Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, December 13, 2015

ኢትዮጵያዊያኑን ከዳር እስከ ዳር የሚያሳትፍ ትግል እንዲሆን በማድረግ መልዕክት በማስተጋባት የፖለቲካ አመራር ብቃታችሁን አሳዩን

ዘሬን ዘሬን ስንል ወይ ከሰው አልያም ከፈጣሪ ድል የለም። ፍቅር አንድ ያላደረገውን ህዝብ መከራ አንድ ያደርገዋል መከራ አንድ ያላደረገው ህዝብ ግን ለመጥፋት እራሱን ያዘጋጀ ህዝብ ብቻ ነው።
AMBO 3
ፓለቲካውን እንመራለን የምትሉ አካሎች ፖለቲካዊ ትንታኔ እንሰጣለን የምትሉ ሙሁሮች የህዝብ ህመም ይመማማቹ የህዝብ ስቃይ ይሰማችሁ የህዝብ መከራ ይረዳችሁ እናንተ ፖለቲከኞች ትግሉን ከሁኔታዎች እና ከግዜው ጋር በማጣመር እስትራቴጂካዊ ስልት በመቀየስ ግፈኛው እና አንባ ገነኑ ወያኔ የሚወገድበትን ስልት በመንደፍ ትግሉን አገር አቀፍ ትግል ኢትዮጵያዊያኑን ከዳር እስከ ዳር የሚያሳትፍ ትግል እንዲሆን በማድረግ መልዕክት በማስተጋባት የፖለቲካ አመራር ብቃታችሁን ታሳዩን ዘንድ ያስፈልጋል። ሃዘንና መከራ በአገራችን አሰፍኖ ህዝብን ከህዝብ አፋጅቶ ስልጣኑን ለማርዘም የሚራወጠውን ወያኔ የሞት መረብ የዘረጋልንን ወያኔ በመለያየት ስንጮህ፣ ስናለቅስ፣ ሰልፍ ስንወጣ፣ ወያኔ ሲያተራምሰን እኛ ስንተራመስ እንከርማለን እንጂ ነጻነት የሚባል ነገር አይታሰብም ወያኔን ከስልጣን ማስወገድ የሚባል ነገር አይታለምም። ግና ፖለቲከኞቹ ስለ ህዝብ እና ስለ አገር አሳቢ ከሆናችሁ የአንድነት ጥሪ አድርጉ የአንድነት ድምጽ  አሰሙ የአንድነት ዜናን አሰሙን ያኔ ወያኔ ለኛ ብሎ ባዘጋጀው የሞት እና የመጠፋፋት መረብ እራሱ ይገባል በአንድነት መሃል የህዝብ ድል አለ  በአንድነት መሃል የእግዚአብሔር ኃይል አለ።
አንድ እውነት አለ በኢትዮጵያ ውስጥ ሰፊውን ቁጥር የያዙት ሁለት ወንድማማች ህዝብ አሉ እነርሱም ኦሮሞ  እና አማራ ናቸው። የሁለቱ ጸብ ለኢትዮጵያ መጥፋት መሰረቶች ናቸው። የሁለቱ ጸብ አሸናፊም ተሸናፊም የማይኖርበት ነገር ግን በቃላት የማይገለጽ ጥፋት የሚደርስበት እንደሆነ መገመት ይቻላል። የሁለቱ ወንድማማቾች ጸብ ለሁለቱም ምንም አይጠቅምም ሁለቱም የሚያገኙት አንዳችም ትርፍ የለም ይልቁንም ዘወትር ለማጣላት እና ለማጋጨት የሚተጋው ወያኔ ግቡን የሚመታለት ድሉንም ለዘላለም የሚያበስርበት ንግስናውንም እንዳለው 100 አመት የመግዛቱ ሃሳብ የሚሳካለት ይሄ ነው። ያኔ እንደ ባሪያ ማድረግ ይችላል እግዚአብሔርንም የሚፈሩ ሰውንም የማያፍሩ ህግንም የማያከብሩ ስለሆኑ አንዱን አማራ አንዱንም ኦሮሞ  አድርገው እንደ ጥማድ በሬ ተጠቅመውብን ልማት ልማት ለሚሉት እያረሱብን ያለሙብናል ወገኔ ቆም ብለን እናስብ ያኔ እንዲህ ብናደርግ ብለን ከመቆጨታችን በፊት አሁን ነቅተን ጥፋታችንን በጋራ እንከላከል።
