Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, February 20, 2016

ኢሳት: ጋዜጠኛ ሰለሞን ከበደና ሌሎች ሙስሊሞች ጥፋተኞች ተባሉ

ጋዜጠኛ ሰለሞን ከበደና ሌሎች ሙስሊሞች ጥፋተኞች ተባሉ
በአማን አሰፋ መዝገብ በሽብርተኝነት ወንጀል ከተከሰሱት መካከል 24ቱ ጥፋተኞች ሲባሉ፣ 4ቱ ብቻ በነጻ ተለቀዋል።
ጥፋተኞች ከተባሉት መካከል የሙስሊም ጉዳዮች መጽሄት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ሰለሞን ከበደ ይገኝበታል። ተከሳሾቹ እስላማዊ መንግስት የማቋቋም ፍላጎት እንዳላቸው፣ በውጭ ከሚገኙ አሸባሪ ድርጀቶች ጋር ግንኙነት ነበራቸው የሚሉና ሌሎችም ክሶች ቀርበውባቸዋል። ተከሳሾች እጅግ በርካታ የሰነድ ማስረጃዎችን ቢያቀርቡም ፍርድ ቤት አልሰማቸውም።
ጋዜጠኛ ሰሎሞን በእስር ቤት ውስጥ በድብደባ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር ይታወሳል። በተመሳሳይ መንገድ የተከሰሰው ሌላው ጋዜጠኛ ዮሴፍ ጌታቸው 7 አመት ተፍርዶበት በእስር ላይ ይገኛል።
በሌላ በኩል ደግሞ እስር ቤት ፍርድ ቤት ነፃ ያላቸውን እስረኞች አለቅም ብሎአል።
በሽብር ተከሰው በእስር ሲማቅቁ የነበሩት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጠቅላይ ፍርድ ቤት ነጻ ብሎ ቢያሰናብታቸውም እስር ቤቱ ሊለቃቸው ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።
ዛሬ የካቲት 7 ቀን 2008 ዓ.ም ፍ/ቤት የቀረቡት አቶ ሀብታሙ አያሌው፣ አቶ ዳንኤል ሺበሺ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ የሽዋስ አሰፋ እና መምህር አብርሃም ሰሎሞን ባለፈው ሳምንት ከቤታችሁ መጥታችሁ ችሎት ትቀርባላችሁ ተብለው የነበረ ቢሆንም፣ የፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ተጥሶ ሁሉም ከቤታቸው ሳይሆን ከእስር ቤት ችሎት ቀርበዋል፡፡
አቃቤ ህግ የካቲት 5 ቀን 2008 ዓ.ም ከደኅንነት መስሪያ ቤት ተላከልኝ ያለውን ማስረጃ ኮፒውን ለተከሳሾች ማድረስ አልቻለም፡፡ በዚህም ኮፒውን በችሎት ለይግባኝ መልስ ሰጭዎች ለማድረስ ለየካቲት 9 ቀን 2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶታል፡፡
ፍርድ ቤቱ ይግባኝ መልስ ሰጭዎች እስካሁን ከእስር አለመፈታታቸውን በተመለከተ እስር ቤቱን ጠይቋል፡፡ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ ዳንኤል ሺበሽ፣ አቶ አብርሃ ደስታና አቶ የሽዋስ አሰፋ የችሎት መድፈር ቅጣት አለመጨረሳቸውን ላለመፍታቱ በምክንያትነት አቅርቧል፡፡
ሦስቱ ይግባኝ መልስ ሰጭዎች በበኩላቸው የችሎት መድፈር ቅጣታቸውን እንደጨረሱ ተናግረዋል፡፡ አቶ የሺዋስ አሰፋ ቅጣታቸውን በተመለከተ፣ ‹‹ችሎት መድፈር የተቀጣነው ሁለታችን የሽዋስና ዳንኤል 14 ወራት፣ እና አብርሃ 16 ወራት እስር ነው፡፡ እኛ ከታሰርን 1 አመት ከ9 ወራት ሆኖናል፡፡ ስለዚህ እስራችንን ጨርሰናል ብሏል፡፡
ማረሚያ ቤቱ ቅጣቱ የሚታሰበው ችሎት መድፈሩ ከተፈጸመበት ቀን ነው ወይስ እጃቸው ከተያዘበት አንስቶ የሚለው ግልጽ አልሆነልኝም ብሏል።
በቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኙት አቶ ሀብታሙ አያሌውና መምህር አብርሃም ሰለሞን ምንም አይነት ቅጣት ባይኖርባቸውም እስካሁን ከእስር አልተፈቱም። የማረሚያ ቤቱ ተወካይ ‹‹የፍ/ቤቱ ትዕዛዝ ግልጽ አልሆነልንም›› የሚል መልስ ሲሰጥ ፣ ዳኛ ዳኜ መላኩ ደግሞ ‹‹እናንተ ምክንያቱ አያገባችሁም፤ መፍታት አለባችሁ። ይህ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እና ህገ መንግስቱን አለማክበር ነው›› በማለት ዛሬውኑ ከእስር እንዲፈቱ ሲሉ አዝዘዋል፡፡
እነ አብርሃ ደስታ የእስር ቤት አስተዳደሩ በቤተሰቦቻቸው እና በጓደኞቻቸው እንዲጠየቁ እንዲያደርግ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው በድጋሜ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ለምን እንደታሰርንም ለምን እንደምንፈታም አሳሪው አካል ያውቃል፡፡ አሁን እኛ የምንጠይቀው፣ መቼም እንፈታ መቼ ታስረን እያለን ሰዎች እንዲጠይቁን ትዕዛዝ እንዲሰጥልንና የትዕዛዙን መፈጸም ክትትል እንዲደረግልን ነው›› ሲል አቶ ዳንኤል ሺበሺ መጠየቁን ነገረ ኢትዮጵያ ዘግቧል።
ኢሳት

No comments:

Post a Comment

wanted officials