Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, February 3, 2016

አቡነ ማትያስ መህበረ ቅዱሳንን አፈርሰዋለው ሲሉ የማፍረሻውን ትዕዛዝ ማን ሰጣቸው? ቅዱስ ሲኖዶስ? ወይንስ….?

H_E_Abune_Matiyas_Archbishop_of_Jerusalem_Misaያልፈረሰን ማፍረስ ያልተነቃነቀን ማነቀነቅ በአንድነት ለዘመናት ተዋደው እና ተፋቅረው የኖሩትን ህዝብ መበተን የኢትዮጵያኖች የእለት ተእለት ዜና ከሆነ ስንብቷል። ዛሬም በአንድነት እና በጥንካሬአቸው  ለቤተ ክርስትያን እውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጉልበታቸውን ሳይሳሱ በመስጠት የቤተክርስትያን ልጅነታቸውን በማስመስከር ያልተማረን እንዲማሩ በማርደግ፣  የአብነት ትምህርት ቤቶችን ህንጻዎችን በማነጽ እንዲጠናከር በማድረግ፣ ቤተክርስትያንን  በቅንነት በማገልገል ወጣትነት ሳያታልላቸው በጉብዝናህ ግዜ እግዚአብሔርን አስብ የሚለውን አምላካዊ ቃል እየፈጸሙ ያሉትን ወጣቶች የበለጠ ፍቅር፣ የበለጠ አባታዊ ምክር፣ የበለጠ ቤተ ክርስትያኗ ድጋፍ፤ ማድረግ ሲገባቸው የቤተክርስትያኗ መሪ በተባሉት በአቡነ ማቲያስ የሰላ ትችት እየተሰጣቸው እጅና እግራቸውን አስሬ ካላስቀመጥኳቸው ተብሎ ዛቻዎችን ስንሰማ እንደ ቤተክርስትያን ልጅነታችን የሚያም ጉዳይ ነው። ማን አይዞት ብሎዎት ነው የቤተክርስትያን ልጆችን ለማሰር የተነሱት? የየትኛውስ አካል ለማስፈጸም ነው ማህበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ የተነሱት?
የማህበረ ቅዱሳን አባል ከአለማዊ ትምህርት የአለማዊ ትምህርታቸውን ጠንቅቀው የተማሩ ከመንፈሳዊ ትምህርታቸውም መንፈሳዊ ትምህርታቸውን በደንብ የተማሩ የተማሩትንም በስራ ላይ የሚያውሉ በአባቶች መሰረት ላይ የተመሰረቱ የቤተክርስትያን አገልጋዮች ናቸው። ማህበረ ቅዱሳን በቁጥር በጣም ብዙ የሚባል አባል እንዳለው የሚታወቅ ሲሆን አገልግሎታቸውም እንደ ቁጥራቸው በጣም ሰፊ ነው። በመላው ኢትዮጵያ የሲኖዶስ አባቶች ሊደርሱበት ያልቻሉትን ቦታዎች ጭምር በመድረስ የቤተክርስትያን ልጅነታቸውን በማስመስከር የተዘጉ ቤተክርስትያንን በማስከፈት፣ ሊዘጉ ያሉትን ሳይዘጉ በመድረስ በተጠናከረ ሁኔታ ቀጣይነት ባለው መልኩ አገልግሎት እንዲቀጥል በማድረግ ቋሚ መገልገያ በመትከል እራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበትን ስራ በመስራት ከፍተኛ ተጋድሎ  እያደረጉ ያሉ የቤተክርስትያን ልጆች ናቸው።
የማህበረ ቅዱሳን እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ብቻ የተወሰነ  ሳይሆን በመላው አለም የተዘረጋ በግዜ እና በቦታ ሳይወሰኑ ለቤተክርስትያን ቅድሚያ በመድረስ አገልግሎት በመስጠት ያለ ስብስብ ነው። ቅዱሳኖች ግዜአቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን ለቤተክርስቲያን በመስጠት ከእግዚአብሔር የአገልግሎታቸውን ዋጋ የጽድቅ አክሊል ተቀብለዋል። የስሙ ስያሜውም እንደሚነግረን የማህበረ ቅዱሳን አገልግሎት ከዚህ የተለየ ባለመሆኑ ማህበረ ቅዱሳን ተብሏል። የቅዱሳንን ፈለግ ተከትለዋልና።
