Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, December 6, 2015

‹‹ጉራጌ ሲሰርቅና ሲያጭበረብር እንጂ ሲታገል አያምርበትም እየተባልኩ እደበደብ ነበር›› 9ኛ ተከሳሽ


‹‹ጉራጌ ሲሰርቅና ሲያጭበረብር እንጂ ሲታገል አያምርበትም እየተባልኩ እደበደብ ነበር›› 9ኛ ተከሳሽ



እነ ዘላለም ወርቃገኘሁ ተጨማሪ መከላከያ ምስክሮቻቸውን አሰሙ
‹‹ጉራጌ ሲሰርቅና ሲያጭበረብር እንጂ ሲታገል አያምርበትም እየተባልኩ እደበደብ ነበር›› 9ኛ ተከሳሽ

በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር


በፌደራል አቃቤ ህግ የሽብርተኝነት ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው እየታየ የሚገኙት እነ ዘላለም ወርቃገኘሁ ተጨማሪ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን ዛሬ ህዳር 24/2008 ዓ.ም አስደምጠዋል፡፡


በዚህ መዝገብ 9ኛ ተከሳሽ የሆነው አቶ ባህሩ ደጉ 3 መከላከያ ምስክሮቹን ያስደመጠ ሲሆን፣ የተከሳሽነት ቃሉንም ለፍርድ ቤቱ ሰጥቷል፡፡ አቶ ባህሩ በተከሳሽነት ቃሉ ላይ እንደጠቀሰው ማዕከላዊ ፌደራል ወንጀል ምርመራ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሞበታል፤ ቃሉንም በግዳጅ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡
አቶ ባህሩ ደጉ ለፍርድ ቤቱ እነዳስረዳው ማዕከላዊ እያለ ራቁቱን ተደብድቧል፤ ከድብደባ ብዛት ሽንቱን መቆጣጠር ተስኖት እንደነበር በማውሳት የገዛ ሽንቱን እንዲጠጣ ተገድዷል፡፡ በተጨማሪም አቶ ባህሩ ‹‹የግንቦት ሰባት መሪ ብርሃኑ ነጋ ምንህ ነው? ከአንዳርጋቸው ጽጌስ ምን አለህ? ብርሃኑ ዘመድህ ነው?›› የሚሉ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች እየቀረቡለት በማያውቀው ነገር ሲሰቃይ እንደነበር ለችሎቱ አስረድቷል፡፡
አቶ ባህሩ ደጉ በማንነቱ ምክንያትም ስቃይ እንዳሳለፈ በማውሳት፣ ‹‹ከጉራጌ መወለድ ወንጀል ነው እንዴ?›› ሲል በችሎት ፊት ጠይቋል፡፡ ‹‹ጉራጌ ሲሰርቅና ሲያጭበረብር እንጂ ሲታገል አያምርበትም እየተባልኩ እደበደብ ነበር›› ያለው አቶ ባህሩ፣ ‹‹የደም ስርህን በጥሰን እንገልሃለን፤ ፖሊሱ፣ አቃቤ ህጉ፣ ፍርድ ቤቱ፣ ደህንነቱ…ሁሉም የኛ ነው፤ አንተን 20 አመት እናስርሃለን›› እየተባለ ስቃይ እንደተፈጸመበት በማስረዳት በምርመራ ወቀት የሰጠው ቃል ተገድዶ የሰጠው መሆኑን ፍርድ ቤቱ እንዲረዳለት አሳስቧል፡፡
9ኛ ተከሳሽ ባህሩ ደጉ የተከሳሽነት ቃሉን ከሰጠ በኋላ ሦስት መከላከያ ምስክሮችን አሰምቷል፡፡ ከምስክሮቹ መካከል በዚሁ መዝገብ 1ኛ ተከሳሽ ዛላለም ወርቃገኘሁ እና ሌላኛው ምስክር ጦማሪ ዘላለም ክብረት ተከሳሹ ‹‹ለሽብር ወንጀል ስልጠና ሊወስድ ነበር›› በሚል ስለቀረበበት ክስ የስልጠናውን አይነትና የአሰልጣኞችን ማንነት በማብራራት ስልጠናው ለሽብርተኝነት ድርጊት ሳይሆን በታወቁ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የሚሰጥ ግልጽ ስልጠና እንደነበር አስረድተዋል፡፡ 3ኛ ምስክር በበኩላቸው ተከሳሹ ማዕከላዊ ወንጀል ምረመራ በነበረበት ወቅት አብረው ታስረው እንደነበር በመግለጽ ይፈጸምበት የነበረውን አሰቃቂ ምርመራ በተመለከተ የሚያወቁትን መስክረዋል፡፡ እኒህ ምስክር ተከሳሹ ሌሊት ለምርመራ በሚል እየተጠራ ድብደባ ይፈጸምበት እንደነበር አስረድተዋል፡፡
በዚሁ መዝገብ 1ኛ ተከሳሽ በምስክርነት የጠሯቸው አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ የሺዋስ አሰፋ እና ዳንኤል ሺበሽ ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲቀርቡ በተደጋጋሚ ትዕዛዝ ከፍርድ ቤቱ ቢሰጥም እስካሁን አለመቅረባቸው ታውቋል፡፡ በዚህም ፍርድ ቤቱ ዛሬም ሌላ ትዕዛዝ በመስጠት ማረሚያ ቤቱ እስካሁን ያላቀረበበትን ምክንያት ገልጾ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርባቸው ታዝዟል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials