Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, February 22, 2016

“ ብሄራዊ መግባባት አጀንዳ ባለቤት አገኘ” – ጊሼይ ጊሻ


“ ብሄራዊ መግባባት አጀንዳ ባለቤት አገኘ” – ጊሼይ ጊሻ



በአቶ ኦባንግ ሜቶ የሚመራው    ሰሞኑን በአሜሪካን ስልቨር ስፕሪንግ ከተማ በጠራውና “ለመተማመን እንነጋገር” የሚል መሪ መፈክር በያዘው ስብሰባ ላይ ለመገኘት እድሉ አጋጥሞኝ ነበር ስብሰባው የጀመረው ከተባለበት ሰዓት “በባሕላችን መሠረት”  አንድ  ሰዓት ዘግይቶ  ቢሆንም ስብሰባው ላይ የተካሄዱት ቁምነገራም ሀሳቦች የስብሰባውን አርፍዶ መጀመር አላስታወሰኝም።
በስብሰባው ላይ ለመሳተፍ ከአውሮፓ ከአውስትራሊያና ከአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የመጡ ኢትዮጲያውያን አሁን ሀገራችን የምትገኝበት እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ እንቅልፍ ያሳጣቸውና የበኩላችንን ማድረግ አለብን ብለው የቆረጡና  ኢትዮጲያ የምንላት ሀገራችንን ከሞላ ጎደል የሚወክሉ ተሳታፊዎች ነበሩ። በርግጥም ኢትዮጲያ ያለችበትን ሁኔታና በውስጧ ያለውን ውስብስብ ችግር ያለምንም አድርባይነትና አስመሳይነት የሚታያቸውን መግለጽ የሚችሉ  ከዘረኝነት ይልቅ ሰውነት ይቅደም  Humanity Before ethnicity የሚለውን ትልቅ መሪ ቃል በስብዕናቸው ያነገቡ ኢትዮጲያውያኖች ነበሩ። ለዚህም መገለጫው እያንዳንዱ ተናጋሪ ስሜቱን በእልህ በቁጭት በዕንባ አጅቦ ሲያቀርበው መታየቱና በተለይም የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ አባንግ ሜቶ ዛሬ በሀገራችን በአምባገነኑ መንግስት እየተካሄደ ያለውን የንጹኋን ዜጎች እልቂት እያንዳንዳችን የራሳችን ወንድም እህት አጎት አክስት ቢሆኑ ኖሮ ምን ይሰማን ይሆን ብለው በጥቁር ፊታቸው ላይ ይፈስ የነበረውን እንባ የተመለከተ ታዳሚ እንዲሁም ”  እናቶች ወንድሞች እህቶች ትውልድን እናድን፤ በሀገራችን ደም መፋሰስ ይብቃ! ብላ በሰሞኑ ግድያ ልጇን እንዳጣች እናት እንባዋን ያጎረፈችውን ወ/ሮ ሰዋሰውን የተመለከተ ወይም ያዳመጠ ሰው የሆነ ሰው በውስጡ ያላለቀሰ ያለ አይመስለኝም። ስብሰባው የፖለቲከኞች ስብሰባ አልነበረም ወይም “ድርጅቴ ነጻ ያወጣችሁዋል” ብሎ ተስፋ የሚሰጥ ተናጋሪ ያለበት አልነበረም ወይም  ሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ጥዬ ዲሞክራሲ በኢትዮጲያ አሰፍናለሁ የሚል አልነበረም። የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ግን ነበሩ። ስብሰባውን ለየት የሚያደርገውም የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች ለአንዲት ሀገር ኢትዮጲያ ጥቅም ለህዝቦቹ ደህንነት ፍትህና እኩልነት የራሳቸውን አመለካከት ለሀገር ጥቅም አንበርክከው የተገኙበት መድረክ ነበር።
