Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Monday, August 8, 2016

ከመላው አገር ወዳድ ክርስቲያኖች፤ ለተጋሩ (ትግሬ) የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖች በሙሉ የቀረበ ወቅታዊ ጥሪ


Tigrai ETOC
ከመላው አገር ወዳድ ክርስቲያኖች ለተጋሩ (ትግሬ) የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያኖች በሙሉ የቀረበ  የወገንህን፣ አገርህን እና ሃይማኖትህን አድን ወቅታዊ ጥሪ
 “አፍህን ስለ ዲዳው ክፈት፤ ተስፋ ስለሌላቸውም ሁሉ ተፋረድ … ለድሀና ለምስኪን ፍረድ።” (ምሳሌ 31፡8-9)
መነሻ
ትግራይ የኢትዮጵያ አገራችን የክርስትና/እስልምና እምነቶች እና የሥነ መንግሥት አስኳል ሆኖ ለዘመናት የዘለቀ ክልል ነው። የአገራችን ኪነ እምነትም ሆነ ኪነ ሕንጻ፣ ኪነ ዜማም ሆነ ኪነ መንግሥት ማማ ትግራይ ነው። ትግራይን ከኢትዮጵያ ነጥሎ ማሰብ እንደማይቻለው ሁሉ ኢትዮጵያን ከትግራይ ነጥሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው። ይሁን እንጂ ይህ የእምነትና የአገር ማማና ምሦሦ የሆነ ሕዝብና ክልል በዘመናችን ታሪካዊ ጥያቄ ቀርቦለት ይገኛል።
ታሪካዊ ጥያቄው አገራችን ኢትዮጵያ በማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ እንደምትገኝ እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥም የሰላምና መረጋጋት እጦት በማየሉ የአገሪቱ ሕዝብ የዕለት ተዕለት ኑሮ እጅግ አስቸጋሪ ደረጃ ላይ ከመድረሱ ጋር የተያያዘ ነው። ይህ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ ዜጎች በጅምላ የሚገደሉበትን እና በጅምላ ወደማሰቃያ እስር ቤቶች የሚጋዙበትን መከራ የተመለከተ ነው። ከታላቁ የትግራይ ክልል የበቀለው እና ላለፉት 25 ዓመታት መንበረ ሥልጣኑን የተቆጣጠረው የሕወሐት ቡድን የሚመራው ፓርቲ እና መንግሥት ለዚህ ቀውስ ዋነኛው ምክንያት መሆኑ ለታሪካዊው ትግራይ ፈተና ሆኖ ቀርቧል።
ይህ ፓርቲና መንግሥት ላለፉት 25 ዓመታት የዘረጋው የአፈና እና የሰቆቃ ሰንሰለት ከሕዝቡ አቅም በላይ በመሆኑ በተለያዩ አካባቢዎች አመጽ በመቀስቀስ ላይ ከመሆኑም ባሻገር አመፁ የአገሪቱን ሕልውና የሚፈታተን ሊሆን እንደሚችል የብዙ ባለሙያዎች እና ተመልካቾች ግምት ነው። ስለዚህም አገራችን ልትወጣው የማትችለው ቀውስ ውስጥ ከመግባቷ በፊት ሕወሐት በስሙ ለሚነግድበት የትግራይ ሕዝብ ጥሪ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
ሐተታ
በርግጥ የተዋሕዶ እምነት ተከታዩን ብቻ ለይቶ ጥሪ ማድረግ ለምን አስፈለገ ሊባል ይችላል። አብዛኛው ሕዝብ ለሚከተለው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታይ ጥሪውን በቀጥታ ማቅረብ ያስፈለገበትን ምክንያት በጥቂቱ እንደሚከተለው መግለጽ ይቻላል።
