ትናንት እና ዛሬን ያሳለፍኩት አዳማ ከተማ ነበር፡፡
ትናንት ከአቶ በቀለ ገርባ ጋር በአዩ ኢንተርናሽናል ሆቴል በአካል ተገናኝተን፣ ከሁለት ሰዓታት በላይ ተጨማሪ ቃለ ምልልስ (ለ‹‹አዲስ ገጽ›› መጽሔት) አድርገን እና በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ኢ-መደበኛ ሀሳቦችን በስፋት ተወያተናል፡፡
አቶ በቀለ ነጻ አመለካከት ያላቸው፣ ሀሳባቸውን በቀላሉ ማሰረዳት የሚችሉ፣ ነገሮችን በተለያዩ ቀላል መንገዶች ማስረዳት የሚመርጡ፣ ሰውን በአስተውሎት የሚያዳምጡ፣ በጨዋታ መሀል ቀልዶች ጣል የሚያደርጉና ጨዋነትን የተላበሱ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ በተለይ አቶ አባዱላ ገመዳን በሚመለከት የተናገሯትን ቁም ነገር አዘል ቀልድ መቼም ቢሆን አልረሳትም፡፡ በድንገት ስቄያለሁ፤ አብረንም ስቀናል፡፡
……በዛሬው ዕለት መድረክ በአዳማ የጠራውን ሰልፍ እንደጋዜጠኛ ለመመልከት ከጥዋቱ 02፡30 ጀምሮ ከተማዋን ለመቃኘት ጥረት አድርጌአለሁ፡፡ በጥዋቱ ወደከተማዋ መግቢያ አካባቢ፣ በዋናው መንገድ ግራና ቀኝ፤ ዱላ የያዙ ፖሊሶችን ማየት ጀምሬ ነበር፡፡ ከቁርስ በኋላ፣ ሠዓቱ ገፋ ብሎ፣ ቀኑ መረፋፈድ ሲጀምር፣ በከተማዋ በርካታ ፖሊሶችን መመልከት በጣም ቀላል ነበር፡፡ ዋናውን መንገድ በእግሬ በመጓዝም ስቃኘው፣ የፖሊሶች ቁጥር በጣም እየጨመረ መጣ፡፡ ከዋናው መንገድ ግራና ቀኝ ወደውስጥ በሚስገቡ የአስፋልትና ፒስታ መንገዶች ውስጥም ፖሊሶች ተሰብስበው አካባቢውን በንቃት ይከታታላሉ፡፡ ሁለት የፖሊስ መኪኖች፣ በአንዱ መኪና ላይ አድማ በታኝና ከላይ እስከታች የመከላከለያ ጭንብል የለበሱ (ቁጥራቸው 8 የሚሆን)፣ መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮች በግራ በቀኝ መሳሪያቸውን አነጣጣረው በመቀመጥ በዋና መንገዱ ላይ በፍጥነት ይሽከረከራሉ፡፡ በሌላኛው መኪና ደግሞ ወታደራዊ ልብስ የለበሱ አልሞ ተኳሾች (8 የሚሆኑ) ተጭነው በሁለት ረድፍ እንደተቀመጡ መሳሪያቸውን በማነጣጠር ከተማዋን ይዞሯት ነበር፡፡ እነዚህን ወታደሮች በጥቂት ሜትሮች ርቀት ላያቸው ችያለሁ፡፡ እጃቸው የመሳሪያ ቃታ ላይ አርፎ ፊታቸው ቅጭም ብሎ እንደተኮሳተረ ነበር፡፡ በግሌ የጭካኔ ስሜት በገጽታቸው ላይ አንብቤያለሁ፡፡ ሌሎች የፖሊስ እና የመንግሥት መ/ቤት መኪኖችም ፖሊሶችን ጭነው ከተማዋን ሲቀኙ አስተውያለሁ፡፡
ዱላ ሳይሆን ‹‹ወፍራም አጠና የያዙ›› ብል የሚቀለኝ በርካታ ፖሊሶች አዳማን ከረፋዱ ጀምሮ እስከቀትር ድረስ ሲያስጨንቋት ነበር፡፡ የጎማ ዱላ የያዙ ፖሊሶች ቁጥራቸው አነስተኛ የነበረ ሲሆን ፖስታ ቤት አካባቢም ፌሮ ብረት የያዘ አንድ ፖሊስ በአይኔ ተመልክቻለሁ፡፡ ሰልፉ ይደርግበታል ወደተባለው ቦታ መግባት ግን እጅግ አስቸጋሪ ነበር፡፡
የሰልፉ አንዱ አስተባባሪ የነበሩትን አቶ በቀለ ገርባን ቀጥር አካባቢ በሞባይል ስልካቸው ላይ አገኘኋቸውና ስለጉዳዩ ጠየኳቸው፡፡ ሰልፉ መበተኑን ከጠቆሙኝ በኋላም፣ ‹‹ሰልፍ ማድረግ አትችሉም፡፡ አልተፈቀደላችሁም፡፡ ሰልፉን የሚጠብቅ በቂ የፖሊስ ሃይል የለንም፡፡ ከላይ የለበስከውን ቲ-ሸርት አውልቅ …›› ተብዬ ነበር በማለት አስረዱኝ፡፡ አያይዘውም ‹‹ሰልፍ ለመጠበቅ የፖሊስ ዕጥረት አለብን አሉን፤ ሰው ለመደብደብ ግን የፖሊስ እጥረት የለባቸውም›› ሲሉ በከተማው አስተዳደር ድርጊት ማዘናቸውን ነገሩኝ፡፡
…ከሰዓት በኋላ በከተማዋ የነበሩት ፖሊሶችና ወታደሮች ቁጥር ቢያንስም አልፎ አልፎ በከተማዋ ጎዳናዎች ላይ ይታዩ ነበር፡፡ ከወዳጄ ፍቃዱ በቀለ ጋር አመሻሽ 11፡00 ሰዓት ገደማ በአዳማ አዲስ አበባ የፍጥነት መንገድ ከአዳማ ተጉዘን የአዲስ አበባውን መግቢያ መንገድ እንደጨረስን፣ በርካታ መኪኖች ተደርድረው ሁሉም ሳፋሪዎች ከመኪና እየወረዱ ሲፈተሹ ተመለከትን፡፡ እኛም የተሳፈርንበት መኪናም ቆሞ ከወረድን በኋላ ተፈትሸን በመግባት ሲመሽ አዲስ አበባ ገብተናል፡፡
እንግዲህ በሁለት ቀናት በአዳማ በነበረኝ ቆይታ እንደጋዜጠኛ የታዘብኩትን በአጭሩ እንዲህ አስነብቤያችኋለሁ፡፡
መልካም ምሽት
No comments:
Post a Comment