የብዙዎች የተቃዋሚ ፖለቲከኞቻችን ከአምባገነኑ መንግስት ጋር ካላቸው  ቂም በተጨማሪ እርስ በርሳቸውም ከሚያናቁራቸውና እልባት ያልተገኘለት መከፋፈል የፖለቲካ ስልጣን ጥያቄና  የወቅቱ  የፖለቲካ ጦርነት በኢትዮጲያና  ኢትዮጲያዊነት ዙሪያ በማንነት ጥያቄዎች ላይ መሆኑን የየተገነዘቡት እነዚህ  ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን በፍቅርና በመነጋገር በመወያየት ማንነትን ያከበረ ኢትዮጲችንን በሚገባ ስለዋታል።
ከተናጋሪዎቹ አስተያየቶች ውስጥ ለአብነት ከላስቬጋስ የመጣው አቶ ሮባ “ታሪክን ለባለታሪኮች ለባለሙያውች መተውና ነገር ግን ዛሬም ባለንበት ሁኔታ እኛ የምንሠራው ታሪክ ነገ በትውልድ ተወቃሽ እንደሚያደርገንና አባቴም እናቴም ለኔ ያወረሱኝን የእርስ በርስ ትግልን እኔም ነገ ለልጄ ትግል አውርሼ እንዳላልፍ መሆን አለበት። ነጻነት የሚለውን ቃልና ትርጉም  የምናይበት እይታችን መሰፋት አለበት። አንዱን ጥሎ ስልጣን መያዝ አልያም ለብቻ የሚባል ነጻነት የለም ነበር ያሉት።
የሀረሪ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆኑትና  በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አባድር የታሪክ ሰዎች መግባባትን ለመፍጠር መነሻ  ናቸው። ምክንያቱም መግባባትን ለመፍጠር ካለፈው መጥፎውን የምንሰማው ለወደፊቱ ትምህር እንዲሆነን ነው። የእኛ ታሪክ (Culture of Resistance ) ነው፤ የአሸናፊ ተሸናፊ ፖለቲካ ነው የፖለቲካ ባህላችን። ይህ ማብቃት አለበት፡ ሁላችንም በአሸናፊነት ልንወጣ የምችልበት መንገድ መኖር አለበት። ችግሩን ለመፍታት መንግስት ወይም የፖለቲካ ድርጅቶችን ብቻ የምንጠብቅ ሳይሆን ሕዝብ ችግሩን እንዲፈታ የህዝብ አጀንዳ ተደርጎ መቅረብ አለበት ብለዋል፡
  • በአቀራረብም ሆነ መድረክ ላይ ሲታይ ለብዙዎች ኢትዮጲያዊያኖች አለባበ ጭምር ለየት የሚልና አማርኛ ቋንቋን እንደሱዳናዊው ሰይድ ከሊፋ “ጤና ይስጥልኝ እንደምናቹ “ብሎ የጀመረው ከአውስትራሊያ የመጣው የቤኑሻንጉሉ ናስር ማንነት በኢትዮጲያዊነት እንዴት ይመዘናል? የሚለውን በራሱ እይታና በሕይወት ታሪኩ ጭምር ያጋጠመውን ገልጾ እስካሁን
የተጓዝንበት ኢትዮጲያዊነት መንገድ ሊፈተሸ ይገባል፡ ለኔ ኢትዮጲያ ኩራቴ ነች የበለጠ እንድኮራባት ግን የአስተሳሰብ ለውጥ በሁላችንም እንዲሁም  የሥርዓት ለውጥ ያስፈልጋል ብሏል።
gishe
በመቀጠልም በወጣትነት እድሜ ውስጥ የምተገኘዋ ሳምራዊት አሁን የያዝኩትን አመለካከት እዚህ ስብሰባ ላይ ከማቅረቤ በፊት  ያለሁበት ከተማ ዲሲ በመሆኑና የዲሲንም ፖለቲካ ስለማውቀው ምን ይሉኛል ብዬ  ብዙ ተጨንቄአለሁ ነገር ግን ለሃገሬ ከምጨነቀው በላይ አያስጨንቀኝም። ከሁሉ በላይ በተለያየ መልኩ ጭቆናና በደል በኢትዮጲያ ውስጥ እንደነበረና አሁንም እንዳለ መረዳት ወሳኘና የሌሎችን ብሶቶች በማዳመጥ ብቻ ነው ከበሽታችን መፈወስ የምንችለው በሽታችን ላይ መተማመን አለብን ይህ እስካልሆነ ደግሞ መፍትሔ ልናመጣ አንችልም ነበር ያለችው።
ከሜኒሶታ የመጣው ነጌሶ ደግሞ “አብዛኛዎቹ ፖለቲከኞች አብዛኛውን የሚያወሩት ስለራሳቸው ነው ወይም እራሳቸውን ስለማስተዋወቅ ነው። ዛሬ በEthnic empowerment   የሀገራችን ፖለቲካችግር አይፈታም በ Civic   political  transition ያስፈልገናል። አሁን ካለው ሁኔታ አንፃር የሚታገለው እየታገለ ዲሲፒሊንድ በሆነ process ብቻ ነው ለውጥ ማምጣት የምንችለው፤ በሥልጣን ላይ ያለው  መንግስት ስልጣኑን ላይ ከማቆየት ማንኛውንም አይነት አደገኛ ካርዶችን ተጠቅሞአል። የኢህአዴግ ስትራቴጂም ከአንዱ ጋር ሀውልት እየሰራ ሌላውን መግደል ነውና ይሄንን መገንዘብ ይኖርብናል ብለዋል።
አቶ ነጋሲ የትግራይ ተወላጅ በበኩላቸው የቆየ አባባል ቢሆንም የተቃራኒነ ባልና ሚስት ወግን በምሳሌነት አስቀምጠው  ባጭሩ ሚስትየው ሁልጊዜ ተቃራኒ መልስ ወይም ድርጊት ማድረግ ስለምትወድ አንድ ቀን ወራጅ ጎርፍ ሲወስዳት  ለማዳን የተሰበሰበውን ህዝብ ወንዙ ወደሚፈስበት ሳይሆን ሽቅብ ወደላይ ነው የምትሄደው ብሎ ፈላጊዎቹን ወደተቃራኒው አቅጣጫ  መራቸው በማለት  እልከኝነት ሀገራችንን እያጠፋ ነው በቅርቡም በኦሮሚያ የተካሄደው የመሬት መፈናቀል ጥያቄ በሁሉም ኢትዮጲያ ግዛቶች ውስጥ መሆኑንና በትግራይም ሕዋሓት እግረሃረግ የሚባል አካባቢን ወደመቀሌ ለማካለል ጥረት ሲያደርግ ሕብረተሰቡ ተቃውሞ በማሰማቱ የእንቅስቃሴው መሪዎች ናቸው የሚባሉ 15  ሰዎች ከ 3  ዓመት እስከ 15  ዓመት ተፈርዶባቸውበእስር ላይ  ይገኛሉ። ስለዚህ ትግሉ የጋራ ነው። ከማለት በተጨማሪ TPDM የሚባለው የታጠቀ ተቃዋሚ ቡድን  በአሸባሪነት ሳይፈረጅ በእስክሪፕቶ የሚታገለውን ኦባንግ ሜቶን አሸባሪ ብሎ የፈረጀ ጉደኛ መንግስት ነው ስልጣን ላይ ያለው በማለት ታዳሚውን አስቀውታል።
የትውልድ እልቂት ነው የያዝነው ባለፉት 40 አመት የሃገራችን እናቶች ሰቆቃ ሊያበቃ ይገባል በሰለጠነው አገር የእሳት አደጋና አምቡላንስ የድመትና የውሻን ሕይወት ለማዳን ምን ያህል  እንደሚደክሙ እያየን ዛሬ በሀገራችን ዜጎቻችን በጥይት በአውላላ ሜዳ ላይ ተዘርግተው ማየት ለኛ ለእናቶች በተለይም ያለፉት 40 ዓመታት እናቶች የእለት እይታችን ሆኗል። እስከመቼ ነው ይሄ የሚቀጥለው ? ስለዚህም ሁላችንም መጮህ አለብን በተለይ የእምነት አባቶች ፖለቲካ ውስጥ አንገባም እያልን አምላካዊ ክቡር ህይወትን ለማዳን እጃችንን አጣጥፈን መቀመጡ እምነታችንን ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል በሀገራችን መግባባት እንዲፈጠር ድምጻችንን ማሰማት አለብን በማለት በጉንጮችዋ ከሚወርደው እንባ ጋር መለክትዋን አስተላልፋለች።
በመቀጠልም በስብሰባው ላይ ተገኝተው ሀሳባቸውን ያካፈሉት ታዋቂው  ምሁርና gtenocide watch   ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ ር ግሪጎሪ ሳቶንተን ነበሩ። ዶ/ር ግሪጎሪ በተለያዩ አገራት የዘር ማጥፋትን በሚመለከት ሰፊ ጥናት በማካሄዳቸውም ካነሱዋቸው ምሳሌዎች እንደነሩዋንዳ አይነቶችንና  በኢትዮጲያ ወስጥም በአኙዋክ ላይ የተፈጠረውን ዳስሰው በአጠቃላይ በኢትዮጲያ የዘር ማጥፋት ወንጀል ወደፊት ሊፈጠር ሚችልበት ሁኔታ አለ ወይ ? ለዚህስ ቅድመ ሁኔቶች አሉ ወይ የሚለውን ጥያቄ አንስተው ከዚህ ቀደም በተደረጉ ጥናቶች ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው የሚባሉትን 10 ደረጃዎችን አስረድተዋል ከእነዚህ ደረጃዎች አብዛኛዎቹ እየታዩ ናቸው በማለትም ገለጻ ሰጥተዋል ። ( አንባቢ ይህን ለማወቅ The  8   stage   of   Genocide   የሚለውን በጎግል ማየት ትችላላችሁ። በመሆኑም ኢትዮጲያዊያኖች ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡ በስልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦችን ወደእልህ የሚያስገባ ፖለቲካ መጫወት አደጋ እንዳለው በተለይም ሙስናና ዘር ማጥፋት ወንጀል ተመጋጋቢ መሆናቸውን አስረድተዋል።
የስብሰባው መቋጫ የሆነውንና በስፋት ለ3 ቀናቶች በመድረኩ ተሳታፊዎች  ቀንና ማታ ተወያይተውበት የደረሱበትን የመፍትሔ ሀሳብ ያቀረቡት ከአትላንታ የመጡት Reve.   ጸጋ ነበሩ። እሳቸውም ገና ወያኔ ኢህአዴግ ስልጣን ሲይዝ ለሀገራችን የመግባባትና የእርቅን አስፈላጊነት ያነሱ ወገኖች እንደነበሩ አስታውሰው አሁንም ሰው ባወቀው መጠን እንደሚቀጣ የእግዚአብሔርም ቃል ይህንኑ እንደሚያስረዳ አመልክተው ይህንን የተገነዘብን ሰዎች በሀገራችን እርቅና ፍትሕ እንዲሰፍን የእርቅና የፍትህ ጉባኤ አቋቁመናል ብለዋል።
የጉባኤው አላማም
–   ሁሉን የሚያካትት ሁሉ አብሮ የሚጓዝበት
–   ከህሊና ክስ ነጻ የሚያወጣ
–   በሁሉም ኢትዮጲያዊያን ዘንድ ፍትህ እክልነት ርትእ የሚያመራ
–   የኢትዮጲያ ብሔር ብሄረሰብ የባሕል የቁዋንቁዋ ልዩነት ደምቆ የሚወጣበት
–   በነጻነትና በሰላም መግባባትን የሚፈጠርበት
–   ከሀይማኖችና ማህበራዊ ተቋሞች ጋር ግንኙነት መፍጠርን
–   የእርቀ ሂደት እንዲደረግ የሚታገሉ ቡድኖችን  ማስተባበርን እንደሚያጠቃልል ገልጸዋል።
በመጨረሻም  ስብሰባውን የጠቀለሉት የ SMNE  መሪ አቶ አባንግ ሜቶ “ጥቁሩ ሰው” በእያንዳንዱ ነጥብ ላይ የተነሱትን ሀሳቦች አሰባስበው እነሆም ሀገራችንን ከክፋ አደጋ ውስጥ ለማዳን የሚያስችል አንድ ወሳኝ እንቅስቃሴ ላይ ደርሰናል፤ ለዚህም ድርጅታችን ከእንግዲህ የብሔራዊ መግባባትንና እርቅን አጀንዳ በባለቤትነት እናንቀሳቅሰዋለን ማንኛውም ለዚህ ዝግጁ የሆነ ኢትዮጲያዊ ቡድን አብሮን ለመስራት በሩ ክፍት ነው ብለዋል።
  እውን ኢትዮጲያ አደጋ ውስጥ ናትየግል  ማጠቃለያ ሃሳብ
ከላይ የእያንዳንዱ ተናጋሪ ሀሳብ ቀንጨብ ያደረግኩት ያለምክንያት አይደለም ሁሉም የወቅቱን የሀገራችንን ፖለቲካ ሁኔታ የሚዳስስና በብዙዎችም ቀደም ሲል የተነገረ ቢሆንም ከመናገር አልፎ ወደ ተግባር ሊያመጣ የሚችል ሀሳብን ስላቀፈ ነው ዛሬ ሀገራችን ስለምትገኝበት ሁኔታ ፖለቲከኛው አክቲቪስቱ  የሀይማኖች መሪዎች ምሁራን ሁሉም  አንዳንድ የሥርዓቱን ሰዎች ጨምሮ የሚሰማቸው  ኢትዮጲየ ከምንጊዜውም የበለጠ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ መግባትዋ ነው ። ከፍተኛ የፖለቲካ የኢኮኖሚ የድህነት የረሀብ ችግር ተደቅኖብናል ። የፖለቲካ ስልጣን የሚኖረው ሀገርና ሕዝብ ሲኖር ነው። ከሁሉም በላይ አይጥና ድመት ጨዋታ በፖለቲካ ውስጥ ያለ ቢሆንም ከዘር  ፖለቲካ ጋር ከተያያዘ ግን አይጥዋም ድመትዋም አይተርፉም ምክንያቱም የድመት ዘር ያልሆነ ሁሉ አይጥ ሲጠፋ ነግ በኔ ስለሚል ከድመት ጋር መጠፋፋቱን ይቀጥላል። ማብረጃውም ቀላል አይሆንም። ባለፉት 25  ዓመታት የዘር የፖለቲካ አቀንቃኞች ቁጥር እየቀነሰ የመጣ ቢመስልም አሁን በአዲስ መል እያገረሸ ነው። አንዳንድ ወገኖቻችን የብሄር ጥያቄ ነው ለምን የዘር ፖለቲካ ትላላችሁ የሚል አስተያየት ወይም ነቀፌታ ያቀርባሉ ወይም የዘር ፖለቲካ ያለውን ሁሉ የአንድ ዘር ሰው ለማድረግ ይሞክራሉ።  እኔ በግሌ አማራ ነኝ ኦሮሞ ነኝ ትግሬ ነኝ ስላለ ወይም ትግሬነቴ አማራነቴ ኦሮሞነቴ ሊታወቅልኝ ይገባል ያጣሁትን ፍትህና እኩልነት ማግኘት አለብኝ ብለው የተነሱ ወንድሞችና ወገኖቼን በዘረኝነት ጭራሽ አላስባቸውም። ያጡትን ነገር እንዲያገኙ እኔም የጎደለኝን አብረውኝ እንዲያሟሉ መታገል ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ ሁላችንም ሳንፈልገው ወይም ሳንታገልበት በተፈጠርንበት ዘር መጠራትን መጥላት የተፈጥሮ ማንነታችንን መጥላት ይሆናል።
ዘረኝነት ከፖለቲካ ስልጣን ጋር የተያያዘና  ወይም በራሱ ዘር ላይ ለመንገስ የሚፈልግ ፖለቲካ አቀንቃኝነት ነው። ይህ ደግሞ በይበልጥ በድህነትና በሁዋላ ቀርነት ላይ ላለ ህብረተሰብ የፖለቲካ መጫወቻ አይነተኛ ካርድ ነው። በሕብረተሰብ እድገት ቤተሰብ ሠፈር መንደር አካባቢ ክልል ሀገር እያደጉ የመጡ ተቋሞች ናቸው።  ሰው ለጥቅሙ ሲል አንዳንዶችም በተፈጥሮ አስገዳጅነትያቁዋቁማቸው ተቁውሞች ናቸው።
የዘረኝነት ፖለቲካ አቀንቃኞች ደግሞ  በአንድ አካባቢ ወይም ለአንድ ብሔረሰብ የተሰጠ መለያ አይደለም። የቁጥር ማነስ የመደራጀት ወይም ህብረተሰቡን የማንቀሳቀስ ደረጃ ሊለያይ ይችላል። በኢትዮጲያችን  የህብረተሰባችን የእድገት ደረጃ የዘረኘነትን ፖለቲካ  የመሸከም አቅም በሁሉም ህብረተሰብ ውስጥ አለ። ለዚህም ነው አምባገነኑ መንግሥት ስልጣኑን ለማራዘም ሁሉንም በዚህ ካርድ የሚጫወትበት ። የዘረኝነት ፖለቲካ ለኔ የራሱን ዘር ከሌሎች የተሻለ አድርጎ መሳልና በዘሩ ተከልሎ የፖለቲካ ስልጣን ለመያዝ ወይም በራሱ ዘር ላይ ለመንገስ የሚፈልግ ፖለቲካ አቀንቃኝነት ነው።
ስለዚህ ዛሬ በሀገራችን እያቆጠቆጠ ያለውና የሥርዓቱ ዋነኛ ካርድ የሆነውን “ማንነት በዘር” ልናተኩርበት የሚገባን በዚህ አቅጣጫ የሚሄዱትን ተው ማለት አስፈላጊ ይመስለኛል በተለይ አንዱ ወንድማችን በስብሰባው ላይ እንደገለጸው አባቶቻችን ትግል ትተውልናል
እኛም ለልጆቻችን መታገልን(ፖለቲካዊ ቀውስ) ማስተላለፍ መቆም አለበት ያለው ትክክል ይመስለኛል።በዚህ ረገድ በሀገራችን ውስጥ ያለውን ውጥረተት ለማርገብ በእነ አቶ ኦባንግና በሌሎች ኢትዮጲያዊያን የተጀመረው የብሔራዊ መግባባት አጀንዳ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል ይህን አጀንዳ በሚመለከት ወገኖች የሚያቀርቧቸው በርከት ያሉ አስተያየቶች ጥያቄዎች ተቃውሞዎች ድጋፎች አሉ። የሚያሳዝነው ግን ሁላችንም በዚህ ጉዳይ የአቶ መለስ ራዕይ አንጋቢዎች ሆነን መቆየታችን ነው። ማንና ማን ተጣሉ ማንና ማን ነው የሚታረቀው?                ……በሌላ በኩል ደግሞ ወያኔ ኢህአዴግ እሺ አይልም ወዘተ.. እስከሚገባኝ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ብሔራዊ መግባባት ወይም ብሔራዊ እርቅ መደረግ እንዳለበት በትጥቅ ትግል የተሳተፉትም ሳይቀሩ የሚያነሱት ጉዳይ ቢሆንም አንዳቸውም ወደተግባር የሚያመራ እንቅስቃሴ አላደረጉም።
እስከማውቀው ድረስም በስልጣን ላይ ያለው  የኢህአዴግ መንግስትም  የሚያወራውና የሚሰራው የተለያየ ቢሆንም በሚቀጥሉት አምስት አመት ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ ብሔራዊ መግባባትና ዲሞክራሲን በሚመለከት የሚያተኩር በአባዱላ ገመዳ የሚመራ አንድ ኮሚቴ መቋቋሙን ከዚህ ቀደም ከሪፖርተር  አንብብያለሁ። ይህ አጀንዳ አሁን ሃገራችን ለገባችበት ቀውስ ሊያወጣት የሚችልና የፖለቲካ ድርጅቶች አሽናፊነትና ተሽናፊነት ፖለቲካ ሳይሆን ህዝብ በአሸናፊነት ሊወጣ የሚያስችል አይነተኛ መንገድ ቢሆንም ባለቤት ያጣ አጀንዳ በመሆኑ ብዙዎቻችን ባለቤት እዲያገኝ የጮህንለት ጉዳይ ነው። አሁን በእነአቶ ኦባንግ የአጀንዳው ባለቤትነት ጥያቄ በመመለሱ
መልካም ጅምርና ብዙዎች ኢትዮጲያውያን ሊያሰባስብ የሚችል በመሆኑ በርቱ ግፉበት እንላለን። ፖለቲከኞቻችንም ለዚህ አጀንዳ አብሮ መስራት ሌላው የመፈተኛ ጥያቄም መሆኑን ሊያምኑ ይገባል ። የፖለቲካ ስልጣን ጥያቄን መመለስ የሚቻለው የተግባባ ማህበረሰብ ሲኖረን ነው። ሊዩነቶቻችንን በመነጋገርና በመወያየት መፍታት ስንችል ብቻ ነው። አምባገነንነትና የዘር ፖለቲካ የወያኔ ኢሃዴግ ብቻ መለያ አይሆንም። ያንን ፖለቲካ የሚሽከም የህብረተሰብ ክፍል ያቀፈው ሁሉ በውስጡ የተደበቀውን በሽታ  ጠመንጃ ሲይዝ ያወጣዋልና ።  ለብሄራዊ መግባባት የምትጮሁ ወገኖች አንገታችሁን ቀና አድርጉ። ወቅቱ የግድ ይላል።
ምንጭ:-

No comments:

Post a Comment

wanted officials