1ኛ. ጉዳዩ ክርስቲያኑን ብቻ የሚመለከት ስለሆነ ወይም ሌላ እምነት የሚከተለው ኢትዮጵያዊ ጉዳዩ ስለማይመለከተው ሳይሆን ጥሪውን ለማስተላለፍ የተሰባሰቡት ወገኖች የተሰበሰቡበት ዐውድ ሃይማኖት በተለይም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት በመሆኑ ጥሪውን ለእምነት አጋሮቻቸው ማቅረቡ ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ፣
2ኛ. በ1999 ዓ.ም የተደረገው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት እንደሚያመለከትው ከጠቅላላው የትግራይ ሕዝብ መካከል 95.6 በመቶው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ በመሆኑ እና የዚህ ምእመን ውሳኔ በሕወሐት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ እጅግ ከፍ ያለ በመሆኑ እና የተዋሕዶ እምነት ተከታዩ የትግራይ ሕዝብ ታቦተ ጽዮንን ጨምሮ በታሪክ የተሸከመው እምነቱንና አገሩን የመጠበቅ ታሪካዊ አደራ እንዳለበት ለማስታወስ፣
3ኛ. አገራችን አሁን ከገባችበ ቀውስ አንጻር ክርስቲያኑ የትግራይ ሕዝብ ሃይማኖቱ የሚያዘውን ሃይማኖታዊ ግዴታ በፍፁም መንፈሳዊነት ቢፈጽም አገሩን፣ ሃይማኖቱን እና ራሱን ከታላቅ አደጋ ሊያድን እንደሚችል ፍፁም እምነት በመኖሩ፣
4ኛ. በዘር ላይ በተመሠረተው እና ለመግባባት እና ለመወያየት ዕድል ሊከፍት ባልቻለው የዘር ፖለቲካ ግራ የተጋባው ሕዝባችን ተስፋ ወደ መቁረጥ በመድረሱ እና በቀቢጸ ተስፋ ሊወስድ የሚችለው ርምጃ ነገ ልንቀለብሰው የማንችለው አዘቅት ውስጥ እንዳይጥለን በማስጋቱ ለትግራይ ክርስቲያን ወገናችን ቀጥታ የአገርህን እና ሃይማኖትህን አድን ጥሪ ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው።
የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ምን ይላል? 
ለትግራይ የተዋሕዶ ወገናችን ጥሪ ስናስተላልፍ ቅድስት ክርስቲያናችን ከቅዱሳት መጻሕፍት ባገኘችውና ዘወትር በምታስተምረው ትምህርት ላይ ተመርኩዘን ነው። ከብዙው በጥቂቱ የሚከተሉትን መሠረታዊ ነጥቦች እንመልከት።
1ኛ. እግዚአብሔር ሁላችንንም በአርአያውና በአምሳሉ ፈጥሮናል። ሁላችንም የእጁ ሥራዎች ነን። ለአያሌ ዘመን በአንድ አምላክ እምነት የኖርን ሕዝቦች ነን። በኋለኛውም ዘመን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን በደሙ ተዋጅተን ልጅነትን ያገኘነው የአንድም የሐዋርያ ደም ሳናፈስ እንደሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፀሐፊዎች በሙሉ ይመሰክራሉ።መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የመንግሥቱ ወራሾች እንድንሆን በሞቱ የሞትን ማሠሪያ ሲፈታልን እርሱ አባታችን ሁላችንም ደግሞ ወንድም እና እህት ሆነናል። አባታችን እግዚአብሔር እናታችን ቤተ ክርስቲያን ብለን ለክብር በጠራን አምላክ ፈቃድ የአንድ አምላክ ልጆች ተብለናል።
2ኛ. ክርስትና ለተለየ ዘር፣ ለተለየ ጎሳ እና ነገድ የተሰጠ ሳይሆን ሁሉም ዜጋ እና ወገን ክርስቲያን ይሆን ዘንድ የተጠራበት ሰማያዊ ቤተሰብ እንደመሆኑ ቋንቋ፣ የትውልድ ሐረግና እና መኖሪያ አካባቢ በሥላሴ አርአያ የተፈጠረው የሰው ልጅ መለያያ ምክንያት ሊሆን አይችልም። ቅዱስ ጳውሎስ «አልቦ በዝንቱ አይሁዳዊ፣ ወአልቦ አረማዊ፣ ወአልቦ ነባሪ፣ አልቦ አግዓዚ፣ አልቦ ተባዕት ወአልቦ አንስት፤ ዳእሙ ኩልክሙ አሐዱ በኢየሱስ ክርስቶስ። አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።» ሲል ለሰብዐ ገላትያ (3፡28) እንደጻፈላቸው ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም በሰው ልጅ አንድነት ታምናለች ታስተምራለች። ከዚህ ውጪ የዚህ ብሔረሰብ፣ የዚህ ብሔር፣ የዚህ ቋንቋ ተናጋሪ እያሉ ሰውን ማቅረብና ማራቅ ከመንግሥተ እግዚአብሔር እና ከክርስትና ትምህርት መለየት ነው።
3ኛ. ኦርቶዶክሳዊነት ከድንበር እና ከክልል በላይ ነው። ከአራቱ የቤተ ክርስቲያን መገለጫዎች መካከል ማለትም «ቤተ ክርስቲያን አንዲት ናት፣ ቅድስት ናት፣ ሐዋርያዊት ናት፣ ዓለማቀዊት ወይም የሁሉ እና በሁሉ ያለች ናት» ከሚለው ውስጥ ዓለማቀፋዊነት (የሁሉ እና በሁሉ ያለች) የሚለው ነጥብ ክርስትና በዜግነት ብቻ ያልተከለለ መሆኑን ያሳየናል። ሐዋርያዊት ስለሆነችም እንደ ሐዋርያት ትምህርት ድሃውንና ባለጸጋውን፣ ገዢውንና ምንዝሩን፣ የሰማዩንና የምድሩን አንድ አድርጋ የምታስተዳድር፣ በሰዎች መካከል ልዩነትና ድንበር የማታበጅ ቤተ ክርስቲያን ናት።
4ኛ. ቤተ ክርስቲያናችን የዜግነት ድንበር የማያግዳት «የሁሉ እና በሁሉ ያለች» ብትሆንም ኢትዮጵያ ደግሞ በአምላክ ዘንድ የተወደደች፣ እንደ ሕጉ እና እንደ ተስፋ ቃሉ የኖረች፣ በቅዱሳን ኪዳተ እግር የተባረከች፣ እንደ ሰማይ ከዋክብት እንደ ምድር አሸዋ የበዙ ቅዱሳንን/ ቅዱሳትን ያፈራች ቅድስት አገራችን ናትና እምነታችንን ከአገራችን፤ አገራችንን ከእምነታችን ለይተን አንመለከትም። በእምነታችን ላይ የሚመጣ የአገራችን አደጋ እንደሆነ፤ በአገራችን ላይ የሚመጣ አደጋ ደግሞ የእምነታችን አደጋ እንደሆነ አበው አስተምረውናል። «ዳሯን እሳት መሐሏን ገነት» አድርግልን ብለው በጸሎት እንደጠበቋት ሁሉ የግዱ ቀን ሲመጣም ስለ አገራቸውና ስለ እምነታቸው ሰማዕትነት ለመቀበል ታቦታቸውን እና መስቀላቸውን ይዘው ከጦር አውድማ ውለው ውድ ሕይታቸውንም በሰማዕትነት እንደከፈሉት ሁሉ ለአገራችን ሰላምና አንድነት እኛነታችንን መስጠት እንዳለብን እንገነዘባለን።
