ዓለም አቀፍ ኢነርጂ ምክር ቤት ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር እያካሄደች የምትገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት፣ ከኢኮኖሚ ይልቅ ለፖለቲካ ጥቅሞች ያደላ ነው አለ፡፡
የዓለም ኢነርጂ ምክር ቤት ከሳምንት በፊት ለውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር በላከው ደብዳቤ፣ ኢትዮጵያ ለጎረቤት አገሮች ኤሌክትሪክ ሽያጭ ለመፈጸም አቋም መያዟ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስታውቋል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ በኩል የሚደረገው የኤሌክትሪክ ሽያጭ ስምምነት ወቅታዊውን የዓለም የአሌክትሪክ መሸጫ ዋጋ ያላገናዘበ መሆኑን በመግለጽ፣ የዋጋ ድርድሩ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ይልቅ ለፖለቲካዊ ጥቅሞች ያደላ ነው በማለት አትቷል፡፡
ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ምክር ቤቱ በዚህ መሠረት ኢትዮጵያ ቀደም ሲል ያካሄደቻቸውን የኤሌክትሪክ ሽያጭ ስምምነቶች፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት እያከናወነቻቸው ያሉ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ድርድሮች ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች አንፃር በድጋሚ ልታጤነው እንደሚገባ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡
የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ የዓለም ኢነርጂ ምክር ቤት ደብዳቤውን መላኩን ለሪፖርተር አረጋግጠው፣ ይህ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ባለሥልጣን መተላለፉን አመልክተዋል፡፡
አቶ ሞቱማ እንደገለጹት በኤሌክትሪክ ሽያጭ መንግሥት ያለው የፖሊስ አቅጣጫ ወቅታዊ የዓለም ዋጋ፣ ወይም የዓለም የጨረታ ዋጋን መሠረት ያደረገ ነው፡፡
‹‹ርካሽ ነው ወይም ውድ ነው የምንለው ነገር አይደለም፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያ ያልተቀመጠ ዋጋን አንጠቀምም፣ አንቆልልምም፤›› በማለት መንግሥት የሚከተለውን አግባብ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን መንግሥት ለዓለም ኢነርጂ ምክር ቤት ምላሽ የሚሰጠው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ባለሥልጣን ጉዳዩን ካጤነው በኋላ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 2,368 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅም ያላት ኢትዮጵያ፣ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ዓመታዊ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም ከአሥር ሺሕ ሜጋ ዋት በላይ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ከውኃ 50 ሺሕ ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ 1.3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት፣ ከእንፋሎት አሥር ሺሕ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አላት፡፡ ይህንን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም የያዘችው ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካና የአካባቢው አገሮች የኤሌክትሪክ እምብርት የሚያደርጓትን ግንባታዎች በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡
በዚህ መነሻነት ከኬንያ፣ ከሱዳንና ከጂቡቲ ጋር የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ስምምነት ስትፈጽም፣ ከሩዋንዳ፣ ከታንዛንያ፣ ከደቡብ ሱዳንና ከቡሩንዲ ጋር ድርድር በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡
ቀደም ሲል በአገሮች ማቅረብ የጀመረችበት ዋጋ ዝቅተኛ መሆኑን፣ አሁን በመደራደር ላይ ያለችበት ዋጋም ዝቅተኛ ነው በማለት የዓለም ኢነርጂ ምክር ቤት መከራከሪያውን አቅርቧል፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ከፍተኛ ገንዘብ ተበድራ ግንባታ የምታካሂድ በመሆኗ፣ ብድሩን ለመመለስ የኤሌክትሪክ መሸጫ ዋጋ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የዓለም አቀፍ ኢነርጂ ምክር ቤት 90 አገሮች ውስጥ የሚገኙ 3,000 አባላት አሉት፡፡ የኢነርጂ ምክር ቤቱ ባቀረበው ማሳሰቢያ ላይ መንግሥት ወደፊት በሚኖረው ምላሽ ላይ የኢትዮጵያ ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታሁን ሞገስ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
No comments:
Post a Comment