Please read in PDF
ስለተከሰሱ ሰዎች መብት የኢትዮጲያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሕገ መንግሥት “በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር ፥ መብት አላቸው፡፡” በማለት ይገልጣል፡፡ (ሕ/መን.አን.20(3)) ነገር ግን “ሕጻናትን የሚመለከቱ እርምጃዎች በሚወሰዱበት ጊዜ በመንግሥታዊ ፥ ወይም በግል የበጎ አድራጎት ተቋሞች ባለ ሥልጣኖች ወይም በሕግ አውጪ አካላት፥ የሕጻናት ደህንነት በቀደምትነት መታሰብ አለበት፡፡”
በቀደምትነት መታሰብ ያለበት ብቻ ሳይሆን ፦
“ማንኛውም ሕጻን ጉልበቱን ከሚበዘብዙ ልማዶች የመጠበቅ ፥ በትምህርቱ፥ በጤናውና በደህንነቱ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ሥራዎች እንዲሠራ ያለመገደድ ወይም ከመሥራት የመጠበቅ መብትም እንዳለው” በግልጥ አስቀምጧል፡፡
(ሕገ መን.አን.36(1)መ)
|
አንድ ተጠርጣሪ ከፍርድ “በፊት እንደንጹሕ ሰው የመታየት መብቱ” የተጠበቀ ቢሆንም፥ ይህ ግን የፍርድ ሂደትን በሙግት ከመከራከር ይልቅ አገር ለቆ ለመጥፋትና ከፍርድ ሂደት ለመሰወር ሊሆን ይገባዋል የሚል ግምትም ፤ እምነትም እኛም ሆን የአገሪቱ የወንጀል ፖሊሲ አይከተሉም፡፡ በተለይም የድርጊቱ አጸያፊነት ፤ የሃይማኖትንና የአገሪቱን ባህልና እሴት ፍጹም በሚጻረር መልኩ ሲከናወን ላየ ደግሞ ድርጊቱን ለማውገዝ ብዙ ማሰላሰልና ሊቅ መሆን አይገባም፡፡
ስለግብረ ሰዶም አስከፊነትና መነሾ ሀሳብን በመንግሥትና በማህበረሰቡ ትኩረት ሊሰጣቸው ከሚገቡ ሥፍራዎች በዋናነት የሕጻናት መዋያንና ትምህርት ቤቶችን በቅድሚያነት ማስቀመጣችን አይዘነጋም፡፡ እንደቀደመው ደግሜ እላለሁ ፦ ግብረ ሰዶም አጻያፊ ርኩሰት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ሕጻናትን ትኩረት በማድረግ የሚፈጸም በሚሆንበት ጊዜ፥ አስከፊነቱን ከወዲሁ በመረዳት “ሳይቃጠል በቅጠል” እንዲባል ፈጥኖ መረባረቡ የሁሉም አካላት ድርሻ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያን የሰማይ መንግሥት ሠራተኛ እንደመሆኗ፥ ለእግዚአብሔር ክብርና ቅድስና ብቻ ልትቆም ይገባታል ፤ ከእግዚአብሔር ባህርይና ፈቃድ ጋር የሚቃረነውን የኃጢአተኞችን ኃጢአት ፥ ነውር ለመቈጣትና ለመፍረድ ዳግመኛ ምጽዓቱን የሚጠብቅ አይደለም ፤ ጌታ እግዚአብሔር ንስሐ ከመግባት የሚዘገዩትን (ሉቃ.13፥3) ፤ በአሁኑ ዘመንም “እርስ በርሳቸው ሥጋቸውን ሊያዋርዱ ለልባቸው ፍትወት ወደ ርኵስነት አሳልፎ ይሰጣቸዋል፤” (ሮሜ.1፥24)፡፡ ኃጢአት በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ግድግዳ ሆኖ የእግዚአብሔር ፊቱን ከእኛ ይጋርዳል(ኢሳ.59፥2) ፤ በእርግጥም “የአንዳንዶች ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ ነው ፍርድንም ያመለክታል፥ ሌሎችን ግን ይከተላቸዋል፤” (1ጢሞ.5፥24)፡፡
በሞግዚትነትና በሃይማኖት ጥላ ሥር ባሉ ሕጻናት ላይ ያነጣጠረ ግብረ ሰዶማዊነት ከምንም በላይ አደገኛነቱ አያጠያይቅም ፤ ሕጻናትንና አማንያንን ቤተ ክርስቲያን በወንጌል ከወለደቻቸው (1ቆሮ.4፥15) ፤ የማንም ግብረ ገብነት የጎደላቸው አገልጋዮችና ሰዎች መጫወቻ ሲሆኑ ማየት ተገቢነት የጎደለው ብልሹ አካሄድ ነው፡፡ ሕጉ የሚያገለግለው ለድሆች ፣ ገንዘብ ለሌላቸው ፣ የሚያስመካ ባዕለ ሥልጣን ዘመድ ለሌላቸው ፣ ለተጠቁ ወገኖች ብቻ ሳይሆን በገንዘባቸው ለሚመኩና ለሚባልጉ “ባዕለጠጎች” ፣ አድሎአዊነትን ለሚያገኑ ባዕለ ሥልጣናት ፣ ለውጪም ዜጎችና ለእግዚአብሔር አገልጋዮችም እንዲውል መጽሐፍ ቅዱስም ፤ ሕገ መንግሥቱም ያዛሉ፡፡
እንኪያስ፦ ጣሊያናዊው ግብረ ሰዶም ፈጻሚ የደብር አገልጋይ ከአገር እንዲወጣ በዋስ የተለቀበበትና ሲወጣም ዝም የተባለበት ጉዳይ ብዙ ነገሮችን እንድናብሰለስል ያደርገናል፡፡ የፈለጉትን ወንጀል ፈጽሞ (ያውም ከበቂ በላይ ማስረጃ በምስልና በሰው የተረጋገጠ ማስረጃ እያለ) በስመ የውጪ አገር ዜጋ ፣ በስመ ባዕለ ጠጋ ፣ በስመ የባዕለ ሥልጣን ዘመድ … በሕጉ እንዲህ የሚፈነጨው እስከመቼ ነው? በእውኑ እንዲህ የትውልድን ህሊና ከሚያጨልምና የነገን ተስፋ ከሚያስደነግዝ የበለጠ ምን የሚበልጥ ነውርና ርኩሰት አለ?!
በእውኑ አገር ሊለቅ ሁሉን ነገር እንደጨረሰ እየታወቀ ፤ ዋስትናን ከመጠበቅ ይልቅ በህጻናቱ ላይ የተፈጸመው አካላዊና ሥነ ልቡናዊ የግብረ ሰዶም ጥቃት ሚዛን ሳይደፋ ቀርቶ ነውን ተከሳሹ በዋስ የተለቀቀው? … በዋስ ይለቀቅ ግድ የለም … እንዲህ ያለ ነውር ሰርቶ አገር ሲለቅና ሲወጣ ዝም ነው የሚባለው? የውጪ ዜጎችንና በገንዘባቸው ጉልበት የፍትህን ህሊና በሚጠመዝዙ ሰዎች ዙርያ ዳግም እጅግ መጤን ያለበት ብዙ ነገር እንዳለ ይሰማናል፡፡ የመጀመርያው ቀለምና ቆዳን ብቻ አይቶ ከእኛ ይሻላሉ የሚለው መርህ ዛሬም እንዳልቆመ እያስተዋልን ነው፡፡ ሐበሻዊውን ጥቁር አርክሶ ፣ ፈረንጅን አጽድቆ ያየው አይናችን ውጤቱን ሳይርቅ እያሳየን ነው፡፡ ንጹህ ጥቁርም ፤ ንጹህ ነጭም ያለውን ያህል ለትውልድ የማይጨነቅና የማያስብ ነጭም ጥቁርም እንዳለ እናምናለን፡፡ ስለዚህም እይታችን መስተካከል አለበት፡፡
ሁለተኛው፦ የላላው ሕግ መጥበቅ እንዳለበት እናምናለን፡፡ በሕጉ አስፈጻሚና በሕጉ ተርጓሚዎች ዘንድ ያለው ልኩን ያለፈ ተላላነትና ዝንጉነት ፈጽሞ መስተካከል አለበት፡፡ ትውልድ እየተመረዘ ፣ ሕጻናት በርኩሰት እየተከበቡ ፣ ባዕለ ገንዘቦች ፍትህን እያጣመሙ … ነገን ተስፋ ማድረግ ተኩላን አስሮ የበግ ግልገል የመጠበቅ ያህል እጅግ ከባድ ነው፡፡ ፍርድ ሲላላ ጻድቅ ተወቅሶ ኀጥኡ ይጸድቃልና ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ሦስተኛው የኃይማኖት ተቋማት አንዳቸው በሌላው ላይ ማላከክን ትተው ራሳቸውን ቢፈትሹና ንስሐ ቢገቡ የምድሪቱን ፈውስ ያስቸኩላሉ፡፡ በተለይ የዚህን ኃላፊነት የተሸከመው የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር በአብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ ላይ የግብረ ሰዶማዊነትን አስከፊ ገጽታ ከማውሳቱም ባሻገር ተጨባይ ለውጥ እስኪመጣ የአብያተ ክርስቲያናት መሪዎችን ተግቶ በቃለ እግዚአብሔር ማነጽና በጸሎት የማትጋት ሥራ መሥራት እንዳለበት እናስባለን፡፡ በተያያዥነትም አብያተ ክርስቲያናትና የመንግሥት መሪዎች እንዲህ ያለውን ነውር በመረባረብ እንዲሠሩ ምክራችንም ፤ የዘወትር ጭንቀታችንም ነው፡፡
ጌታ እግዚአብሔር ለምድራችን የንስሐ ልብ ያብዛ፡፡ አሜን፡፡
Source http://abenezerteklu.blogspot.com/2015/11/blog-post.html
No comments:
Post a Comment