Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, February 29, 2016

በኦሮምያ ተከታታይ ተቃውሞዎች እንደሚቀጥሉ ከያካባቢው የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል

በኦሮምያ ተከታታይ ተቃውሞዎች እንደሚቀጥሉ ከያካባቢው የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል

የካቲት ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- 
ገዢው ፓርቲ የአጋዚ ወታደሮችን በየቦታው አሰማርቶ ግድያና እስሩን አጠንክሮ ቢቀጥልም፣ በሚቀጥሉት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎችን ለማድረግ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው። በተለይ የሻኪሶ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ የጉጂ ዞን አካባቢዎች ጠንካራ ተቃውሞች እንደሚካሄዱ የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በቦረና ዞንም እንዲሁ ተቃውሞዎች እንደሚቀጥሉ የአካባቢዎች ነዋሪዎች ተናግረዋል። በምእራብ ሃረርጌ ዛሬም የተቃውሞ ሰልፍ ሲካሄድ ውሎአል።
በጉጂ እና በቦረና ዞኖች ካለፉት ሶስት ሳምንታት ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ታስረዋል። ብዙዎችም የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመከላከል ሲሉ ጫካ ገብተዋል። ይሁን እንጅ የተለያዩ የማህበረሰቡ አባላት ባደረጉት ውይይት ተቃውሞአቸውን አጠናክረው እንደሚገፉበት ስምምነት ላይ ደረሰዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ ከፍተኛ የሆነ የፍርሃት ድባብ መኖሩን ኤ ኤፍ ፒ ዘግቧል።
ክልሉ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን ባነገቡ ወታደሮች እና ተሽከርካሪዎች ተሞልቷል። በየአካባቢው የሚካሄደው ተከታታይ ፍተሻ እና እንግልት ነዋሪውን በእጅጉ አስመርሯል።
“በምሽት ብትወጣ ፣ ፖሊስ ያስርሃል። ወረቀቶችህንና ስልክን ይፈትሻሉ። ከተቃውሞው ጋር የተያያዙ ፎቶዎች ከተገኙብህ ከፍተኛ ችግር ላይ ትወድቃለህ። ” ሲል አንድ የጊንጪ ወጣት ለኤ ኤፍ ፒ ተናግሯል። ሌላ እናት ደግሞ “ለልጆቼ እፈራለሁ። ሌሊት መተኛት አቁሜአለሁ። ኑሮአችን ሲኦል ሆኗል። ህይወት ትርጉም አጥቷል። ” ማለታቸውን የዜና ድርጅቱ ዘግቧል። በአምቦ አንዳንድ ሱቆች ቢከፈቱም፣ ትምርትቤቶችና ሆስፒታሎች ካለፉት 3 ወራት ጀምረው እንደተዘጉ ነው።
ኤፍ ፒ ያነጋገረው አንድ የባንክ ሰራተኞች ፣ በአምቦ “የፖሊስ ቁጥር ከኮብልስቶን ቁጥር ይበልጣል” ብለዋል።
የሁለት ልጆች እናት የሆኑ ሴት፣ እነዚህ ወታደሮች የእኛን ቋንቋ አይናገሩም። ከእነሱ ጋር መግባባት አልቻልም። የእነሱ ብቸኛ ቋንቋ የጦር መሳሪያቸው ነው” ብለዋል።
በኦሮምያ የሚደርሰው ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲቆም የተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች በጋራ በመሆን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ጉባኤ ደብዳቤ ጽፈዋል። ድርጅቶቹ በጋራ በጻፉት ደብዳቤ በኦሮምያና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ዜጎች ላይ የሚወሰደው የሃይል እርምጃ እንዲቆም፣ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እንዲሁም ተቃውሞ ሲያሰሙ የታሰሩት በሙሉ እንዲፈቱ፣ የተፈጸሙትን ግድያዎች የሚመረምር ነጻና ገለልተኛ መርማሪ አካል እንዲወቋቋም፤ ሰብአዊ መብቶችን በመጣስ የሚወነጁ ባለስልጣት አለማቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ፍርድ ቤት እንዲዳኙ ጠይዋል።
ጥያቄውን በጋራ ያቀረቡት የሰብአዊ መብት ማህበር በኢትዮጵያ፣ ሲቪከስ፣ ሲቪል ራይትስ ዲፌንደርስ፣ ዲፌንድ ዲፌንደርስ፣ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ፕሮጀክት፣ ፍሮንት ላይን ዲፌንደር፣ ሂውማን ራይትስ ወች እንዲሁም አለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች ፌዴሬሽን ናቸው።
አሜሪካ፣ ኖርዌይና እንግሊዝ ዜጎቻቸው ወደ ተለያዩ የኦሮምያ አካባቢዎች እንዳይጓዙ አስጠንቅቀዋል።
የእንግሊዝ መንግስት ዜጎቹ ወደ ዝዋይ፣ አዳሚ ቱሉ፣ ምስራቅ ሸዋ፣ ሻሸመኔ፣ አርሲ ነገሌ፣ ሰራሮ፣ ኮፈሌ፣ ዶዶላ፣ ኮኮሳ ወረዳ እና ላንጋኖ እንዳይጓዙ ሲያስጠነቅቅ፣ የአሜሪካ መንግስት ደግሞ ዜጎቹ በሻሸመኔ ሞጆ መንገድና አምቦ መንገድ እንዳይጓዙ አስጠንቅቋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials