ኦሮሚያ የመላው ኢትዮጵያዊ መላው ኢትዮጵያም የሁሉም ኦሮሞ ናት! -አበበ ቶላ (አቤ ቶክቻው )
ከጃዋር ሃሳብ የማልስማማበት እና የምስማማበትን ስለመለየት፤
የኛ ሀገር ፖለቲካ የቡዳ ፖለቲካ ነው እንዳሉት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና አሁንም ድጋሚ ፖለቲካችንን ቡዳ ሊበላው ነው መሰል ጣት መቀሳሰር እና እነ እንትና እነ እንትና መባባል ልንጀምር ይመስላል… ምናባቱ እንግዲህ ካልደፈረሰ አይጠራም…
ጃዋር ሰሞኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በዋሽንግተን ዲሲ ካደረጉት ንግግር በኋላ በአራት ጉድዮች ላይ አስተያየት ሰጥቷል። ካነሳቸው ሃሳቦች ውስጥ በተወሰነ ደረጃ የምስማማባቸው ሃሳቦች ቢኖሩኝም በርካታ የማልስማማባቸው ሃሳቦችም አሉ። ከሁሉ ከሁሉ ግን በትልቁ የማልስማማበት፤ ኦሮሞ በሙሉ ተመሳሳይ ነው ብሎ ሁሉንም ኦሮሞዎች በአንድ ቅርጫት ውስጥ ለማስቀመጥ የሚሞክረው ነገር ሁልጊዜም በጣም የሚያበሳጨኝ ነው። (እነደሱ አባባል እርሱ በሚለው የማይስማማ ኦሮሞ ኦሮሞ አይደለም (ሲያናድድ!))
እኛ ኦሮሞዎች ሰዎች ነን። ምንም እንኳ የሰው ልጆች በሙሉ በፍጥረታቸው አንድ ናቸው ቢባልም፤ በአስተሳሰብ እና በአመለካከት ግን አንድ አይነት መሆን አይችሉም። ሁሉም ሰው የየራሱ አመለካከት እንዳለው ሁሉ፤ ኦሮሞዎችም የየራሳችን አመለካከት አለን። እኛ በፋብሪካ የተመረትን ሮቦቶች አይደለንም። የተለያየ አመለካከት የተለያየ አስተሳሰብ፣ የተለያየ የምፍትሄ አቅጣጫ፣ የተለያየ ምኞት እና ፍላጎት ያለን ሰዎች ነን። ይሄ ሰው በመሆናችን የተሰጠንም ጸጋ ነው። ጃዋር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፤ ‘’ከለዘብተኛ ኦሮሞዎች ጋር አብረን እየሰራን ነው’’ ማለቱን ተከትሎ በኦሮሞ ውስጥ ለዘብተኛ አክራሪ የለም ብሎ ይሞግተናል። ሞልቶ! በሁሉም ማህበረሰብ ውስጥ በአንድ ጉዳይ ላይ አክራሪ እና ለዘብተኛ እንዳለው ሁሉ በኦሮሞ ማህበረሰብ ውስጥም ይሄ አለ። ወደፊትም ይኖራል።
ለምሳሌ ያክልም፤ ራሱ ከጃዋር እና የመሳሰሉት ኦሮሚያ የኦሮሞ ናት ሲሉን እየሰማን ነው። በነገራችን ላይ የ ‘የ’ እና የ ’ለ’ ነገር በትርጉሙ ላይ ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም። ኦሮሚያ ለኦሮሞ ናት ተባለም ኦሮሚያ የኦሮሞ ናት ተባለም ምንም የፍቺ ልዩነት የላቸውም። (ወዳጃችን ጃዋር ኦሮሚያ ለኦሮሞ ናት አላልኩም ኦሮሚያ የኦሮሞ ናት ነው ያልኩት ሲል አይቼ ባውጠነጥን ባውጠነጥን ምንም ልዩነት አላየሁበትም።) የሆነው ሆኖ ጃዋር እንደሚያስበው ይሄ አስተሳሰብ የሁሉም ኦሮሞዎች አስተሳሰብ ነው። በኦሮሚያ የተነሳው ተቃውሞም ዋና ሃሳብ ይሄ ነው ይለናል።
እኛ ጃዋር ኦሮሞ አይደለም ብለን አንከራከርም። ነገር ግን እርሱ ብቻ ሳይሆን እኛም ኦሮሞዎች ነን። እንደኛ አስተሳሰብ ኦሮሚያ የመላው ኢትዮጵያዊ መላው ኢትዮጵያም የኦሮሞ ናት። እንኳንስ ኦሮሚያ እና ብሪታኒያ እና አሜሪካንን የመሳሰሉት ሀገሮች እንኳን የብርትሾች እና የአሜሪካኖች አይደሉም፤ የሁላችንም ናቸው እንጂ! (ምንም እንኳ እንደ ዶናልድ ትራምፕ አይነት ቀውሶች ይሄ አሳብ ቅዠት ቢመስላቸውም አሁን አለም ባለችበት ደረጃ ግን ማንም ሰው የሀገሪቱን ህግ እና ደንብ አክብሮ እስከኖረ ድረስ ሁሉም ሀገር የሁሉም ነው። በዛ መሰረት ነው ጃዋርም ሆነ እኔ በአሜሪካ እና እንግሊዝ የምንኖረው!)
በኦሮሚያ ክልል የተነሳው ተቃውሞ ዋና ማጠንጠኛ ኦሮሞ ዘመዶቻችን አንድም በገዛ ወገኖቻቸው፤ (በኦህዴድ አባላት) አንድም ከፌደራል በሚሄዱት እነ አባይ ጸሃዬ የሚደርስባቸው ስር የሰደደ በደል ሞልቶ ስለፈሰሰ ነው፤ እንጂ ኦሮሚያ ለኦሮሞ ትሁን በሚል አይደለም። እንደዚ የሚሉ ቢኖሩም እንኳ በኔ አስተሳሰብ ስህተት ውስጥ እየገቡ ነው። ማንም ሰው በአግባቡ እና በደንቡ መሰረት እስከተንቀሳቀሰ ድረስ (በእግር ኳስ ቋንቋ ፌር ፕሌይ እስከተጫወተ) ሁሉም ሃገር የርሱ ነው። ኦሮሚያን ጨምሮ። ብቻ ገበሬዎችን ያለአግባብ አያፈናቅል። ብቻ ገበሬውን በገዛ መሬቱ ላይ ከአምራችነት ወደ ዘበኛነት አይቀይር እንጂ!
አሁን ኢህአዴግ እየፈጸመ ያለው ዘረፋ በኦሮሚያ ላይ ነውር ነው! በትግራይም ላይ ሲፈጸም ብልግና ነው! በአማራ ክልልም ሲደረግ ጸያፍ ነው።
ይልቅስ ጃዋር በብሄር ስለመደራጀት ያነሳው ነገር ላይ እስማማለሁ። ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ይሄ የኔ አመለካከት ነው ብለው በነገሩን መሰረት የብሄር ወይም ዘውጌ ፖለቲካዊ ስብስብ አይመስጣቸውም ብቻ ሳይሆን አፍራሽ ነው ሲሉም ኮንነውታል። በርግጥ ‘’እባብን ያየ በልጥ ይደነግጣል’’ እንዲሉ አሁን አሁን እየሆነ እንዳለው ነገር የብሄር አደረጃጀቶች የሚያስፈራ ነገር አላቸው። ቢሆንም ግን አፍራሽ ናቸው ብሎ ድምዳሜ ላይ መድረስ ከባድ ነው። ሰዎች በመሰላቸው መልኩ የመደራቸት እና የመታገል መብታቸው በጽኑ ሊከበር ይገባል። በሰለጠኑት ሃገራት በብሄር የተደራጁ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲ ግንባታ አፍራሽ ሚና ሲጫወቱ አላየንም። እንደ ምሳሌም ስኮቲሽ ናሽናል ፓርቲ በ ዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲካ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ ማየት ይቻላል። እኛም ሃገር ቢሆን ፖለቲካችን አፍራሽ ሚና የሚኖረው ከአያያዛችን እንጂ ከአደረጃጀታችን አይመስለኝም። (እንደውም ከቤተሰብ ጉባኤ አንስቶ ብብሄር መደራጀት ተፈጥሯዊ ነው ብዬ አስባለሁ…. አፍራሽ የሚሆነው ክኔ ብሄር በላይ ላሳር ማለት ሲጀመር ነው! እሱን የሚገራ ሀገር አቀፍ ህግ መኖር ይኖርበታል!)
በኢሳት ቴሌቪዥን የኦሮምኛ ቋንቋ ዝግጅቶች መጀመራቸውን አስመልክቶ የኦሮሞን ህዝብ ትግል ለማዳከም ነው የሚለን ጃዋር ከላይ እንዳነሳሁት በኢሳት ቴሌቪዥን ላይ በአዘጋጅነት የሚሰሩትን ኦሮሞዎች ስለ ኦሮሞ ጉዳይ የማያስቡ ራሱን ደግሞ ከማንም በላይ ለኦሮሞ አሳቢ የማድረግ አዝማሚያ ነው ያየሁበት… ይሄኔ ይቺ ሰውዬ ቀስ ብላ እኔንም ለኦሮሞ አታስብም ትለኝ ይሆናል እኮ ብዬ ስቄ ትቼዋለሁ!
እያልኩ ልጻፍ ልተወው… በማለት እያሰብኩ ነው….
No comments:
Post a Comment