የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የአማራ ክልል ሹሞች በጎንደር ጎሃ ሄቴል ለሦስት ተከታታይ ቀናት ያደረጉት ድብቅ ስብሰባ ያለምንም ውጤት በፀብ ብቻ ተቋጨ፡፡ በህወሓቶችና በብአዴኖች መካከል የተካረረ ፍጥጫና ንትርክ ተከስቶ የነበረ መሆኑም ተደርሶበታል፡፡
(የአርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬድዮ) በጎንደር ከተማ ጎሃ ሆቴል ውስጥ ከጥር 28 እስከ የካቲት 1 2008 ዓ.ም በድብቅ በተካሄደው ስብሰባ ላይ የተገኙት የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናት አባይ ፀሐዬ፣ ስብሃት ነጋ፣ ደብረ ፂዮን ገ/ሚካኤል፣ አባይ ወልዱ እና የትግራይ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ሹም ናቸው፡፡
ገዱ አንዳርጋቸው፣ አለምነው መኮንን እና መኳንንት /የአማራ ክልል ፀጥታ ሹም/ ደግሞ ከብአዴን ወገን የተገኙ የአማራ ክልል ሹማምንቶች ነበሩ፡፡
የህወሓት ከፍተኛ ባለስልጣናትና የህወሓት ዲቃላ የሆነው ብአዴን ባለስልጣናት በጎንደር ጎሃ ሆቴል ተሰብስበው የተነታረኩባቸው አጀንዳዎች ሁለት ሲሆኑ የወልቃይትን የአማራ ማንነት ጥያቄ እና ብረት ያነሱ የነፃነት ድርጅቶችን /በተለይም አርበኞች ግንቦት 7ን/ በሚመለከት ነው፡፡
የትጥቅ ትግል እያደረጉ የሚገኙ የነፃነት ድርጅቶችን በሚመለከት ህወሓቶች “ሰተት ብለው ከበረሃ ወደ ህዝቡ እንዲገቡ እያደረጋችኋቸው ነው…” በማለት ብአዴኖችን ወቅሰዋቸዋል፡፡
ከወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ደግሞ የትግራይ ክልል አስተዳዳሪና የህወሓት ሊቀ መንበር የሆነው አባይ ወልዱ እንዲህ ብሏል፡፡
“ወልቃይት የትግራይ ነው! የአማራነት ጥያቄው በዚህ የማያቆምና ተጠናክሮ የሚቀጥል ከሆነ የማያዳግም እርምጃ እንወስዳለን…!”
ቀጥሎም አባይ ወልዱ የአማራ ክልልን አስተዳዳሪ ገዱ አንዳርጋቸውን “አንተ የአማራን ህዝብ የጦር መሳሪያ ያስታጠከው ሆነ ብለህ በትግራይ ላይ ጦርነት ለማወጅ ነው…” በማለት ተናግሮታል፡፡
ገዱ አንዳርጋቸውም በበኩሉ “እኔ ህዝቡ በሀብቱ ገዝቶ ከጥንት ጀምሮ ታጥቆት የቆየውን ጦር መሳሪያ ህጋዊ ፈቃድ በመስጠት አፀናሁለት እንጂ ልክ እንዳንተ ከመንግስት ግምጃ ቤት አውጥቼ በገፍ አላስታጠቁትም፡፡ በትግራይ ህዝብ ላይ ጦርነት አወጅክ ላልከኝም የትግራይን ህዝብ ሰብስበህ በወልቃይት ህዝብ ላይ እርምጃ እንወስዳለን ብለህ በይፋ ጦርነት ያወጅከው አንተ ነህ፡፡” በማለት ለአባይ ወልዱ መልስ ሰጥቶታል፡፡
የጦር መሳሪያን በሚመለከት ደብረ ፂዮን ገ/ሚካኤል ገዱ አንዳርጋቸው የአማራን ህዝብ እንዳስታጠቀ ወቀሳ ሰንዝሯል፡፡ ደብረ ፂዮን ስለ ወልቃይት ህዝብ የአማራ ማንነት ጥያቄ የሚከተለውን በማለት ቁልጭ ያለ አቋሙን አስቀምጧል፡፡
“የወልቃይት ጉዳይ ክልል አንድን እንጂ ማንንም አይመለከተውም፤ ውሳኔውም ሊሆን የሚችለው የክልል አንድ ብቻና ብቻ ነው፡፡”
ለዚህ የደብረ ፂዮን ንግግር ገዱ አንዳርጋቸው ሲመልስ
“እኛ ሄደን ኑ አንላቸውም፤ ከመጡ ግን የማንቀበልበት ምንም ምክንያት የለም፤ ደግሞም ውሳኔ ማስቀመጥ ያለበት ራሱ የወልቃይት ህዝብ ነው፡፡”
በመሆኑም በሁለቱ ክልሎች /በትግራይና አማራ/ አስተዳዳሪዎች ማለትም በአባይ ወልዱና ገዱ አንዳርጋቸው መካከል ስብሰባው ውስጥ የተካረረ ፍጥጫ ተከስቶ ነበር፡፡
ህወሓቶች ለገዱ አንዳርጋቸው ከባድ ማስጠንቀቂያ ሰጥተውታል፡፡
በአጠቃላይ በጎንደር ጎሃ ሆቴል ከጥር 28 እስከ የካቲት 1 2008 ዓ.ም በድብቅ የተካሄደው የህወሓቶችና የብአዴኖች ውይይት ያለምንም መግባባት በፀብ ብቻ ተጠናቋል፡፡
No comments:
Post a Comment