5ኛ. ሁሉንም ከምድር አፈር ያበጀ፣ አእምሮውን ለብዎውን ያድላቸው ዘንድ በእስትንፋሱ ያጸናቸው አምላክ እርሱ ለማንም እንደማያዳላ ቅዱስ ጴጥሮስ «አማነ ርኢኩ ከመ ኢያደሉ እግዚአብሔር ለገጽ በኩሉ አሕዛብ። እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንደማያደላ በውነት አየሁ» (የሐዋ. 10፡34፤ ዘዳ 10፡ 17፤ 1ሳሙ 16፡7፤ ሮሜ 2፡11) ሲል ያስተማረውን አንገነዘባለን።
6ኛ. ይሁን እንጂ በስመ ክርስቲያን የምንጠራ ኦርቶዶክሳውያን ከዚህ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ርቀን፣ ይልቁንም በአሕዛብ እንኳን የሌለ መለያየት በመፍጠር፣ ሰዎችን በቋንቋቸው እና በዘር ሐረጋቸው በመውደድና በመጥላትፀ በመጥቀምና በመጉዳት ለአገራችንም ለሃይማኖታችንም ትልቅ የመሰናክል ድንጋይ አስቀምጠናል። ያለፈውን ዘመን ብንተወው እንኳን በዘመናችን ብቻ የመለየየታችን እና የመጠላላታችን ውጤት አገራችንን ለከፋ አደጋ የሚያጋልጥበት ድንበር ላይ አድርሶናል። እንደ ችግሩ ምንጭ ሁሉ መፍትሔውም ከሁሉም የሚጠበቅ ቢሆንም ለታሪካዊው የትግራይ ሕዝብ ግን እነሆ ፈታኝ ጥያቄ ሆኖ ቀርቦለታል።
በዚህም መሠረት፡-
1ኛ. የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተለይቶ የሚቀርበት አስከፊ የታሪክ አጋጣሚ እየተከሰተ መሆኑን በጥሙና እንዲገነዘብ፣
2ኛ. ላለፉት ሁለት እና ሦስት ሺህ ዓመታት አብሮ የኖረው ሕዝብ እና የሃይማኖት ቤተሰብ ከኤርትራ ጋር እንደተፈጠረው ያለ ፖለቲካዊ መለያየት እና መከፋፈል፣ እንዲሁም ከሌላው የሃይማኖት ወገኑ ተነጥሎ የመቅረት ዕዳ ሊወድቅበት እንደደረሰ እንዲያስታውስ፣
3ኛ. ለዚህም ክርስቲያኑ ተጋሩ በዋነኝነት የመከፋፈሉን ተግባር እየሠራ ያለውና በትግራይ ስም የሚነግደው የሕወሐት ቡድን መሆኑን አውቆ በደስታውም ይሁን በሐዘኑ ከእርሱ ከማይለየው ከቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር አብሮ እንዲቆም፣
4ኛ. በመንፈሳዊ እና በማኅበራዊ ሕይወቱ ዘወትር አብሮት ያለውን የቀሪውን ኢትዮጵያዊ ወገኑን የለትተዕለት ሰቆቃ፣ እስር፣ እንግልት፣ ከመሬትና ንብረት መፈናቀል፣ ግድያ እና ስደት የርሱም (የትግራይ ወገኑም) ሰቆቃ፣ እስር፣ እንግልት፣ከመሬትና ንብረት መፈናቀል፣ ግድያ እና ስደት መሆኑን አምኖ ለወገኑ ድምጹን እንዲያሰማ፣
5ኛ. አገሪቱ ውስጥ ፖለቲካዊ ነጥብ በማስቆጠር ይህንን የመከራ ዘመን ለማራዘም ደፋ ቀና የሚለውን ፓርቲ ኢ-ሃይማኖታዊ፣ ኢ-ባህላዊ እና ኢ-ኢትዮጵያዊ ጥሪ አልቀበልም በማለት ለነገው የትግራይ ተተኪ ትውልድ ግፍ እና ቂም እንዳይተርፍ እንዲያደርግ፣
6ኛ. ከሕወሐት ጋር በማበር የፓርቲውን የሰቆቃ ተግባር ከሚባርኩት በትግራይ ምእመን ስም በጵጵስና፣ በምንኩስና እና በክህነት ባለሥልጣንነት ከሚነግዱት ትግራዋዮች እንዲለይና እና ዘረኝነትን፣ ግፈኝነትን፣ ደም ማፍሰስን ከሚጠየፈው ከአማናዊው የተዋሕዶ ትምህርት ጎን በመቆም ቀሪ ኢትዮጵያዊ ወገኑን እንዲታደግ፣
7ኛ. የትግራዩ ወገናችን ሌላውን ኢትዮጵያዊ ወገኑን ሊያጠፋ እንደመጣ ጠላት አድርገው የሚነግሩትን የአገርና የሃይማኖት ተቃራኒዎች አልሰማም በማለት በቤቱ፣ ከራሱ ወንድሞች እና እህቶች ጋር በሚያውቀውና በሚረዳው አግባብ እንዲወያይ እና መፍትሔ እንዲያበጅ፣
8ኛ. በመላው አገሪቱ በተለይም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በየቀኑ የሚፈሰውን የንፁሐን ደም እንዲያስቆም፣
9ኛ. ማንኛውም ዜጋ ሊያገኘው የሚገባውን መብት፤ (ለምሳሌ በታመሙ ጊዜ ሕክምና የማግኘትን መብት)፤ ለተከለከሉ ወገኖች ጠበቃ እንዲሆን መጠየቅ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ እነሆ ጥሪውን አቅርበናል።
በፈሪሀ እግዚአብሔር ተቃኝቶ ለኖረው ለትግራይ ሕዝብ በሌላው ሕዝብ መከራ፣ ሞትና ስደት በመበልፀግ ላይ ያለ ቡድን ደጋፊ እና አጋር መስሎ እንደመታየት ልብን የሚያደማ ነገር እንደሌለ እንገነዘባለን። በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት የሚያስፀይፍ በደል የሚፈጽሙትን ሰዎች የሚቃወሙ አያሌ ትግራዋዮች (ትግሬዎች) እንዳሉ ግልጽ ቢሆንም የእነርሱ ዝምታ ክፉዎችን የልብ ልብ ሰጣቸው እንጂ ከድርጊታቸው ስላልመለሳቸው ድምጻቸውን እንዲያሰሙ መጠየቅ ግድ ብሏል።
ይህ ጥያቄ የትግራይ ሕዝብ የፈጸመው የተለየ ዕዳና በደል ስላለበት የቀረበ ጥሪ ሳይሆን እንደ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ኃላፊነቱ ሊወጣ የሚችለው ሚና ከፍ ያለ እንደመሆኑ ሳይደርቅ በርጥቡ፣ ሳይርቅ በቅርቡ መፍትሔ ይፈልግ ዘንድ ለማበከር ነው። ጌታም እንዳስተማረን «ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፥ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል።» (የሉቃስ ወንጌል 12፥48) እንዲል። ታቦተ ጽዮን በአክሱም ያረፈቸው እና ለአክሱማውያን የጠባቂነቱን ኃላፊነት እግዚአብሔር ባወቀ የተሰጠው ያለ ነገር አይደለም። የንጉሥ ካሌብ አጽም ያረፈበት ምድር፣ ተሰዓቱ ቅዱሳን መንፈሳዊ ተጋድሎ የፈጸሙበት፣ ቅዱስ ያሬድ የበቀለበት ምድር ሕዝብ ለሌላው ወገኑ ደራሽ፣ የኃዘኑ ተካፋይ እንዲሆን መጠበቅ ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይሆንም።
ስለዚህም ከምሥራቅ የኦጋዴን በረሃዎች እስከ ጋምቤላ፣ ከወልቃይት፣ ጠገዴና አፋር እስከ ኦሮሚያ ከተማና ገጠሮች ያለው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ሰቆቃ የሚገዳቸው እና ዕንባውን ሊያብሱለት የሚሹ፣ የተቃጣበትን ከባድ ጦር የሚያረግቡለት የትግራይ ወገኖቹን መፈለጉ ተገቢ የማይሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም።
ይህ በኢትዮጵያዊነት እና በተዋሕዶ ወገንተኝነት የቀረበ ጥሪ በጊዜያዊው የፖለቲካ ፀጉር ስንጠቃ ሳይመዘን በጎ ምላሽ እንዲያገኝ ምኞታችን ነው። በተለይም ቃለ እግዚአብሔርን በየአጥቢያቸው በመስማት ተኮትኩተው በማደግ ላይ ያሉ ወጣት የትግራይ ወንድሞች እና እህቶች ዘመኑ ያመጣው የመለያየት አባዜ ሰለባ ሳይሆኑ በአገራዊ አንድነት እና በሃይማኖታዊ ዜግነት ተጠልለው ራሳቸውንም ወገናቸውን ወደ አንድነት የሚመሩ የፍቅር መልእክተኞች እና መከራ በመቀበል ላይ ላለው ሌላው ወገናቸው የሚቆረቆሩ እንደሚሆኑ ተስፋ አለን።
በመጨረሻም፡- እግዚአብሔር በሰጠን ጊዜ ተጠቅመን ይህንን ሳናደርግ ብንቀር ግን መዘዙ የከፋ መሆኑን የሚያሳዩ የምጥ ጣር መጀመሪያ ምልክቶች መታየት መጀመራቸውን ሳይጠቅሱ ማለፍ የዚህን ጽሑፍ መልእክት ማጨንገፍ ይሆናል። የትግራይ ሕዝብ ያለበደሉ እና ያለ ኃጢአቱ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ደም ተቃብቶ፣ በጠላትነት ተፈርጆ፣ አንዳንድ ኅሊና ቢሶች እንደሚያደርጉትም ከትግራይ በመፈጠሩ ብቻ ከዘመኑ አጥፊዎች ጋር ተደምሮ የጥቃታቸው ዒላማ ሆኖ ሊታይ እንደሚችል ምልክቶቹ በይፋ ይታያሉ። ከአባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን እስከ ተሰዓቱ ቅዱሳን፣ ጻድቃን ከሚባሉት ከ500ዎቹ ቅዱሳን እስከ አባ ሰላማ መተርጉም፣ ከአቡነ አረጋዊ እስከ አባ ገሪማ ጻድቅ፣ ከቅዱስ ያሬድ እስከ አቡነ ተ/ሃይማኖት በበረከታቸው የጎበኙት ሕዝብ እና ምድር ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ በጥላቻ መጋረጃ ተሸፍኖ እንዳይቀር በእጅጉ ያሰጋል።
ስለዚህም በጎ ኅሊና ያላቸው የትግራይ ወገኖቻንን በሙሉ መልእክቱን በጥሙና ተመልክተው እንዲወያዩበት፤ በአገር ሽማግሌ፣ በተከበሩ አባቶች እና እናቶች ምክር ኢትዮጵያውያን በዘርና በቋንቋቸው እየተለያዩ የሚጠፋፉበትን ክፉ መርዝ እንዲያመክኑ፣ ለዚህም የትግራይ አንጋፋዎች የሰላም መልእክተኞች እንዲሆኑ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። ይህ መልእክት ለክርስቲያኑ በይፋ የቀረበ ቢሆንም በእምነት አንድ ባንሆን በዜግነት አንድ የሆንን ኢትዮጵያውያን በሙሉ ያለ እምነት እና ብሔረሰብ ልዩነት ለሰላም ጥሪ ለማድረግ የምንነሣበት እንዲሆን እንመኛለን። ከልባችን መልካም ነገር ለማድረግ ብንነሣ ደግሞ እሳተ መዓቱን በምሕረት ውኃው የሚያቀዘቅዝ አምላክ ለሰላም አልዘጋጅ የሚል ድንጋይ ልባችንን በሰላም ልብ ቀይሮ ሰላማዊ ልብ እንደሚሰጠን ምሉዕ እምነት አለን።
እግዚአብሔር አምላካችን አገራችንን እና ሕዝባችንን ከሚታየውና ከሚሰማው ክፉ ነገር ሁሉ ይሰውርልን፣

የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ወገኖቻችሁ ከመላው ዓለም

No comments:

Post a Comment

wanted officials