Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, August 20, 2016

ኢትዮጵያ የእርሻ ምርቷ ክፉኛ ጉዳት እንደሚደርስባት ተመድ አስታወቀ

ኢትዮጵያ የእርሻ ምርቷ ክፉኛ ጉዳት እንደሚደርስባት ተመድ አስታወቀ
ኢሳት (ነሃሴ 10 ፥ 2008)
በተያዘው አመት የዝናብ እጥረት ምክንያት ለድርቅ አደጋ የተጋለጠችው ኢትዮጵያ፣ ዳግም በሚከሰት የቅዝቃዜ የአየር ንብረት ለውጥ የእርሻ ምርቷ ክፉኛ ጉዳት እንደሚደርስባት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳሰበ።
ሃገሪቱን ከጥቅምት ወር ጀምሮ ይመታታል ተብሎ የሚጠበቀው ይኸው ቀዝቃዛ የአየር ንብረት ለውጥ የእርሻ ምርት እንዲቀንስ በማድረግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለምግብ ድጋፍ ይዳርጋል ሲል ድርጅቱ ማክሰኞ ባወጣው ማሳሰቢያ አመልክቷል።
ጉዳዩ እጅግ አሳሳቢ ነው ሲሉ የገለጹት በኢትዮጵያ የአለም ምግብ ፕሮግራም ተወካይ የሆኑት አማዱ አላሁሪ በጥቅምት ወር ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው ቀዝቃዛ የአየር ለውጥ በኢትዮጵያ ተጨማሪ ጉዳትን ያስከትላል ተብሎ ስጋት መኖሩን እንዳሳሰቡ የአፍሪካን ኒውስ ኤጀንሲ ዘግቧል።
በተያዘው አመት በስድስት ክልሎች ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ ከ10 ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ መጋለጣቸው ይታወሳል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ድርቁ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ ርብርብ በማድረግ ላይ ሲሆን፣ ዳግም በቅዝቃዜ ሳቢያ ይደረጋል የተባለው የሰብል ምርት ችግሩን የከፋ ያደርገዋል ተብሎ ተሰግቷል።
በድርቁ ምክንያት የዘር እህሎቻቸውን ላጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች የተለያዩ የእርሻ ግብዓቶችን ለማቅረብ በቀጣዮቹ አራት ወራቶች ብቻ ከ90 ሚሊዮን ዶላር ብቻ እንደሚያስፈልግ የአለም ምግብ ፕሮግራም ገልጿል።
በሃገሪቱ ተከስቶ ያለው የድርቅ ጉዳት ለመቅረፍ ኢትዮጵያ አስቸኳይ የሆነ አለም አቀፍ ድጋፍን ትፈልጋልች ሲሉ በኢትዮጵያ የድርጅቱ ተወካይ የሆኑት አማዱ አላሁሪ አክለው አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ አስር ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ እጥረት ተጋልጠው የሚገኙ ሲሆን፣ ከተረጂዎቹ መካከል ወደ ስድስት ሚሊዮን የሚሆኑት ህጻናት መሆናቸው ታውቋል።
ለምግብ እጥረቱ ተጋልጠው ከሚገኙት ስድስት ሚሊዮን ህጻናት መካከል ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት በከፋ የምግብ እጥረት የተነሳ የአካልና የጤና ችግር እየደረሰባቸው እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ የመለክታል።
የአለም አቀፍ ተቋማት ድርቁ ወደ ከፋ ደረጃ ይሸጋገራል የሚል ተደጋጋሚ ስጋትን ቢገልጹም መንግስት ችግሩን ለመቆጣጠር ርብርብ እየተደረገ ነው ሲሉ ምላሽን ሰጥቷል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials