Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, February 19, 2016

ሰማያዊና መድረክ ከስዊድን የፓርላማ አባላት ጋር ተወያዩ

ሰማያዊና መድረክ ከስዊድን የፓርላማ አባላት ጋር ተወያዩ
የሰማያዊ እና የመድረክ ፓርቲዎች አመራሮች ከስዊድን የፓርላማ አባላት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት ተናግረዋል፡፡
የፓርቲዎቹ አመራሮች የሆኑት ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ፣ ኢ/ር ይልቃል ጌትነት እና ዶ/ር መረራ ጉዲና ከስዊድን ፓርላማ የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ልዑክ ጋር በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ዛሬ የካቲት 9/2008 ዓ.ም መወያየታቸው ታውቋል፡፡
የፓርቲ አመራሮቹ ከስዊድን ስድስት ፓርቲዎች ከተውጣጡ 11 የልዑካኑ አባላት ጋር በተወያዩበት ወቅት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተለይም በኦሮሚያ በተቀሰቀሰው የህዝብ ተቃውሞ እና በጋምቤላ ክልል ስለነበረው ግጭት ገለጻ አድርገውላቸዋል፡፡ አመራሮቹ ለተቃውሞ አደባባይ በወጣው ህዝብ ላይ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እየወሰዱት ያለውን እርምጃ በተመለከተም በውይይታቸው አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ በኢትዮጵያ የተቃውሞ ድምጽ የሚያሰሙ የፓርቲ አባላትን እና በነጻነት ስራቸውን በሚያከናውኑ ጋዜጠኞች ላይ እንዲሁም በአጠቃላይ ተቃውሞ በሚያሰማው ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው አፈና እየጨመረ መሆኑንና በሀገሪቱ ፓርላማም አንድም ተቃዋሚ ድምጽ የማይሰማበት መሆኑን እንደገለጹላቸው ታውቋል፡፡
የስዊድን ፓርላማ አባላትም የተቃዋሚ ፓርቲዎች እያደረጉት ስላለው የፖለቲካ እንቅስቃሴና በጋራ ስለሚሰሩበት ጉዳይ ጥያቄ አንስተው በፓርቲዎች አመራሮች ገለጻ እንደተደረገላቸው ኢ/ር ይልቃል ተናግረዋል፡፡
የስዊድን የፓርላማ አባላት ጠ/ሚ ኃ/ማርያም ደሳለኝን ጨምሮ ከተለያዩ የመንግስት አካላት ጋር እንደተወያዩም ለማወቅ ተችሏል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials