Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, August 19, 2016

የህዝብን የነፃነት ጥያቄ በጠመንጃ ማፈን አይቻልም!

ለዘመናት በአንድነቱና በነፃነቱ ጸንቶ የኖረው የኢትዮጵያ ህዝብ ከአብራኩ በወጡ ሃገር በቀል ወራሪዎች ላለፉት ሃያ አምስት አመታት በመሪር አገዛዛቸው ሲቀጠቀጥና ሲታሰር፣ሲገደልና ሲሰደድ የአንድ ትውልድ ዕድሜ ነጉዷል። የኢትዮጵያ ህዝብ ከእሳት ወደረመጡ እንዲሉ ዛሬ በዓለም መድረክ ሰቆቃ ከሚፈጸምባቸው ህዝቦች ቀዳሚው ነው ብንል አልተጋነነም።ትናንት በአባቶቻችን ዕድሜ ነጻነታቸውን ያገኙ የአፍሪካ ሃገራት ህዝቦች ነጻነትና ዲሞክራሲን ሲያጣጥሙ እኛ በባርነትና በጭቆና እየማቀቅን ለመሆኑ ዋቢ መጥራት አያስፈልገንም። ሃገራችን የጥቂት አምባገነኖች ንብረት ሆና ህዝባችን በረሃብና በበሽታ እንዲማቅቅ ተፈርዶበት፣ልጆቹ እንጀራ ፍለጋ በየሃገሩ ተሰደው ለአውሬና ለባህር ብሎም ለነፍሰ በላ አሸባሪዎች ህይወቱን የገበረው በዚህ ዘረኛ አገዛዝ ዘመን ነው። በየእስርቤቱ የሚማቅቁት ወገኖቻችን ሁሉ ለነጻነትና ለፍትህ በመሟገታቸው በፈጠራ ወንጀል ተከሰው በአድር ባይ ዳኞች ፍርደ ገምድል ውሳኔ በየማጎርያ ቤቱ የስቃይ ኑሮ የሚገፉት ለህዝባችን መብትና ነጻነት መረጋገጥ መሆኑን እንገነዘባለን። እኛም ከእናት ሃገራችን በግፍ ተሰደን በዩጋንዳ የምንኖር ስደተኞች በደረሰብን ወከባ ፣ስቃይና እንግልት ለስደት ተዳርገን የመከራ ህይወት የምንገፋው ሃገር አልቦች ሆነን ሳይሆን በዕኩልነትና በፍትሃዊነት የሚያስተዳድረን የመረጥነው መንግስት ባለመኖሩ ነው። ዛሬ ላይ በሃገራችን የተቀጣጠለው የህዝብ ብሶት የዘመናት የፍትና የርትዕ ዕጦት መሆኑንም እንረዳለን። ህዝቡ በወረቀት ላይ በሰፈረው ህገመንግስታዊ መብት ጥያቄዎቹን በማቅረቡ ገዢው ሃይል የሰጠው ምላሽ ጅምላ ግድያና እስር መሆኑ በዚህ ሃያ አንደኛው ክፍለዘመን በጉልበት ህዝብን አንበርክኬ እገዛለሁ ማለት ትላንት በሰሜን አፍሪካ ተቀጣጥሎ የነበረው ህዝባዊ ማዕበል የቱንዚያን ንጉሳዊ አገዛዝ እንዳስወገደ፣የግብጹን ሆስኒ ሙባረክና የሊቢያውን ሙአመር ጋዳፊ ከተጣበቁበት ወንበር አሽቀንጥሮ ለውርደትና ሞት እንዳበቃ የወያኔ መንግስት እንዴት መገንዘብ እንዳቃተው ለሁላችንም እንቆቅልሽ ነው። የገዛ ህዝብን በሰራዊት ብዛት አስጨንቆና አሸማቆ ለዘመናት መግዛት አይቻልም።የህዝብን ጥያቄ በአግባቡ አስተናግዶ ምላሽ መስጠት እንጂ በመሳርያ ተማምኖ ህዝብን መፍጀት መንግስት ከሆነ አካል የሚጠበቅ ተግባር ሳይሆን የአሸባሪዎች ድርጊት ነው። በመላ ኦሮሚያ ከመንፈቅ በላይ በዘለቀው ህዝባዊ ተቃውሞ ወጣት ተማሪዎችን በጥይት በመደብደብ ህዝባዊውን ንቅናቄ አዳፍናለሁ የሚለው የወያኔ የጉልበት ርምጃ ችግሮችን ከማባባስ በስተቀር የፈየደው ነገር የለም።ዛሬ ደግሞ መላው አማራ በደረሰበት ግፍና በደል ተማሮ አደባባይ በመውጣቱ ወገኖቻችን በግፍ እየተጨፈጨፉ መሆኑን በዓለም መገናኛ ብዙኃን እየተከታተልን ነው። በማንኛውም ወገናችን ላይ የሚፈጸመውን ግድያ ፣እስርና ማሳደድ አጥብቀን እናወግዛለን።በሰላማዊው ህዝባችን ላይ በማን አለብኝነት ፍጅት እንዲካሄድ የሚያደርጉትን ወገኖች ከአፈራሽ ተግባራቸው ተቆጥበው የህዝቡን የነጻነት ጥያቄ በሃይል በመጨፍለቅ የስልጣን ዕድሜን ማራዘም እንደማይቻልና ውድቀትንም እንደሚያፋጥን ከታሪክ እንዲማሩ እናሳስባለን። በመላ አለም ላይ ያሉ ለሰዎች ልጆች ሰብዓዊ መብት የሚቆረቆሩና የሚሟገቱ መንግስታት፣ሃገራትና ተቋማት እንዲሁም የዓለም መገናኛ ብዙሃን በህዝባችን ላይ የሚፈጸመው ግፍና ሰቆቃ እንዲቆም ከህዝባችን ጎን እንዲቆሙ ጥሪያችንን እያቀረብን በአምባገነኖች ትዕዛዝ ክቡር ህይወታቸውን ለተነጠቁ ወገኖቻችን የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን ስንገልጽ ለዲሞክራሲና ነጻነት መረጋገጥ የህይወት ዋጋ የከፈሉ ሁሉ ጀግኖች ሰማዕታት በመሆናቸው በታሪክ መዝገብ ስራቸውና ስማቸው ህያው ሆኖ እንደሚኖር ጽኑ እምነታችንን ለመግለጽ እንወዳለን። በሰው ሃገር በስደት የምንኖር ወገኖች የመንከራተት ዘመናችን አብቅቶ ከህዝባችን ጋር ዳግም ተገናኝተን በነጻነት ፣በፍቅርና በአንድነት እናት ኢትዮጵያን ወደነበረችበት የክብር ሥፍራ ለመመለስ እንድንችል የአምላክ ፈቃዱ እንዲሆን ከልባችን እንመኛለን።

በዩጋንዳ የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ማህበር ነሐሴ 9 ቀን 2008 ዓ/ም (ኦገስት 15, 2016)

No comments:

Post a Comment

wanted officials