ታዲያ አቡነ ማቲያስ ማህበረ ቅዱሳንን ማፍረስ ለምን አስፈለጋቸው? እውነተኛ አባት ቢሆኑ ልጆቻቸው  በቤተ ክርስትያን ተሰብስበው ሲያዮ ደስ ሊላቸው ሲገባ… ልጆቻቸው  ተሰብስበው ስለቤተክርስትያን በአንድነት ሲቆሙ ሊያኮራቸው ሲገባ… ልጆቻቸው ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ሳይሳሱ ለቤተክርስትያን ሲሰጡ ሊኮሩባቸው እና የበለጠ እንዲተጉ ሊያበረቷቷቸው ሲገባ አስሬአቸው እነሱን ሳላጠፋ እንቅልፍ አይወስደኝም ተብሎ መዛቱ ከፓትሪያሪክ የሚጠበቅ ነውን? ሲኖዶሱ ልጆቻቸው እጅና እግራቸው ታስሮ ከቤተክርስትያን መጥፋት አለባቸው ተብለው ሲዛትባቸው የማህበሩ አባላት ካልጠፉ እንቅልፍ እንደማይተኝ ሲነገርባቸው ምን ተሰምቷችሁ ይሆን?
ሲኖዶስ ከዚህ በፍት አቡነ ማትያስ ላይ በማህበረ ቅዱሳን እና በሌላ ቤተክርስትያናዊ ጉዳዮች ላይ አቡኑ በግላቸው ጥቂት ግለሰቦችን ሰብስበው ከሳቸው ጋር እንዲቆሙ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ላይ ጠንካራ አቋም በማሳየት የአቡኑን ሃሳብ በሙሉ ውድቅ በማድረግ ጥንካሬአቸውን አይተናል። እኛም በእውነተኛ አባቶች በሲኖዶሱ ውሳኔ እጅጉን ኮርተናል። ዛሬ ለምን ተመልሶ መጣ? ተመልሶ ሲመጣስ የሲኖዶስ ውሳኔ ምን ይሆን? ወደፊትስ ተመልሶ እንዳይመጣ ምን አይነት ውሳኔ ይሆን የሚወሰነው?
እንደ ቀልድ በሚሊዮን የሚቆጠር ስብስብን እግሩን እና እጁን አስረዋለው ብሎ  መናገር ከቤተክርስትያን አባት ይጠበቃልን? የአባቶች ድርሻ እኮ ያልተሰባሰቡትን ወደ ቤተክርስትያን መሰብሰብ እንጂ በቤተ ክርስትያን ስር የተሰበሰቡትን ከቤተክርስትያን ማባረር አይደለም። በእግዚአብሔር ቤት ላይ ሹመት የተቀበላችሁት በቤተክርስትያን ጥላ ስር የተሰበሰቡትን ለማፍረስ እና ለመበታተን ነው እንዴ? በእውነተኛዋ ቤተክርስትያን ስር በፍቅር ተሰብስበው በጥላዋ ያረፉትን እንደ ሰው ፍላጎት በቀላሉ ማፍረስስ ይቻል ይሆንን? በቤተክርስትያን  ስር ያለመለያየት በአንድነት የተሰበሰቡትን የቤተክርስትያን ልጆችን አፈርሳችኋለው ብሎ መናገር የቤተክርስትያን አባቶች ሃሳብ ወይንስ የሌላ አካል ሃሳብ?
አቡነ ማቲያስ መሐበረ ቅዱሳንን አፈርሰዋለው ብለው ይናገሩት እንጂ ከኋላቸው  ማን እንዳለ የታወቀ  ነው። ማህበረ ቅዱሳን ያሰባሰባቸው ሁሉም የቤተክርስትያን ልጆች መሆናቸው ብቻ ነው። የማህበሩ አባል የሚሆነው ወይንም የሆኑት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ  አማኝ የሆነ ብቻ ነው። ምንም አይነት የፖለቲካ አላማ  የሌለው ማህበር ነው። የዘር የቀለም ልዩነት የለም።በእርግጠኛነት ለመናገር ከሁሉም ብሄሮች ውስጥ የተዋህዶ ልጅ ከሆነ የማህበሩ አባል መሆን የፈለገ መሆን ይችላል። ወደዚህ ማህበር ሲመጣ ስለ ብሔር ወይንም ስላለህ ፖለቲካ አመለካከት ቦታ የለውም። ምክንያቱም የማህበሩ ምስረታ ምድራዊ መንግስትን ለማገልገል ሳይሆን ሰማያዊ መንግስትን መስበክ ስለሆነ። ምድራዊ ስልጣንን ለማስገኘት ሳይሆን የማታልፈውን የእግዚአብሔር መንግስት ለማውረስ ስለሆነ። ስለዚህ የሐጥያት ስር የሚባሉት ዘረኝነት፣ ወገኝተኝነት፣ገንዘብ ወዳድነት፣መለያየት የመሳሰሉት በማህበሩ ውስጥ ቦታ የሚሰጣቸው ጉዳዮች አይደሉም። ስለዚህ እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት እና የእግዚአብሔር አገልጋዮች የሚገኙበት ማህበር ነው። ከየትም ይምጣ ከየት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጅ ከሆነ የዚህ ማህበር አባል መሆን ይችላል። ማህበሩን የማታውቁት አለ ብዬ መናገር ባልደፍርም ካላችሁ ግን ያለው እውነት ይሄ ነው።
ማህበረ ቅዱሳንን ማፍረስ የተፈለገበት ዋናው አላም ለመንግስት ፖሊሲ የተመቸ ስላልሆነ ነው። እንደ መንግስት ሃሳብ በዘር የተደራጀ ቢሆን ኖሮ አልያም የመንግስት ደጋፊ ሆነው መንግስት የሚፈልገውን የማለያየት ስራ የሚሰሩ ቢሆኑ ኖሮ ወይንም እንደ መንግስት ሃሳብ ኢትዮጵያን የማፍረስና  ታሪኳን የማጥፋት ስራ የሚሰሩ ቢሆኑ ኖሮ የኦርቶዶክስ አማኝ በሙሉ ወደዚህ ማህበር እንዲገቡ መንግስት ያስገድድ ነበረ። ይሄ ባለመሆኑ ዘረኝነት የእግዚአብሔርን መንግስት አይወርስም ታሪካችንንም ለአፍሪካ ብሎም ለአለም ህዝብ ምሳሌ ነው በማለት አንድነት፣ ፍቅር፣ የእግዚአብሔር መንግስት የሚሰበክበት ማህበር በመሆኑ ዘረኝነት ነብሳቸው ትጸየፋዋለች ጥላቻንም አያስተምሩም ፍቅር ቤታችው፣ ፍቅር አገራችው፣ ፍቅር አምላካችው ነው በመሆኑ መንግስት ለማፍረስ ተነሳ። እንደተለመደው መንግስት እጄ የለበትም ለማስባል ሁሉንም በራሳቸው ሰዎች ከኋላ ሙሉ ድጋፍ በመስጠት  የሚያስመታው። ነገሮች አቅጣጫውን ስተው ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሞት መቀልበሻው ሲጠፋውና ሲጨንቀው ደግሞ እርቅ ይላል። አቡነ ማቲያስ በማህበረ ቅዱሳን ላይ የመነሳታቸው ሚስጢር 100% የመንግስት መዶሻ ሆነው ማህበሩን ለመምታት የተነሱ አባት ናቸው እንጂ ለቤተክርስትያን በመቆርቆር ከቤተክርስትያን አባቶች ጋር ተማክረው  የቤተክርስትያንን መሰረቷን ለማጥበቅ የተነሱ እንዳልሆነ ጥንቅቀን እናውቃለን።
የቤተክርስትያንን ህልውና የሚፈታተንና ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነገር ከፊታችን ቀርቧል እኛ ልጆቿ ከእግዚአብሔር ዋጋ የምናገኝበት አልያም የምናጣበት።
ይሄንን ሁላ የምለው የማህበረ ቅዱሳን አባል ሆኜ አይደለም ነገር ግን እንደ ቤተክርስትያን ልጅኔቴ የቤተክርስትያን ጉዳይ ስለሚያገባኝ ነው። ስለ ቤተክርስትያን ጉዳይ ዝም ማለት አየር ሳትተነፍስ መኖር አንድ ነው። ስጋዊ ህይወትህ ማኖር ካለብህ ለደቂቃም ማጣት የማትችለው ነገር አየር ነው። ነፍስህን ለዘላለም በእግዚአብሔር እቅፍ ማኖር የምትችለው ቤተክርስትያን ስትኖር ብቻ ነው። ስለዚህ ስለ ቤተክርስትያን ዝም አንልም።
ከተማ ዋቅጅራ
28.01.2016

No comments:

Post a Comment

wanted officials