Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, February 1, 2016

ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳዎች ይልቅ የሙጋቤ መልእክት ትኩረት አግኝቷል



ከአፍሪካ ህብረት አጀንዳዎች ይልቅ የሙጋቤ መልእክት ትኩረት አግኝቷል
===============
የአፍሪካ ህብረት የሊቀመንበርነት ጊዜያቸውን ያጠናቀቁት የዚምቧቡዌው ፕሬዘዳንት ሮበርት ሙጋቤ በ26ኛው የመሪዎች ስብሰባ ለተተኪያቸው ቦታቸውን ከመልቀቃቸው አስቀድሞ ህብረቱን በመወከል በተባበሩት መንግስታት፣በነጮችና በባራክ ኦባማ ላይ ጠንከር ያለ ወቀሳ ሰንዝረዋል፡፡
ሙጋቤ ንግግር ለማድረግ ወደ ተዘጋጀላቸው ቦታ ሲያመሩ ከአጋሮቻቸው ደመቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፣ ፕሬዘዳንቱ በንግግራቸው ከተለመደው ከፋ ባለ መልኩ ምዕራባዊያንን፣ነጮችንና የአሜሪካውን ፕሬዘዳንት አብጠልጥለዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ ባንኪ ሙን የ91 ዓመቱ ሙጋቤን ንግግር እያደመጡ በተቀመጡበት ወንበር በጭንቀት ተውጠው ተስተውለዋል፣ ‹‹ሞተዋል አልያም በጠና ታመዋል›› የሚሉ ወሬዎች ሲነዙባቸው የሰነበቱት ሙጋቤ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ካላገኘች ድርጅቱን ለቅቃ እንደምትወጣ ዝተዋል፡፡
‹‹የጸጥታው ምክር ቤት እንዲሻሻል ደግመን ደጋግመን ጠይቀናል››ያሉት ተሰናባቹ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ‹‹አፍሪካዊያን ለውጥና ውጤት በሌለው የድርጅቱ ወሬ ተሰላችተዋል››ብለዋል፡፡
አፍሪካዊያን እውነተኛ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባላት አይደሉም ያሉት ሙጋቤ ‹‹አባላቶቹ ባለነጭ ቆዳዎቹ ብቻ ናቸው፣ አንድ ቀን ግን አፍሪካዊያን ከወሰኑ ከድርጅቱ ጋር ገደል ግቡ ብለው ሊወጡ ይችላሉ››ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
‹‹የተባበሩት መንግስታት በህይወት እንዲቆይ ከተፈለገ እኛ አፍሪካዊያን እኩል መብት ያለን አባላቱ መሆን አለብን››በማለት ተናግረዋል፡፡ሙጋቤ ጣታቸውን ወደ ባንኪሙን ቀስረውም ‹‹እርስዎ ጥሩ ሰው ነዎት ነገር ግን እኛ እንዲታገሉልን አናስገድድዎትም፣ ግዳጅዎም ይህ አይደለም ነገር ግን እኛ ስለራሳችን ማንነትና ስብዕና እንደ አፍሪካዊ እንታገላለን››ብለዋል፡፡
ለተባበሩት መንግስታት አድርሱልን በማለትም ሙጋቤ ባንኪ ሙንን ‹‹አፍሪካዊያንም መንፈስ ሳይሆኑ አለም የምትገባቸው ሰዎች መሆናቸውን ንገሩልን››ብለዋቸዋል፡፡
የድርጅቱ ዋና ጽህፈት ቤት በኒውዮርክ መገኘቱን ‹‹ስህተት›› ያሉት ሙጋቤ ዋና ጽህፈት ቤቱ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር ባላቸው አገሮች ለምሳሌ በቻይና፣በህንድ ወይም በአፍሪካ አህጉር መገኘት ይገባው ነበር ብለዋል፡፡
