዚህ በስም አጠራር ምክንያት ዱላ ቀረሽ ጭቅጭቅ ሲስተናገድ አይቻለሁ፤ እራሴም ብሆን ወያኔ ከሚለው አልፎ አልፎም የትግሬ ሕዝብ ነጻነት ግንባር ከሚለው በስተቀር ሌላ ባፌ ስለማይዞር ካንዳንድ ወዳጆቼ የትግራይ ተወላጆች በንግግራችን መሃል እንዲያው እንዲህ ከምትል እንዲህ ብትለው ይሻላል የሚል ጥቆማ ያጋጥመኛል። የትግራይ ወንደሞቼን ችግራቸውን አልረዳም ማለቴ እንዳልሆነ ግን ተረዱልኝ፤ ትግሬ የሚለው ቃል ከክፉ አድራጊዎች ጋር ተቀላቅሎ መነገሩ ስለሚያሰቆጫቸው እንደሆነ እረዳለሁ፤ አኔም በነሱ ቦታ ብሆን ከዚያ የተለየ አቋም ላይኖረኝ እንደማይችል ዋስትና አልሰጥም። እዚህ ያነሳሁበት ምክንያት ግን በህበረት ትግል ሂደቶች ውስጥ ላለመተማመን በመጠኑም ቢሆን ምክንያቶች እንደሚሆኑ ስለምገነዘብ ነው። ስለሆነም ተነጋግሮ ለስርዓቱም ሆነ ለስርዓቱ አራማጆች በጋራ ስምምነት የተደረሰበትን ስም የህብረቱ የጋራ ቋንቋ ይዞ መሄድ የመለያያ ምክንያቶችን ማጥበቢያ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ። እነዚህን ሁለት ከስም አጠራር ጋር የተያያዙ ሃሳቦችን ከዳሰስኩ በዃላ ወደዋነው ጉዳይ ስመለስ በተለይ ሥርዓቱን በተመለከተ የትኛውን ዓይነት ሥርዓት ነው የምንታገለው የሚለውን ጥያቄ አንስቶ በሱ ላይ ስምምነት ኖሮ ግልጽ አቋም ሳይደወሰድ በተሸፋፈነ መልክ አንዱ ዘረኛ ሌላው አምባገነን እያለ አብሮ በህብረት መስራት እንደማይቻል፤ ግልጽ ነው። ነገር ግን ሁለቱም በየግላቸው ሊታገሉ ይችላሉ ወደዲያሰፖራው ተመልሰን የሚፈጠረውን አጣዳፊ ሕብረት እንየው፤
ትግሉ ሰላማዊ ነው እስከተባለ ድረስ፤ ዶ/ር በያን ያነሱት በሀገር ቤት ተተክሎ እዚያ ስለሚፈጠር ሕብረት ወይም እዚሁ በዲያስፖራው ስለሚመሰረት የድጋፍ ድርጀት ሕብረት የሚለውን ጥያቄ በቅድሚያ መልስ እንዲያገኝ ማድረጉ አላስፈላጊ የሆኑ ውጣ ውረዶችን ያስወግዳል። ሌላው ከዚሁ ጋር እየተነሳ ያለው „ሁሉን ያቀፈ“ የሚባለው ሃሳብ ነው። ይህ ነገር ለመረዳት ከሚያስቸግሩኝ ሚሊዎን ነገሮች አንዱ ነው። ሁሉን ያቀፈን ጽንሰ ሃሳብ የሚያራምዱት ወገኖች አንዴም አብራርተው ሲያስቀምጡት አላየሁምና ነው። ያ ማለት ግን፤ እራሴን በራሴ ለመርዳት ሙከራ አላደረግሁም ማለት አይደለም።
ስለሆነም፤ የመጀመሪያው ግንዛቤዬ እንዲታቀፉ/እንዲተቃቀፉ የሚፈለጉት በየሜዳው፤ በየተራራው፤ በየሸንተረሩ፤ በጓዳ በጎድጓዳው ተበታትነው የሚገኙትን የተደራጁ ሃይሎች በወረንጦ ለቅሞ ይዞ አስተባብሮ/ተባብሮ ሕብረት መፍጠር ማለት ይመስለኛል። እዚህ ላይ ግን፤ አንተኛው ማተብህን በጥሰህ፤ አንተኛው ደግሞ ክርስትና ተነስትህ ነው ለዕቅፍ የምትበቃው የሚሉ ገደቦች እነዳሉም አለመዘንጋቴን