ሰማያዊ ፓርቲ ለተገደሉት እና ጉዳት ለደረሰባቸው አጋርነቱን ገለፀ
• ከመድረክ እና ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ለመስራት ወስኗል
ሰማያዊ ፓርቲ ዛሬ ታህሳስ 3/2008 ዓ.ም በካሄደው የብሄራዊ ምክር ቤት ስብሰባ ከ‹‹ማስተር ፕላኑ›› ጋር በተያያዘ ለተገደሉትና ጉዳት ለደረሰባቸው የህሊና ፀሎት ያደረገ ሲሆን አጋርነቱን መግለፁንም የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸው ከበደ ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡
የፓርቲው ብሄራዊ ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ውይይት ያደረገ ሲሆን የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን በተቃወሙት ኢትዮጵያውያን ላይ መንግስት እየወሰደ ያለው ኢ-ሰብአዊ እርምጃ እና ለሱዳን በሚሰጠው መሬት ላይ ውይይት አድርጓል፡፡ ውይይቱ ከመጀመሩ በፊትም ማስተር ፕላኑን በመቃወማቸው በመንግስት የፀጥታ ሀይሎች ለገደሉትና የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው የህሊና ፀሎት እንደተደረገ ሰብሳቢው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡
ማስተር ፕላኑ አርሶ አደሮችን የሚያፈናቅል እና ለመሬት ቅርምት የሚዳርግ መሆኑን በመግለፅ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን በማሰማታቸው በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ለተገደሉትና ጉዳት ለደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን አጋርነት የገለፀው ሰማያዊ ፓርቲ በቀጣይነት በጉዳዩ ላይ ሰፋ ያለና የተደራጀ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግም ተገልጾአል፡፡ ፓርቲ ከመድረክ ጋር ለመስራት ውይይት መጀመሩን የገለፁት አቶ ይድነቃቸው ከበደ በቀጣይም ከመድረክና ከሌሎች በወቅታዊ ችግሮች ላይ ለመስራት ፈቃደኛ ከሆኑ ፓርቲዎች ጋር እንዲሰራ ብሄራዊ ምክር ቤቱ መወሰኑን ገልፀዋል፡፡ ሰማያዊ ፓርቲ ኀዳር 27 ቀን 2008 ዓ.ም ‹‹በገዛ አፈ-ሙዙ መቃብሩን የሚቆፍር የሽንፈትን ጽዋ ይጎነጫል !›› በሚል ባወጣው መግለጫ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ ባሰሙት ኢትዮጵያውያን ላይ መንግስት የወሰደውን ኢ-ሰብአዊ እርምጃ ማውገዙ ይታወሳል፡፡
በነገረ - ኢትዮጵያ
No comments:
Post a Comment