አፍሪካዊያንና ሌሎች በኒውዮርክ መገኘታቸውን በመጥቀስም ‹‹ነገር ግን በዚያ ነጫጭ ፊቶችና ፒንክ አፍንጫ ያላቸው ከእኛ ቀጠለው ይገኛሉ ፣እነርሱ ከእኛ ጋር በቁጥር ሲነጻጸሩ ምን ያህል ይሆናሉ?›› በማለት ባንኪሙንን ጠይቀዋል፡፡
ሙጋቤ ባንኪሙንን በንግግራቸው መሐልም ማወደሳቸው አልቀረም ‹‹አፍሪካ ኢቦላን እንድትዋጋ፣ሽብርተኝነትን እንድትከላከልና ሌሎች ቀውሶች ባጋጠሟት ወቅትም ከአፍሪካዊያን ጎን መቆምዎን አንዘነጋም›› ብለዋቸዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማን ‹‹የነጮች አሻንጉሊት›› በማለት የወረፏቸው ሙጋቤ ‹‹ነጮቹ አፍሪካዊያንን በየውቅያኖሱ ሲወረውሩ እንደነበር የዘነጉ ጥቁሮች በተለይም ኦባማ አሁን ጥቁሮች ነጻ ሰዎች እንደሆኑ ያስባሉ፣ ነገር ግን እርሱ (ኦባማ) ምንድን ነው ? የእነርሱን ቋንቋ ለመናገር ድምጽ የተሰጠው? የእኛን ሳይሆን የእነርሱን እንቅስቃሴ የኮረጀ አይደለምን? እነርሱ (ነጮች)እስካሁን ድረስ የበላይ ናቸው››፡፡
ሙጋቤ ጥቁሮች በአሜሪካ እስካሁን ድረስ የበታቾች መሆናቸውን በመጥቀስ ትምህርትና የጤና መድህን ዝቅተኛ በሆነበት ኒውዩርክ ውስጥ በሚገኘው ሃርለም በብዛት እንደሚኖሩ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ጥቁሮች በመንገድ ላይ በጥይት ይመታሉ ፣ ማንም ይህንን ለመናገር የሚፈልግ አይመስልም፡፡ ነገር ግን እነርሱ(ነጮቹ) ስለ እኛ መናገር ይፈልጋሉ››ብለዋል፡፡
የቅኝ ግዛት ዘመን ካበቃ በኋላ እንኳን የቀድሞዎቹ ቅኝ ገዢዎች በሁሉም የአፍሪካ ክፍሎች በእርዳታ ድርጅቶች ስም እንደሚገኙ ያወሱት ሙጋቤ ‹‹ሰላዩችና አስመሳዩች ቢሆኑም አንዳንዶች እኛን ለመደገፍ ነው እዚህ የሚገኙት ሲለ ይደመጣሉ፡፡ሌላው ቀርቶ የስርዓት ለውጥ እንዲደረግ ታጣቂ ቡድኖች መካከልም ይገኛሉ››በማለት የነጮችን ጣልቃ ገብነት ተቃውመዋል፡፡
አስር ደቂቃ ለንግግር ተሰጥቷቸው የነበሩት ሙጋቤ ለአንድ ሰዓት ያህል በመድረኩ ላይ ቆይተዋል፡፡በንግግራቸው ማጠቃለያም የሊቀመንበርነት ቦታቸውን ለተረከቡት ለቻዱ ፕሬዘዳንት ኢድሪስ ዴቤይ ‹‹አጠገብዎ የምገኝ በመሆኑ በፈለጉኝ ሰዓት ሊደውሉልኝ ይችላሉ፣ አምላክ ከእኛ በፊት የሄዱትን እንድቀላቀል እስኪጠራኝ ድረስ እዚሁ ነኝ››ብለዋቸዋል፡፡
ሙጋቤ ወደ መቀመጫቸው ከማምራታቸው አስቀድሞም በጥቁሮች የስልጣን ሰላምታ ጉባኤውን ተሰናብተዋል፡፡የደቡብ አፍሪካው ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ ሲቀሩ ለሙጋቤ ቀሪዎቹ ፕሬዘዳንቶች ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው አክብሮታቸውን አሳይተዋቸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials