Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, August 10, 2016

ባለፉት ሶስት ቀናት በኦሮምያና በአማራ ክልሎች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 200 እያሻቀበ ነው


 ኢሳት ዜና :- አጋዚ የሚባሉት የገዢው ፓርቲ ታማኝ ወታደሮች በኦሮምያና በአማራ ክልሎች በንጹሃን ዜጎች ላይ በፈጸሙት ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ የተገደሉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ከተለያዩ አካባቢዎች የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኦሮምያ ክልል ብቻ ከ130 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በአማራ ክልል ደግሞ ከ70 ያላነሱ ሰዎች ተገድለዋል።
ከፍተኛ ግድያ ከተፈጸመባቸው ቦታዎች መካከል ባህርዳር ቀዳሚ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ ጫካ ውስጥ የተጣሉ አስከሬኖች እየተገኙ ነው።
በባህርዳር ታሪክ የመጀመሪያ በተባለው ሰልፍ ከ100 ሺ በላይ የሚሆነው የከተማው ህዝብ በነቂስ ወጥቶ አገዛዙን በቃኝ ብሎአል። በባህርዳር ዛሬም ድረስ ማንኛውም እንቅስቃሴ ቆሟል።
ከጠዋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ከተለያዩ አቅጣጫ የተሰባሰበው የባህርዳርና አካባቢው ህብረተሰብ በነቂስ ወጥቶ ወደ መስቀል አደባባይ ተመመ፡፡
የህውሃት አምባገነንነት ይብቃ!
‹‹አማራነት ይከበር!››
‹‹ወልቃይት አማራ ነው!
በጥቂት አምባገነኖች ኢትዮጵያ አትፈርስም!
የኦሮሞ ወንድሞቻችን ግድያ ይቁም!
አንዳርጋቸው ጽጌ መሪያችን ናቸው!
የእስልምና ኮሚቴዎች ይፈቱ!
ወልቃይት ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ! እና የመሳሰሉትን መፈክሮች የያዙ ባነሮች ከፍ በማድረግ ልዩ ልዩ መፈክሮችን በማሰማት የደመቀ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያካሄድ አርፍዷል፡፡
በሰልፉ ላይ የሚታየው የህዝቡ አንድነትና መከባበር አስደናቂ ነበር፡፡አንዳንድ ተሰላፊዎች የማይሆን ንግግር ሲናገሩና ዲንጋይ ሲያነሱ ‹‹ተው!›› የሚሏቸውን ታላላቆች በመስማት ሰላማዊ በሆነ መልኩ ተቃውሞሟቸውን ሲያሰሙ ታይተዋል፡፡
ከአሁን በፊት ታይቶና ተሰምቶ ባማያውቅ ሁኔታ 100 ሺ የሚሆነው የባህርዳር ከተማ ሰላማዊ ሰልፈኛ የከተማዋን ዋና ዋና ጎዳናዎች በመሙላት ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞውን በህውሃት ኢህአዴግ አመራር ላይ አሳይቷል፡፡እስከ ጠዋቱ አራት ሰዓት ጥያቄያቸውን በመፈክር ሲያሰሙ አርፍደዋል፡፡
ወደ አባይ ማዶ በተደረገው ጉዞ በየመንገዱ መፈክሮችን በማሰማት እና ‹‹ይለያል ዘንድሮ የወያኔ ኑሮ!›› በማለት እየጨፈሩ የሚጓዙት ሰልፈኞች በድብ አንበሳ ሆቴል ፊት ለፊት የሚገኙትን የአፄ ቴዎድሮስ እና የደጃዝማች በላይ ዘለቀ ሃውልቶች ላይ ነባሩን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ በማልበስ ጭፈራቸውን ቀጠሉ፡፡
