Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, February 19, 2016

“ብሔራዊ ጭቆናው የትግላችን መዘውር ሆኖ ይቀጥላል! ” – ድምጻችን ይሰማ


muslim a

ረቡእ የካቲት 9/2008
ኢትዮጵያዊው ሙስሊም እየደረሰበት የሚገኘውን ብሔራዊ ጭቆና ከጫንቃው ላይ ለማራገፍ ላለፉት አራት አመታት ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየታገለ ይገኛል። ይህ እልህ አስጨራሽ ትግል የተለያዩ እርከኖችን ሲሻገር ሰላማዊነቱን እንደጠበቀ መሆኑ ብዙዎችን አስደምሟል፡፡ ለአንዳንዶችም ትምህርት መሆኑ አልቀረም። ሙስሊሙ ማህበረሰብ ትግልን እንደ ህይወት መንገድ፣ ድልን ደግሞ በመንገዱ ላይ እንደሚገኝ ፍሬ አድርጎ ስለተመለከተው ከመንግስት በኩል የሚደርሱበት አሳዛኝ በደሎች ሳይበግሩት ትግሉን ጠብቆ ማቆየት ችሏል። ወትሮውንም ቢሆን ለፍትህ በሚደረግ ሰላማዊ ትግል የሙስሊሙ ድርሻ መታገል፣ ድሉን ማሳካት ደግሞ የፈጣሪው ድርሻ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ይሁንና ሰላማዊውን ትግል ለማደፍረስ ሳር ቅጠል የሚበጥሰው መንግስት መልክና ቅርጹን እየለዋወጠ ሙስሊሙን ማህበረሰብ ከትግሉ ለማደናቀፍ እየሞከረ ይገኛል። ከዚህ ቀደም በተለያዩ ልሳኖቹ ብቅ እያለ ሰላማዊውን ትግል ከማጠልሸት አንስቶ ንጹሀን ኮሚቴዎቻችንን በሀሰት እንደወነጀለው ሁሉ አሁንም ከእውነት ፍጹም የራቁ መረጃዎችን በህብረተሰቡ ዘንድ እየረጨ ነው። ‹‹የታጠቀ ሰራዊት በወሬ ይፈታል›› እንዲሉ መንግስት በጉልበት አልገታ ያለውን የሙስሊሙን የመብት ጥያቄ በሀሰት ፕሮፓጋንዳ ለማድቀቅ የከፈተውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ ቀጥሎበታል።
ሰሞኑን ትግሉን በሚመለከት በ‹‹ኢትዮ ቻናል›› ጋዜጣ ታትሞ ለንባብ የበቃው ዘገባም የሚያሳየው ይህንኑ ተጨባጭ ነው። መንግስት በቆርጦ ቀጥል የቅንብር መርሁ መሰረት የውድ ኮሚቴዎቻችንን ሰነድ ከሚፈልገው ዘገባ ጋር በማዛመድ ‹‹በሬ ወለደ›› አይነት ዜና አውጇል። ከዚህ ቀደምም ቢሆን ‹‹ጂሀዳዊ ሀረካት›› ብሎ በሰየመው ‹‹ልብ ወለድ›› ዘገባው ላይ የኡስታዝ አቡበከርን ንግግር ቆራርጦ ‹‹ለጂሀድ አነሳስተናል›› የሚል አይነት ወሬ ለመፍጠር ያደረገውን ጥረት የምንዘነጋው አይደለም። ይሁንና ሙስሊሙ ህብረተሰብ በእንዲህ አይነቱ ደባ ከመሸወድ ይልቅ አንድነቱንና የመረጃ አሰባሰብ ክህሎቱን አጠናክሮ መቀጠሉ መንግስትንና የሀሰት ልሳኖቹን ማክሰሩ ተስተውሏል። ጋዜጣው ‹‹የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት መንግስትን ይቅርታ ለመጠየቅ እየተማጸኑ ናቸው›› ሲል ያሰራጨው ዘገባ የሙስሊሙን ማህበረሰብ ሞራል ለመሸርሸር እና እንድነቱን ለማዳከም ታቅዶ የተዘጋጀ ጥንቅር እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። ለመረጃነት አባሪ ተደርጎ የቀረበው የኮሚቴዎቻችን ፊርማም ከጽሁፉ ጋር ምንም አይነት ተዛምዶ የሌለው ነው። ይልቁንም ኮሚቴው ላለፉት አራት አመታት ሰላማዊነቱን ጠብቆ እንደተጓዘው ሁሉ አሁንም ቢሆን ሰላማዊ አማራጮችን በሙሉ እስከ መጨረሻው ድረስ አሟጦ እንደሚጠቀም፣ መንግስትም ከማያዋጣ እብሪተኝነቱ በመታቀብ በሙስሊሙ ህብረተሰብ ላይ ያወጀውን ብሄራዊ ጭቆና ለማቆም ዝግቹ እስከሆነ ድረስ ኮሚቴው ሰላማዊ መፍሄን መሻት ስቃይ እና መከራ ያማያዛንፈው አቋሙ መሆኑን በፊርማው ያረጋገጠበት ልዩ ሰነድ እንጂ ‹‹ይቅርታ ለመጠየቅ የተደረገ ተማጽኖ›› አይደለም፡፡ (የትግላችንን ሰላማዊነት በተመለከት በግንዛቤ ማስጨበጫ ትንታኔዎችን ወደፊት በአላህ ፈቃድ የምንመለስባቸው ይሆናል፡፡)
