(ዘ-ሐበሻ) አንደኛ ሳምንቱን የያዘውና በድጋሚ የተነሳው የኦሮሞ ተማሪዎች ተቃውሞ በተለያዩ ከተሞች የቀጠለ ሲሆን ዛሬ ጠዋት የአጋዚ (ፌደራል ፖሊስ) ሠራዊት አባላት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲን ጥሰው በመግባት በርካታ ተማሪዎችን በድብደባ አቆሰሉ::
የዘ-ሐበሻ የዜና ምንጮች እንደሚሉት በቀድሞዋ ሃገረ ማርያም ወረዳ ስር በነበረችው ቡሌ ሃራ ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪዎች አዲሱን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በመቃወም ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ሲያሰሙ የዋሉ ሲሆን ሄልሜትና ድንጋይ መከላከያ የታጠቁ ፌደራል ፖሊስ ግቢውን ጥሰው በመግባት ክፍተኛ ቅጥቀጣ አድርገውባቸዋል::
በተማሪዎቹ ላይ ፖሊስ እየፈጸመ ያለውን ግድያና ዱላ እንዲያቆም ተቃዋሚዎቹ ሲጠይቁ የዋሉ ቢሆንም ሰሚ አላገኙም:: ለዘ-ሐበሻ እንደደረሰው መረጃ በቡሌ ሃራ ዩኒቨርሲቲ ከተማሪዎቹ በተጨማሪ በአስተማሪዎች ላይም ከፍተኛ የሆነ ጉዳት ደርሷል::
እስካሁን ድረስ በቡሌ ሃራ ዩኒቨርሲቲ ፌደራል ፖሊስ ባደረሰው ከባድ ጉዳት የሞተ ተማሪ እንዳልተመዘገበ ጨምሮ የደረሰን መረጃ ይጠቁማል::
No comments:
Post a Comment