ጎንደር ለማን ሞተ- ለአማራ ብሎ
ጎንደር ለማን ሞተ- ለኦሮሞው ብሎ
ጎንደር ለማን ሞተ- ለጋምቤላው ብሎ
ጎንደር ለማን ሞተ-ለደቡቡ ብሎ
ጎንደር ለማን ሞተ- ለሶማሌው ብሎ . . .
ጎንደር ለማን ሞተ- ለኢትዮጵያ ብሎ በማለት ጭፈራ እያሳዩ በመንገድ ላይ በሚገኙ መስሪያ ቤቶች የሚገኙ ባንዲራዎችን በአረንጓዴ ቢጫ ና ቀዩ ባንዲራ በመተካት ጉዞ ወደ አባይ ማዶ ሆነ፡፡
አባይ ማዶ ‘ኮበል የኢንዱስትሪ መንደር’ በመባል በሚታወቀው የቀድሞ የኢህአዴግ የጦር ጉዳተኛ ታጋዮች የተመሰረተው የንግድ ተቋም ላይ ሰልፈኛው ሲደርስ በዋናው መንገድ በስርዓት ሲጓዙ የነበሩትን ሰልፈኞች የኮበል ኢንዱስትሪ ዘበኛ እና አስቀድሞ ቦታ ቦታ በመያዝ ያደፈጠው የአጋዚ ጦር ከየአቅጣጫው ብቅ በማለት አስለቃሽ ጢስ በመተኮስ በመበታተን በአልሞ ተኳሸች ጥይት  መልቀም ጀመሩ፡፡በጥይት ተመቶ የሚወድቀውን ሰልፈኛ ለማንሳት የሚጠጉትን ሰልፈኞች ላይም በመተኮስ ባዶ እጁን የወጣውን ሰላማዊ ሰው ደም አፈሰሱ፡፡ህጻናትም የሰለባው አካሎች ሆኑ፡፡
የአጋዚ ወታደሮች በኮበል አካባቢ በሚገኘው የጋራ መኖሪያ ቤት ውስጥ በመግባት በነዋሪው መስኮት ብቅ በማለት በቀጥታ በሰልፈኛው ላይ ተኩሰዋል፡፡
ሰልፈኛው ጥይቱን ሳይፈራ ሰልፉን ወደፊት በመቀጠልና ዲንጋይ በመወርወር ራሱን ቢከላከልም በመንገዱ ግራና ቀኝ የመሸገው የአጋዚ ጦር ህዝቡን ያለርህራሔ ጨፈጨፈ ፡፡
የተጎዱት ሰላማዊ ሰልፈኞች በአካባቢው ባለው የአባይ ማዶ  ፣በጋምቢና በፈለገ ህይወት ሆስፒታል ህክምና የተደረገላቸው ሲሆን ፤የቀይ መስቀል አምቡላንሶች ሁሉንም ተጎጂ በየህክምና ተቋማቱ ለማድረስ ከፍተኛ ስራ በዝቶባቸው ሲሯሯጡ ታይተዋል፡፡
በዚህ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ በኮበል አካባቢ የነበረ አንድ የጭነት መኪና ተቃጥሏል፡፡
በከፍተኛ ቁጣ ውስጥ የገባው የባህርዳር ህዝብ በቀበሌ ስድስት  አካባቢ ህዝቡን ሲደበድቡና ሲያሸብሩ በነበሩ የስርኣቱ  ታማኝ ወታደሮች ላይ ጥቃት ፈጽሞ አንድ ወታደር ገድሎ ሌሎቹን አቁስሏል፡፡በቀበሌ አስራ አራት ውሃ ስራዎች መስሪያ ቤት አካባቢም እንዲሁ ከወታደሮች ጋር በተነሳው ግጭት አንድ ወታደር በጩቤ ተወግቷል፡፡
በባህርዳር ማረሚያ ቤት ውስጥ የነበሩ የህግ ታራሚዎችም የስርዓቱን አገዛዝ በመቃዎም ጩኸት ሲያሰሙ አርፍደዋል፡፡በነበረው የቶክስ ልውውጥም የተገደሉና የቆሰሉ የህግ እስረኞች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ሰኞ ነሐሴ 2
ሁሉም መስሪያ ቤቶች ዝግ ነበሩ፡፡ በከተማዋ ምንም አይነት የትራንስፖርት አገልግሎት አልነበረም፡፡ባንክ ቤቶች ምግብ ቤቶችና ሶቆች በሙሉ ተዘግተው ውለዋል፡፡
በቀበሌ 16 እና ቀበሌ 7 በወያኔ አልሞ ተኳሸች የተገደሉትን ወጣቶች ለመቅበር የተሰባሰበውን ህዝብም ለመበተን ከፍተኛ ርብርብ ሲያደርጉ የነበረ ቢሆንም ቀብር ላይ የተሰባሰበው የከተማው ህዝብ ግን ‹‹ይለያል ዘንድሮ የወያኔ ኑሮ›› በማለት ተቃውሞውን በማሰማት ወንድሞቹን ቀብሮ ተመልሷል፡፡
ከቀብር መልስም ተሰባስቦ የሚመጣውን ወጣት እየተከታተሉ በመደብደብ ችግር ሲፈጥሩ የነበሩ የስርዓቱ ታማኝ ወታደሮች ታይተዋል፡፡
