ኀዳር ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- መንግስት የአዲስ አበባን አስተዳደር ለማስፋት ያዘጋጀው አዲሱ የመሬት ካርታ ወይም ማስተር ፕላን ተግባራዊ እንደሚደረግ የመንግስት ባለስልጣናት የተለያዩ መግለጫዎችን መስጠታቸውን ተከትሎ፣ የክልሉ ተማሪዎች ተቃውሞአቸውን እየቀጠሉ ሲሆን፣ በአምቦ፣ ኤሉባቦር፣ በምእራብ ወለጋና በሌሎችም የተካሄዱት ተቃውሞዎች ወደ ሃሮማያ (አለማያ)ዩኒቨርስቲ ተዛምቶ፣ በተማሪዎችና በፖሊስ መካከል በተነሳው ግጭት፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ተማሪዎች ተጎድተው ሆስፒታል ገብተዋል።
ተማሪዎቹ ተቃውሞአቸውን በሰላም በማሰማት ላይ እያሉ የፌደራል ፖሊስ አባላት ወደ ዩኒቨርስቲው ግቢ በመግባት ድብደባ በመጀመራቸው ከ30 ያላነሱ ተማሪዎች ተጎድተው ወደ ህክምና መወሰዳቸውን የአይን ምስክሮች ገልጸዋል። እስካሁን የሞቱ ተማሪዎችን ቁጥር በትክክል ለማወቅ ባንችልም፣ የተወሱ ተማሪዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድተው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። አንድ የፌደራል ፖሊስም በድንጋይ መመታቱንና ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ተቃውሞ መነሳቱን ተከትሎ የተወሰኑ ተማሪዎች ግቢው በመልቀቅ ወደ ሃረርና ድሬዳዋ ሄደዋል።
በሌላ በኩል ዬዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት የሆኑት ፕ/ር ጨመዳ ፊኒንሳ ከዩኒቨርስቲው አመራሮች፣ ከኦህዴድ አባላትና ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ባደረጉት ስብሰባ፣ ተማሪዎች ለተቃውሞ ሰልፍ ሲወጡ መወሰድ ስለሚኖርበት እርምጃ ግልጽ የሆነ መመሪያና እቅድ ባለመተላለፉ ፣ መቸገራቸውን ለተሰብሳቢዎች ገልጸዋል። የስብሰባው ተሳታፊ ነበሩ የኢሳት ምንጮች በድብቅ ቀርጸው በላኩት ድምጽ፣ የተለያዩ ተወካዮች፣ ፕ/ሩ ተቃውሞ እንደሚነሳ እያወቁ መረጃ አስቀድመው ባለማሳወቃቸው ወቀሳ አቅርበዋል። ይሁን እንጅ ፕ/ር ጨመዳ፣ ተቃውሞ መነሳቱን የሰሙት እሁድ ሌሊት መብራት ጠፍቶ በነበረበት ወቅት መሆኑን፣ ዛሬ ሁኔታው መባባሱን ገልጸዋል።
ተቃውሞዎች ሲነሱ ፣ የፖለቲካ ስራ በመስራት እናሳምናለን ቢባልም፣ ተማሪዎች አናምንም ካሉ ስለሚወሰደው ቀጣይ እርምጃ ግልጽ የሆነ እቅድ ባለመኖሩ፣ ግራ መጋባታቸውን ተናግረዋል መንግስት የአዲስ አበባን አዲሱን ካርታ ወደ ተግባር ከመቀየር ወደ ሁዋላ እንደማይል አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment