ኅብረተሰቡን ለአመፅ የሚገፋፉና ግጭት ሊፈጥሩ የሚችሉ መጻሕፍት በማዘዋወርና በመሸጥ የተጠረጠሩ መጽሐፍት አዟሪዎች፣ ከነሐሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ መታሰራቸው ታወቀ፡፡
ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ መጻሕፍት አዟሪዎች በተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች መታሰራቸውንና በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ተረኛ ችሎት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸው ቤተሰቦቻቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
አዟሪዎቹ የተጠረጠሩት ሕዝብ የሚያነሳሱና አመፅ የሚቀሰቅሱ መጣጥፎችን በፍትሕ ጋዜጣ ላይ በማተም ክስ ተመሥርቶበት የሦስት ዓመታት ጽኑ እስራት የተፈረደበት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ በቅርቡ ‹‹የፈራ ይመለስ›› በሚል ርዕስ ያሳተመውን መጽሐፍ፣ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ‹‹የኦሮሞና አማራ የዘር ግንድ›› በሚል ርዕስ ያሳተሙት መጽሐፍና ጋዜጠኛ ሙሉ ቀን ተስፋው ‹‹የዘመኑ ጥፋት›› በሚል ርዕስ ያሳተመውን መጽሐፍ በማዞር ሲሸጡ ስለተገኙ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ቀደም ብሎ ክስ ተመሥርቶበትና ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ቅጣት የተጣለበትን መጣጥፍና በድጋሚ በመጽሐፍ መልክ ያሳተመውን መጽሐፍ ማሠራጨት ወንጀል መሆኑን ፖሊስ ለፍርድ ቤት ማስረዳቱ ታውቋል፡፡ ሌሎቹም የተጠቀሱት መጻሕፍት አመፅ ቀስቃሽ መሆናቸውን በመግለጽ መሠራጨታቸው ተገቢ አለመሆኑን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስረድቶ፣ መጻሕፍቱ ሲታተሙ ያተማቸው ማተሚያ ቤት በመጽሐፉ ላይ መግለጽ የነበረባቸው ቢሆንም ሳይገልጹ መቅረታቸውንም አክሏል፡፡ ይኼም ሆን ተብሎ መንግሥት ቁጥጥር እንዳያደርግ በድብቅ የሚሠራ ሕገወጥ ተግባር መሆኑን በማስረዳት፣ ለተጨማሪ ምርመራ ተጨማሪ ጊዜ መጠየቁ ተገልጿል፡፡
የተወሰኑ አዟሪዎች መጻሕፍቶች ተነጥቀው ሁለተኛ እንዳያዞሩ ፈርመው መለቀቃቸውንና ማተሚያ ቤቱን እንዲጠቁሙ ተገደው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ሐሙስ ነሐሴ 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ጊዜ ቀጠሮ የተጠየቀባቸው መጻሕፍት አዟሪዎች ሰኞ ነሐሴ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በድጋሚ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ታውቋል፡
No comments:
Post a Comment