በዚሁ እለት የሚካሄዱ የቀብር ስነስርዓቶች ላይ ችግር ይፈጠራል ብሎ ያሰበው የህወሃት/ኢህአዴግ መንግስት የክልሉን ፌደራል ፖሊስ ና በመኮድ ውስጥ የሚገኘውን የክልሉን አድማ በታኝ ሃይል ለማሰማራት ቢሞክርም በወገናቸው ሞት ሃዘን የተሰማቸው አባላቱ ባሳዩት እምቢተኝነት ከመቀሌ በአንቶኖቭ አውሮፕላን ወታደሮችን ጭኖ በማምጣት ህዝቡን ሲያውክ ውሏል፡፡
ህዝቡ በከተማዋ መሃል በሚገኘው የአውቶቡስ መነኸሪያ አካባቢ የመኪና ጎማ በማቃጠልና በፓፒረስ ሆቴል አካባቢ ድምጹን በጩኸት በማሰማት ተቃውሞውን ቀጥሎ ውሏል፡፡
በቀበሌ 17 ዕውቀት ፋና ትምህርት ቤት አካባቢም በነበረው ተቃውሞ ወታደሮች በተኮሱት ጥይት አንድ የአከባቢው ወጣት እጁ ላይ በጥይት ተመቶ ቆስሏል፡፡
የአባይ ማዶ ወጣቶችና የአካባቢው ነዋሪዎቸ በመሰባሰብ መንገዱን በኮንክሪት ግንድ በመዝጋት ተቃውሟቸውን ሲገልጹ የዋሉ ሲሆን አጋዚዎችም  የሚያገኙትን ወጣት በማፈስ ወደ መኮድ የጦር ካምፕ በመውሰድ  ሲያስሩ ውለዋል፡፡
ማክሰኞ ነሐሴ 3
ዛሬም አብዛኛው የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ባንኮች፣ሆቴሎችና ሱቆች ዝግ ናቸው፡፡
በህውሃት አልሞ ተኳሸች ተገድሎ በትላንትናው እለት የቀብር ስነስርዓቱ የተካሄደው የጢስ አባይ ተወላጅ ሰላማዊ ሰልፈኛ ቤተዘመዶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ሌሊቱን ከህውሃት ጦር ጋር ጠበንጃ አንስተው ሲዋጉ ማደራቸው ከጢስ አባይ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡በጢስ አባይ ከተማ ያለው ውጥረት እየተባባሰ በመሄዱ ዛሬ ረፋዱ ላይ  ከአንድ መቶ ሃያ በላይ ተጨማሪ የህውሃት ሰራዊት  ከተለያዩ የሃገሪቷ ክፍሎች በአንቶኖቭ በመምጣት ወደ ጪስ አባይ ለውጊያ ተልኳል፡፡ የአካባቢው ታጣቂም ፍልሚያውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በአጠቃላይ
ህዝቡን በግድ ወደ አመጽ አስገብተውታል በሚባለው የደብረታቦሩ ሰላማዊ ሰልፍ በእለቱ አራት ሰዎች ሲሞቱ በትላንትናው ዕለት ከፈለገ ህይወት ሆስፒታል በወጡ መረጃዎች ሁለት የቆሰሉ ሰልፈኞችም ህይወታቸው አልፎ አስክሬናቸው ወደ ሃገራቸው ተልኳል፡፡
በወረታ ሁለት ሰዎች የወያኔ ጥይት ራት ሲሆኑ በይፋግና አዲስ ዘመን ደግሞ አራት ሰዎች መሞታቸው ታውቋል፡፡
መረጃ
በደብረ ማርቆስ፣ብቸና፣ፍኖተሰላም፣ቡሬ፣ኮሶበርና ሞጣ በተከታታይ ሊነሳ ይችላል ተብሎ የተሰጋውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ለማዳፈን ሁሉም የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በመሰማራት ፓርቲውን አባላት በመሰብሰብ  ስብሰባዎችን ማክሸፍ ሚቻልበትን መንገድ እንዲያመቻቹ የተሰጣቸውን ተልዕኮ ይዘው በመስራት ላይ ናቸው፡፡ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሰልፍ ዳግም በየትኛውም ከተማ እንዳይደረግ ለማፈን በዚህ ስራ ተወጥረዋል፡፡
  

No comments:

Post a Comment

wanted officials