ዕወቁልኝ፤ ወደዃለም እመለስበታለሁ። በወረንጦ መልቀሙ ከተቻለ መጥፎ አይደለም። መቻሉን ግን እጠራጠራለሁ። ሌላው የሚታየኝ አማራጭ ደግሞ፤ ሁሉንም ለቅሞ መያዝ ሳያስፈልግ አንድም፤ ሁለትም፤ ሶስትም ጠንከረከር ያሉ ሃይሎች ተሰባስበው፤ እነሱ ለህዝብ የሚመኙለትን ሳይሆን፤ ሕዝቡ ምን ይፈልጋል? ምን እያለ ነው? የሚለውን ጥያቄ አንስቶ፤ የህብረተሰቡን ስሜት ተከታትሎ በመረዳት፤ ዛሬ ምን ይዘን ብንቀርብ ነው ህዝብ ለማዳመጥ ጆሮውን የሚሰጠን? የሚለውን ጥያቄ መልሶ፤ ለዚህ የህዝብ ስሜት ቀራቢ የሆነና ሁሉንም ያሰባስባል የሚል ፐሮግራም ዘርግቶ፤ ማስተዋወቅ፤ ሁሉም እስኪሰባሰብ ሳይጠብቁ እጅ ላይ ባለው ሃይል ሥራ መጀመር፤ ዱሮ ለቡሄ ስንጨፍር „እዚያ ማዶ ጭስ ይጨሳል አጋፋሪ ይደግሳል“ እንደምንለው የስራ ጭስ ሲጨስ ያየ፤ ቀድሞ ጥሪውን ያልሰማው ጭምር፤ እዚያ ማዶ ምን አለ ሲል ጆሮውን ይቀስራል፤ ይህ የኔ እምነት ብቻ ሳይሆን፤ በልምድ ያገኘሁትና፤ አሁንም የሚታይ ነው።
ሰለማተብ መበጠስና ስለክርስትና መነሳት ባነሳሁት ላይ እመለስበታለሁ እንዳልኩት ተመልሻለሁ፤ በዛሬዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ አንድነት የሚሏቸው አነጋገሮች በተወሰኑ የየዘውጋቸውን መብት እናስጠብቃለን በሚል ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ አካባቢ ጉሮሮ የመከርከር ጠባይ ያላቸው መሆናቸውን አሌ ማለት ይከብደኛል። – አንድ ትዝ የሚለኝ ነገር፤ ዶ/ር መርራ ጉዲና ጀርመን ሃገር አንድ ማህበራዊ ስብሰባ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ሁኔታ ንግግር እንዲያደርጉ ጋብዣቸው ንግግሩን ካደረጉ በሁዋላ፤ ስላደረጉት ንግግርና ሌላም ሌላም ለብቻችን ቁጭ ብለን ስንጨዋወት፤ የኢትዮጵያዊነቱና የተያያዙ ጉዳዮች ተነስተው ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ፤ ወዘተ … እያልኩ ስንጫጫባቸው ይመስለኛል፤ እንደመሰልቸት ብለው፤ „እናንተ ( እናንተ የሚለው የተቀየረ ስም ነው) እኮ የኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያ አንድነት ችግር የለባችሁም፤ እኛ ሰፈር ግን ችግር አለ።“ ያሉኝን አስታውሳለሁ። – ከእነዚህ ንቅናቄዎች ውስጥ ደግሞ „እንገነጠላለን“ ይላሉ የሚልም አለ። ሕብረት እንፍጠር ብለው ለሚነሱ ሌሎች ወገኖች እንዲህ ያለ ጥያቄ የሚያነሳን ዓይኑን አያሳየኝ ይሉና ለመተባበር መጀመሪያ ይህንን አላማሕን ሰርዘህ፤ ያንን አቋምህን ትተህ ነው ካንተ ጋር የምነጋገረው ይላሉ፤ በበኩሌ የዚህ ዓይነቱን ጥያቄ ማቅረብ ማለት በተዘዋዋሪ እራስህን አጥፋ እንደማለት አድርጌ ነው የምወስደው፤ ምክንያቱም ድርጀቱ ያለአላማ፤ አላማው ደግሞ ያለድርጅቱ ህልውና ሊኖራቸው ስለማይችሉ ጥያቄው ፉርሽ ነው ማለት ነው።
እንደኔ ከነጻ አውጭዎቹ የሚጠበቀው እንዲሁ አየር ላይ የተነሳፈፉ ሳይሆኑ፤ የሚኖሩት እዚቺው ኢትዮጵያ በምትባለው ጥላ ስር መሆናቸውን፤ በዚህ ጥላ ስር የተጠለሉት እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ሚሊዎኖችም እነደሆኑ፤ በዚያውም ልክ ሕይወታቸው ከሌላው ጋር በብዙ ድር የተሳሰረ መሆኑን፤ ባሁኑ ሰዓት ሀገሪቱና ሕዝቧ ላይ ተንሰራፍቶ በሚገኘው ዘረኛ ስርዓት ስር የሚማቅቁ መሆናቸውን፤ እነሱም የዚህ የአጥፍቶ አጥፊ ሥርዓት ሰለባ መሆናቸውን – ይሄኛውን እያረጋገጡጥ እንዳሉ ግልጽ ነው – መቀበል፤ በወዲህ በኩል ደግሞ ልገንጠል ብሎ ጥያቄ ማንሳት ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የሰብአዊ መብትም ጥያቄ መሆኑ ታውቆ፤ የዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ደግሞ በዴሞክራሲ መፈታት ስለሚገባውና ስለሚቻልም „ተገንጣዮች“ ችግራቸው በዴሞክራሲ የሚፈታ መሆኑን በማስረዳት ለጋራ ትግሉ ተባባሪ እንዲሆኑ መጋበዝ፤ በዘውግ ንቅናቄ ውስጥ ያሉ ዴሞክራቶች ይህንን አይቀበሉትም የሚል እምነት የለኝም። ይቻላል ብዬም አምናለሁ። ጥያቄው እንዴት የሚለው እንደሆነም ግልጽ ነው። በኔ እምነት ብዙ የሚከብድ አይደለም። የሚጠይቀው ዋና ጉዳይ ቢኖር በሁለቱም ወገን የዴሞክራሲ አርበኛ ሆኖ መገኘትን ብቻ ነው። በስርዟ ላይ እመለስባታለሁ፤ ወደሚከተለው ላግድም፤
ዴሞክራሲ በተግባር – ይህቺ ቋንቋ ከቪኦኤ በትውስት የተገኘች ነች – ዴሞክረሲያዊ ጥያቄን በዴሞክራሲ ለመፍታት በመጀመሪያ ዴሞክራሲ እራሱ ረጋ ብሎ የሚኖርበት መቀመጫ ቦታ ያስፈልገዋል። ዛሬ ታዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ ቦታ ሁሉ ታጥሮበት፤ መተናፈሻ አጥቶ እንደሚገኝ እናውቃለን፤ እንዲህ ከሆነ ታዲያ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄያችንን በዴሞክራሲ ለመፍታት ከተስማማን፤ ዛሬ ነገ ሳንል ያሉንን ጥያቄዎች(ፐሮግራሞች) ጉዳት እንዳይደርሰባቸው በጠንካራ ካርቶን አሽገን አስቀምጠን፤ ዛሬ ወያኔን ዙሪያውን ከብበን ወደየራሳችን መጎተቱን አቁመን፤ ወደ አንድ አቅጣጫ ጎትተን ጥለን ቦታውን ከወያኔ ጉጀሌ መፈንጫነት የዴሞክራሲ መናኸሪያ ማድረግና ተደራጅተው ወያኔውን በማስወገድ የተሳተፉት ብቻ ሳይሆኑ፤ ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው የህብረተሰብ ተወካዮችን አካትቶ በሚቋቋም የሽግግር መንግሰት አማካይነት ወያኔ በሱ ሽንጥ ልክ የሰፋውን ሕገ-መንግሥት በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሽንጥ ልክ በተሰፋ ሕገመንግስት ተክቶ፤ በሱ መተዳደር መጀመር፤ እዚህ ከተደረሰ ስለሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ገብቼ ላሰለቻችሁ አልፈልግም። ምክንያቱም ያሰመርኩበት ደረጃ እስከሚደረስ ድረስ በሚደረገው ጉዞ በዙ ዳገትና ቁልቁለት ተወጥቶ ተወርዷልና፤ በዚያወም ልክ ብዙ ጉዳዮች ቀደም ብለው ፍጻሜ ስለማግኘታቸው ጥርጥር አይኖርም።
የዴሞክራሲ አርበኛ ሆኖ መገኘትን አመለስባታለሁ እንዳልኩት፤ የምለውን ልበልና ከዚህ ሰፈር ልውጣ፤ ግንዛቤዬ፤- „ተገንጣይ ሃይል“ በሚለው ትይዩ የቆመው „የአንድነት ሃይል“ ነው። በነዚህ ሁለት ሃይሎች ዘንድ ዴሞክራሲ የሚፈራበት („ፈ“ ን አጥብቃችሁ አንብቡ) ጉዳይ አለ። የአንድነት ሃይሉ „አንድነት“ ወደመንግስተሰማያት የሚያስገባው መንገድ እሱ ብቻ ነው የሚል የማይነቃነቅ ዕምነት ስለያዘ፤ በዴሞክራሲ አማካይነትስ ቢሆን፤ እገዜሩ/አላሁ የሚሰሩት ስለማይተወቅ፤ መገንጠል ቢመጣ ምን ይውጠኛል የሚል ስጋት አለው። „ተገንጣይ ሃይል“ ደግሞ የዚያች እጁ የሚያደረጋት ቀበሌ ገዥ ሆኖ በዓለም አቀፍ መድረክ ብቅ ማለት ቅሪት በውስጡ ሰለሚኖር፤ ይህ ምኞት ደግሞ በዴሞክራሲ መንገድ ስለመሟላቱ እርግጠኛ ያለመሆን ስጋት አለው። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ „የዴሞክራሲ አርበኝነት“ ያስፈልጋል የምለው፤ ባጭር ቋንቋ፤ በዴሞክራሲ የተገኙ ውጤቶችን ለመቀበል በቁርጠኝነት መቆም ማለት ነው። ምክር፤- ለ“ተገንጣይ“ ታጋይ! ዛሬ ለመገንጠል ብለህ ብረት አንግበህ በረሃ ለበረሃ መንከራተትህ፤ እንደ አውሬ መታደንህ፤ ይቀርና፤ ዴሞክረሲ በሰፈነባት ኢትዮጵያ ውስጥ ከመገንጠሉ ፖለቲካ ትግልህ ጎን ለጎን በህዝብህ መሃል ሆነህ፤ አገርህን፤ ሰፈርህን፤ መንደርህን እያለማህ አንተም እየለማህ፤ እየወለድክ እየከበድከ የምታደርገው ትግል ስለሆነና፤ ይህ የሰለጠነ አካሄድም እንደሆነ መገንዘብ አስቸጋሪ ሳይሆንብህ፤ ቀደም ብዬ እንደጠቆምኩት፤ ዛሬ ያነገብካትን ፕሮግራም አመቺ በሆነ ቦታ አሽገህ አስቀምጠህ፤ ነገ ዛሬ ሳትል ዛሬውኑ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን በማስፈኑ ስራ ተሳተፍ! „የአንድነት“ ሃይልም የዜጎች ሃይል እንደመሆንህ ከአንድ የዘውግ ስብስብ የከበደ ሃላፊነት እንዳለብህ ተገንዝበህ ያህንን ሃላፊነት የመወጣት ብቃት እንዳለህ ማሳየት ሊቸግርህ አይገባም።
እስከዚህ ድረስ ሕብረትን በተመለከተ ካለፉ ትብብሮች በክፉም ሆን በደጉ ምን መማር እንደሚቻል፤ ተቃዋሚዎች ለትብብር ሲዘጋጁ ቢያጤኗቸው ይጠቅማል የሚሉ ጉዳዮችን በመጠቆም፤ ትብብሩ ሁሉንም ያቀፈ ይሆናል ለሚለውም አማራጭ አካሄዶችን ለማመላከት ሙከራ በማድረግ፤ ከኢትዮጵያ ሁኔታ በመነሳት ለህብረት የሚሰባሰቡ ሃይሎች ሰለዴሞክራሲ ሚና ሰለሚኖራቸው ዕይታና ተመሳሳይ ነጥቦች ላይ ያለኝን ግንዛቤን ነማንሸራሸር ሞክሬአለሁ። እነዚህ በህብረት ለመሰባሰብ ጠቃሚ ናቸው ያልኳቸውን ሃሳቦች ግንዛቤ በማስገባት በዲያስፖራ የሚቀናጀው አጣዳፊው የትብብረ ሃይል በሚከተለው መልክ ቢቀናጅ ፍሬአማ ስራ ሊሰራ ይችላል የሚል እምነት አለኝ።
የወያኔን የባርነት አገዛዝ ለማስወገድ የሚደራጅ ሃይል በርግጥም ታግሎ ለማታገል የወሰነ ከሆነ፤ በሃገር ውስጥ ሕልውናውን አሳውቆ ከሕዝብ መሃል በመገኘት ትግሉን መምራት፤ „በሪሞት ኮነትሮል እመራለሁ ብሎ አለመቃጣት፤ ይህ የማይሳከ ከሆነ ደግሞ፤ ተሳክቶለት በሃገር ውስጥ ታግሎ በማታገል የባርነቱ አገዛዝ እንዲያበቃ ለማድረግ ደፋ ቀና የሚለውን ሃቀኛ ታጋይ ሃይል አጢኖ በስንቅ፤ በትጥቅና በሌላ ሌላም አቅጣጨ በሚደረጉ ድጋፎች ትግሉን ለማጠናከር ተደራጅቶ መንቀሳቀስ። እዚህ ላይም አንድ ምልከታ አለኝ። በተለይ ሁለተኛውን አቅጣጫ በተመለከተ፤ ቅኝቱ ከወያኔው ባህርይ አቅጣቻ መሆን ስላለበት፤ ከሁሉ አስቀድሞ ከሀገር ቤቱ ሃይል ጋር በሚያስማማ ቋንቋ መግባባትን መፍጠር፤ (ወያኔን የሚያሸብሩ ቋንቋዎች አለመጠቀም)፤ ከማንኛውም መሳሪያ አንጋች ጋር ብቻ ሳይሆን፤ ተመሳሳይ ሃሳብ የሚያወጣ የሚያወርድ ነው ተብሎ ከሚጠረጠር ጋር ጭምር ንክኪ እንደይኖር ጥንቃቄ እንደይኖር ማድረግ፤ ይህንን የምለው ያለምክንያት አይደለም። ወያኔን እንደምንታዘበው፤ የራሱም ጥላ ጭምር ስለሚያስሸብረው፤ ተሸብሮ እንዳያሸብርና በሃገር ቤቱና በዲያስፖራው መካከል ያለውን ግንኙነት እንዳያደናቅፍ ለማለት ነው። ጸረ-ሽብር ሕጉ „የንጉሡን ጠላት የራቀውን በመድፍ የቀረበውን በሰይፍ“ እንደሚሉት በቅርብም በሩቅም አገልግሎት ላይ ስለሚውል፤ ስህተት እንዳይፈጸም ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው። በመጨረሻም ጥያቄ አለኝ።
ትግል የሚደረገው ምን ለመድረስ ነው? እስከዛሬ በነበረው አካሄድ ሰላማዊና ሕጋዊ ታጋዮች – የምርጫ ፓረቲዎች – ጥርሳቸውን ነከሰው በያአምስት አመቱ በሚደረገው የምርጫ ግርግር ተሳትፈው የወያኔ የዘውድ በዓል ከተከበረ በዃላ በዚህም በዚያም በምርጫው ላይ የተፈጸመ ደባዎችን መዝግበን፤ ለምርጫ ቦረድ አቅርበን፤ ተወዳዳሪዎቻችን ተደብድበውብን፤ ታስረውብን፤ ታዘቢዎቻችን ተበርረውብን ወዘተ … የበደሉ ዓይነት ተዘርዝሮ አያለቅም፤ እያሉ ይተርኩልናል፤ ዱሮውንም ቢሆን፤ ምረጫው ውስጥ የገባነው ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ ይሆናል ብለን ሳይሆን፤ አንዱ የውጭ መንግስታት ጽንፈኞች የሉናል ብለን ነው፤ ሲል ሌላው ደግሞ ምርጫ ሰው እንደሚለው መወዳደሪያ ሳይሆን፤ መታገያ ስለሆነ ነው የገባነው፤ አንድ ጊዜ ደግሞ የሰማነው፤ ከዚሁ ከምረጫ ጋር የተያያዘ ፊረማ ተፈርሞ የፈረምነው የውጭ መንግስቶች ኮረኩመውን ነው የሚል ሮሮ ሁሉ ሰምተናል። ከምርጫው በሁዋላ ደግሞ – ምርጫውን አያሸንፉ እንጂ የመረጣቸው ምንም ሰው የለም ማለት ግን አይደለምና – እኛን የመረጡ ደጋፊዎቻችንን ገዠው ፓረቲ እኔን ለምን አልመረጣችሁም እያለ ያሰቃያቸዋል፤ ከመሬታቸው ያፈናቅላቸዋል፤ – ምርጫ አለማሸነፋቸው አንሶ ለመራጮቻቸው ጦስ የመሆን ጣጣ ሁሉ አለባቸው። – መቼም ላይችል አይሰጠው ማለት ነው እንጂ መከራው ብዙ ነው። በመጨረሻው ምርጫ ይልቅ በጣም ስለመረራቸው መሰለኝ ቁርጥ አድረገው ምርጫውን አንቀበለውም አሉና “አፈር አስበሉት።” አልፎ አልፎም ምርጫው ነጻና ፍታዊ ቢሆን ያለጥርጥረ እናሸንፍ ነበር የሚሉትም ነገር አለ። እዚህ ላይ ጥሩ ነገር መጣ። „ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ ቢሆን“ የሚለው ነገር፤ ይህን በተመለከተ አጠቃላይ ሕዝብን አንድ ያደረገ ድምዳሜ አለ። ይኸውም በኢትዮጵያ ውስጥ የብዙሃን ፓረቲ ስርዓት የሚስተናገድበትን አካሄድ ተከትሎ ዛሬ ባለው የገዥ ፓርቲ አዘጋጅነት ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ መካሄድ ይችላል ብሎ ማሰብ „የህልም እንጀራ“ ነው የሚለው ነው። ይሄ ወዴት ነው የሚወስደን? ካልን፤ በወያኔ አገዛዝ ስር በምትገኘው ኢትዮጵያ የሚደረገው ፋይዳቢስ የመረጫ ውጣ ውረድ ቀርቶ፤ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ ለሚያስችል ነጻነት መታገልን አስፈላጊ ነው ወደሚለው ይሆናል። ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ ለሚያስችል ነጻነት ስንል ምን ማለታችን ነው? መልስ፤- መራጩ ነጻ መሆን አለበት ማለት ነው። እንደዚያ ካልን ታዲያ ደግሞ የመራጮች ሁሉ ትግል የሚሆነው የነጻነት ትግል ነው ማለት ነው። ለዛሬ እዚች ላይ ላብቃ፤ ነገ በዚሁ የነጻነት ትግል ላይ አቅሜ በፈቀደው ያለኝን ሁሉ አሟጥጬ ይዤ እቀርባለሁ፤ የዚያው ሰው ይበለን።
ጣስው አሰፋ
tassat@t-online.de
No comments:
Post a Comment