Oromo
ሁለተኛውኛው እና ዋንኛው እውነት ደግሞ ሁለቱ ህዝቦች ከተስማሙ የትኛውም ሃይል ሊያሸንፋቸው ያማይችሉ የጸኑ ግንቦች ናቸው። በዚህ ህዝባዊ አመጽ በተነሳበት እንቅስቃሴ መሃል ጠላትን የሚያስደነግጥ እና የሚያሳፍር ወዳጅን ደግሞ ደስ የሚያሰኝ ዜን ሊነገር ይገባል። በዚህ ግዜ ነው ከዳር እስከ ዳር ቀፎው እንደተነካ ንብ ግልብጥ አስብሎ  የሚወጣ ኢትዮጵያን አንድ የሚያደርግ መፈክር ይዞ መወጣት ያለበት። በዚህ ግዜ ነው የፖለቲካውን ስልት ከሁኔታዎች ጋር አመቻችቶ  ሁላችንም አንድ ነን የሚለውን መፈክር ይዘን መነሳት ያለብን። በዚህን ግዜ ነው ኦሮሞ ስለ ጎንደር ህዝብ የጎንደር ህዝብ ስለ ኦሮሞ ህዝብ ጥቃት መጮህ ያለበት። ያኔ ጎንደሬው ኦሮሞ  ነው ኦሮሞው ጎንደሬ ነው ይሄኔ ወለጋም ሲሸፍት ጎጃምም ይሸፍታል አንቦ እንቢ ሲል ወሎው እንቢ ይላል አዲስ አበቤዎች ሲነሱ አዋሳዎች ይነሳሉ አዳማዎች አልገዛም ሲሉ ድሬዳዎች አንገዛም ይላሉ የአንዱ ህመም ሁሉንም እንዲሰማው የአንዱ መደፈር የአገር መደፈር ስሜት እንዲፈጥር የአንድነት አገር እንዲኖረን የአንድነት ድምጽ ያስፈልጋል። የወያኔ ራእይ አማራ እና ኦሮሞን አጋጭቶ እርስ በራስ ሲተላለቆ  100 አመት ያለምንም ተቀናቃኝ እገዛለው የሚለውን ተስፋ እንክትክቱን ማውጣት የሚቻለው እና እንኳን 100 አመት አንድ አመት መግዛት አትችልም የሚለውን ሃሳብ ይዘን መነሳት የምንችለው አንድ ስንሆን ብቻ ነው። ኦሮሞን እና አማራ በጦርነት እሳት ውስጥ ማግዶ በመርዝ የተለወሰ ማር ለአማራውና ለኦሮሞ  በመስጠት ለህዝባችን ሞት ደግሶ የተቀመጠውን ወያኔ ሞቱ የሱ ማድረግ የምንችለው በአንድነት ስንቆም ብቻ ነው። ነገ ከነገ ወዲያ ልንሰማው ይገባል ትግሉ ከዳር እስከ ዳር በኢትዮጵያ በሙሉ አስተጋብቶ ዘጠኙም ክልሎች በፖለቲካ መሪዎቻቸው አማካኝነት ግፍ ይብቃ በደል ይብቃ ውሸት ሰለቸን ሁላችን አንድ ነን አንድነት ሃይል ነው ብለው በመነሳት ህዝባችንን ለመቅበር በቆፈረው ጉድጓድ መጨረሻውን ቀብሩን ለወያኔ ማድረግ የምንችለው አንድ ስንሆን ብቻ ነው።
ጠላት ማፈር ያለበት ሰአት ለይ ነን እየነጣጠለ  ሊያጠፋን ያሰበውን አንድ ሆነን ማሳየት እና ጠላትንም መመከትም ሆነ ማጥፋት እንደምንችል ማሳየት አለብን። ገዳይና ዘራፊ አሳሪ እና አፋኝ ማን እንደሆነ ከታወቀ ትግሉን ወደ አንድነት በማምራት በየሰልፎቹ ኦሮሞ  አንድ ነን፣ አማራ አንድ ነን፣ ደቡቡ አንድ ነን፣  ሱማሌው አንድ ነን፣ ጋንቤላው አንድ ነን፣ ትግሬው አንድ ነን በማለት መነሳት ያስፈልጋል። የኦሮሞው ህመም የአማራው ህመም ነው  የአማራው ስቃይ የኦሮሞው ስቃይ ነው በማለት ትግሉን ከዳር እስከዳር በማቀጣጠል ለነጻነት የሚደረገውን ትግል በማፋጠን አንባ ገነኑን ወያኔ ለመጣል በፖለቲካ አመራር ላይ ያሉት ፖለቲከኞች እንዲሆም ሙሁራኖች እና የአገር ሽማግሌዎች ትልቁን ድርሻ በመውሰድ ዋናውን ሃላፊነት ልትወቱ ይገባል።
addis ababa 2
ፖለቲካ ማለት ሃይማኖት አይደለም ከትውልድ እስከ ሞት የምንከተለው። ፖለቲካ ማለት ከጊዜው ጋር እንደ ግዜው ሁኔታዎችን መለዋወጥ የሚችል፣ እንደ ሁኔታው ከሁኔታዎች ጋር አስማምተው የሚያስጉዙበት፣ ከእድገት ጋር አብሮ  የሚያድግ፣ ከዘመኑ ጋር አብሮ የሚዘምን፣ ከእንቅስቃሴ ጋር ስልቶችን አስማምቶ አብሮ  የሚንቀሳቀስ ነው። ለዚህ ደግሞ  ፖለቲካውን እንመራዋለን የሚሉት አካሎች ከግል የስልጣን ጥቅምና ክብር አገራዊ ክብርን በማስበለጥ ህዝቡ ነጻነቱን የሚያገኝበት እና ከአንባ ገነኖች የሚላቀቅበትን እቅዶች አጋጣሚዎችን በመጠቀም እንቅስቃሴውን ወደ ውጤት የሚመጣበትን ስራ ትሰሩ ዘንድ ግዜው እና ሰዓቱ ያስገድዳችኋል።
ወያኔ በኢትዮጵያ ላይ የሳለው ስዕል በተለይም  በሁለቱ ወንድማማቾች ማለትም በኦሮሞ እና በአማራ አንዱ የአንዱ ጠላት አንዱ የአንዱ አጥፊ ተደርጎ ተቀምጧል። በዚህ አጋጣሚ የወያኔን ድብቅ ስራ በመስበር ክፋፍሎን በተናጠል ተራ በተራ ህዝባችንን እየጨረሱ ሃብታችንን እየዘረፈ መሬታችንን እየነጠቁ በአገራችን ላይ የበዪ ተመልካች እያደረጉን ያለው ወያኔ ሆኖ ሳለ አንተ አማራ አንተ ኦሮሞ በሚለው መነቋቆር መተው አለብን ። የአገር እና የህዝብ ጠላትን አንግሰን ወንድማማቾች የሆነው በትንሽ ነገር ተፈራርተን ዳርና ዳር በመሆን እየተያየን ትላንትና አማራ መንደር ዛሬ ኦሮሞ ሰፈር ሃዘን ገባ ሃዘን ወጣ እያልን እንገኛለን። አንድነታችንን አሳጥቶን ሁለት ወንድማማቾች ተፈራርተን በመቆማችን ወያኔ ተራ በተራ እየገደለን እና ስቃያችን እያበዛብን ይገኛል።
ኦሮሞ  እና አማራ የጋራ ጀግንነት እያለን ኦሮሞ እና አማራ የጋራ አገር እያለን ኦሮሞ  እና አማራ አንድ ደም ኖሮን ሳለ ወያኔ በተባለ ከፋፋይ ተከፋፍለን አማራ እኮ ኦሮሞ እኮ እያልን በማይረባ ነገሮች ተጠላልፈን አገር ስትጠፋ ህዝባችን ሲያልቅ ቆመን እያየን ነው። ትላንትና ወይኔ ወይኔ እያለ ሲያለቅስ የነበረው አማራ ወንድማችን፥ ዛሬ ደግሞ ማሎ ማሎ እያለ ያለቅሳል ኦሮሞ ዘራችን።
ወገኔ በርሃብ አለንጋ እየተጠበሰ እያለ ወያኔዎች ሆዳቸው ስለጠገቡ ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ ድርቅ እንጂ እራብ የለም ድርቅማ ካሊፎርኒያ ገብቷል ድርቅማ አውስትራሊያ አለ እያሉ የሚቀሊዱ ስለ ህዝብ የማያስቡ ያሉበት ስብስብ ናቸው።
የኢትዮጵያን ገበሬ እያፈናቀላችሁ ደሃ አታድርጉ መሬቱን እየነጠቃችሁ ለማኝ አታድርጉት ሲባሉ ወያኔዎች በገበሬው መሬት ላይ የሪል ስቴት ባለቤቶች ስለሆኑ በገበሬው መሬት ላይ ባለ ብዙ ፎቅ ባለቤቶች ስለሆኑ ልማት ላይ ነን ከልማታችን አታደናቅፉን ብለው እየጨፈሩ ይገኛሉ።
ህዝብ በሰላማዊ ሰልፍ ድምጻቸውን ሲያሰሙ በጥይት ደብድበው ይገድሉ እና ከኦነግ ወይንም ከግንቦት 7 ጋር ግንኙነት ያላቸው አሸባሪዎች ናቸው የተገደሉት ብለው እያሾፈብን ይገኛል።
ወገኔ ወያኔን በተናጠል መቼም አናሸንፍም። ወደድንም ጠላንም እውነቱ ይሄ ነው ተነጣጥለን የሚደረግ ጉዞ እንጠፋፋልን እንጂ ድል የሚባል የለም። እውነቱ ይሄ ነው ወያኔ ኦሮሞን ሲያጠፋ ወደ አማራው ተለጥፎ ነው አማራውን ሲያጠፋ ወደ ኦሮሞ ተለጥፎ ነው። እኛም ፍቃድ ሰተነው ዝም ካልነው እየነጣጠለ ይገድለናል እየነጣጠለ ይዘርፈናል እየነጣጠለ ያሰቃየናል ምክንያቱም ይሄንን እንዲያደርግ ፍቃዱን የሰጠነው እኛው ስለሆንን። የለም በወያኔ ከፋፍለህ ግዛ ህዝባችን አይጠፋም በኢትዮጵያ ውስጥ ሞት እስራት ርሃብ ስደት እንዳይኖር የምናስብ ከሆነ እንቢ ዘረኝነት እንቢ መለያየት ማለት ከጀመርን የወያኔ መጨረሻው እና የኢትዮጵያ ህዝብ የድሉች ድል ያኔ ይጀምራል።
በኦሮሚያም ይሁን በአማራ ይሁን በደቡብ ይሁን በሐረር ይሁን በጋንቤላ በሚደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ እንዲ እየተባለ ሰልፍ ቢወጣ እንቅስቃሴው አገር አቀፋዊ በማድረግ የነጻነታችንን በር ከፍቶ እንደ መግባት ሊቆጠር ይቻላል። ትግሉንም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ይሆናል።
አንሰጥም ለዘራፊ አንሰጥም፣
አንሰጥም ለወያኔ አንሰጥም፣
አንሰጥም የሰበታን መሬት ፣
አንሰጥም የሱሉልታን መሬት፣
አንሰጥም የቡራዩ ን መሬት፣
አንሰጥም ለሱዳን አንሰጥም፣
አንሰጥም የጎንደርን መሬት፣
አንሰጥም የወለጋን መሬት፣
አንሰጥም የጋንቤላን መሬት፣
አንሰጥም የጎጃምን መሬት፣
አንሰጥም ለዘራፊው መንግስት፣
አንሰጥም የሲዳሞን መሬት፣
አንሰጥም የአዋሳን መሬት፣
አንሰጥም የኢትዮጵያን መሬት፣
አንሰጥም ለወያኔ መሬት፣
አንድ ነን እኛ አንድ ነን፣
አንድ ነን ሁላችን አንድ ነን፣
አንድነን በደም የተዛመድን፣
አንድ ላይ መቼም የማንለይ፣
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር።

10.12.2015

No comments:

Post a Comment

wanted officials