ሙስሊሙ ማህበረሰብ ያነሳቸው ጥያቄዎችም ሆኑ ጥያቄዎቹን ለማስመለስ ኮሚቴውና አጠቃላይ ሙስሊሙ ህብረተሰብ የሄደባቸው መንገዶች ሰላማዊ፣ ህጋዊ እና ፍትሃዊ ስለሆኑ ይቅርታ የምንጠይቅበት አንዳችም ነገር ያለመኖሩን ያክል ኮሚቴው በማንኛውም አካል በኩል ይቅርታ እንዲጠየቅለት የሚፈልግበት ሁኔታም አይኖርም። በእስር ላይ የሚገኙ የኮሚቴው አባላት እና የሙስሊሙ ህጋዊ መሪዎቻችንም ሆኑ ከትግላችን ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የተለያዩ እስር ቤቶች እየተሰቃዩ የሚገኙ ሙስሊሞች ኢፍትሃዊ የሆነ ስርዓት ሰለባ እንጂ የትኛውንም ህግ የተላለፉ ጥፋተኞች አይደሉም።
መንግስት የሙስሊሙን ትግል ለማዳከም፣ ብሎም ለማጥፋት ባሳለፍናቸው አራት የጽናት አመታት ውስጥ ያልፈነቀለው ድንጋይ እንደሌለ ሁሉ ዛሬም ነገም ይህንን አላማውን ለማሳካት ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለአፍታ የምንዘነጋው አይሆንም። በተለያየ ጊዜ ያወጣቸው የቴሊቪዥን ድራማዎችም ይሁኑ በጋዜጣው የሚያወጣቸው ተረት ተረቶች ለዚሁ ዓላማ የታቀዱ መሆናቸው ምንም የሚያጠራጥር አይደለም። እስካሁን ያልተሳካለት እና ወደፊትም ፍጹም የማይሳካለት ጉዳይ የሙስሊሙን አንድነት እና ለትግሉ ያለውን ሞራል መስበር ቢሆንም ይህ ግን የእኛን የዘወትር ጥረት እና ጥንቁቅነት ይፈልጋል። የመንግስት ሴራ ሰለባ ከመሆን ራሳችንን ልንጠብቅ ይገባል። ብሄራዊ ጭቆናን በቋሚነት ለማስወገድ የምናካሂደው ትግላችን ብዙሃኑን አሳታፊ ሆኖ የሚቀጥል ሲሆን ሁላችንም ከግል ፍላጎቶች በመራቅ ራሳችንን ለወጣው የትግል መርህ ተገዥ በማድረግ እና ይህንንም መርህ ብቻ በመከተል ከድል የምንደርስበትን ቀን ልናፋጥን ይገባል። ይህንን ማድረጋችን አንዳችን ለአንዳችን ተደጋጋፊ ሲያደርገን ሁላችንንም ሰለባ በሚያደርግ የመንግስት ሴራ ውስጥ ገብተን ከመነታረክም እንዲሁ ይጠብቀናል። ትግሉን ለመደገፍ የሚደረጉ ጥረቶች ተኣማኒነት እና ተቀባይነት የሚኖራቸውም የትግሉን መርህ ብቻ ተከትለን ስንንቀሳቀስ ብቻ ይሆናል፡፡ (የትግላችንን ብዙሃኑን አሳታፊነት በተመለከተ በግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎቻችን በሰፊው የምንመለስበት ይሆናል።) በመሆኑም መንግስት ይዞልን የቀረበውን ተረት ተረት ተከትሎ በግልም በቡድንም የሚደረግ የትኛውም አይነት ውዝግብ እንዳይኖር አጥብቀን እየጠየቅን ውዝግቡ ትርፉ የመንግስትን አላማ ከግብ ማድረስ ብቻ እንደሚሆን ለማሳሰብ እንወዳለን።
ስለትግሉ በሚኖሩን መሰረታዊ መረጃዎች ዙሪያ ጥንቃቄ ማድረግም እንዲሁ አስፈላጊ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ አላህ (ሱ.ወ) እንዲህ ይለናል፦ ‹‹እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ነገረኛ ወሬን ቢያመጣላችሁ በስህተት ላይ ኾናችሁ ሕዝቦችን እንዳትጎዱና በሠራችሁት ነገር ላይ ተጸጻቾች እንዳትኾኑ አረጋግጡ፡፡›› (ሱረቱል ሁጁራት 43፡6) በዚህ መለኮታዊ ትእዛዝ መሰረት መረጃን ሳያጣሩ ድምዳሜ ላይ መድረስና እርምጃ መውሰድ ለጥፋት የሚያጋልጥ ጠንቅ ነው፡፡ በመሆኑም ምንጊዜም የሚደርሱንን መረጃዎች በጥንቃቄ መመርመር እና ለሌላ ሰው ከማስተላለፋችን ወይም ለራሳችን እውነት ነው ብለን ከመቀበላችን በፊት ተአማኒነቱን ማረጋገጥ አስፈላጊ መሆኑን ልንዘነጋ አይገባም፡፡ ትግላችንን እና ሂደቱን፣ እንዲሁም አቅጣጫውን በተመለከቱ ጉዳዮችም ምንጊዜም ትክክለኛውን መረጃ ከ‹‹ድምጻችን ይሰማ›› ገጽ ብቻ መውሰድ እንዳለብንም በአንክሮ ለመግለጽ እንወዳለን። ትግላችን ብሔራዊ ጭቆናው እስካልተወገደ ድረስ ተጠናክሮ የሚቀጥል እና በየትኛውም አይነት ሴራ ሊገታ በማይችልበት ህዝባዊ መሰረት ላይ ያረፈ መሆኑንም በዚሁ አጋጣሚ ለማስታወቅ እንወዳለን።
ብሄራዊ ጭቆናን አንሸከምም!
ትግላችን እስከድል ደጃፎች በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማል!
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment

wanted officials