Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, August 23, 2016

በባህርዳር የተጀመረው ከቤት ያለመውጣት አድማ ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎ ዋለ

በባህርዳር የተጀመረው ከቤት ያለመውጣት አድማ ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎ ዋለ
ኢሳት (ነሃሴ 16 ፥2008)
በቅርቡ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የተፈጸሙ ድርጊቶችን በማውገዝ በተለያዩ ተቃውሞ ውስጥ የቆዩ የባህርዳር ከተማ ነዋሪዎች እሁድ የጀመሩት ከቤት ያለመውጣት አድማ ሰኞ ለሁለተኛ ቀን መቀጠሉን ለኢሳት አስታወቁ።
ህዝበ ውሳኔ ተላልፎበት ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኘው ይኸው አድማ የከተማዋ ነዋሪ በመንግስት የሚፈጸሙ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን በፅኑ ለመቃወም ያለመ መሆኑን ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ከዜና ክፍላችን ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
የከተማዋ ነዋሪ የወሰደውን አድማ ተከትሎ የባህርዳር ከተማ ሙሉ ለሙሉ ጭር ብላ የምትገኝ ሲሆን፣ አድማውን በጣሱ ሰዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ በነዋሪው ዘንድ ስምምነት መደረጉን እማኞች አስታውቀዋል።
ከቤት ያለመውጣቱንና የስራ ማቆም አድማውን በጣሱ ሰዎች ላይ እርምጃ እንዲወስድ እማኞች አስታውቀዋል።
ከቤት ያለመውጣቱና የስራ ማቆም አድማ መደረጉን ተከትሎ በባህርዳር ከተማ የሚገኙ የግልና የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሙሉ ለሙሉ ስራ አቁመው እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የከተማዋ ነዋሪ በመንግስት ላይ ያለውን ተቃውሞ ለመግለጽ አደባባይ በወጣ ጊዜ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት የሃይል እርምጃ በበህር ዳር ከተማ ብቻ ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።
በተመሳሳይ ሁኔታ በጎንደር ከተማ የተፈጸመን ግድያ በመቃወም የከተማዋ ነዋሪዎች ባለፈው ሳምንት የሶስት ቀን ከቤት ያለመውጣት አድማ ሲያደርጉ መቆየታቸውም የሚታወቅ ነው።
እሁድ በአማራ ክልል መዲና በሆነችው ባህርዳር ከተማ የተጀመረው ከቤት የለመውጣት አድማ እንዲያበቃ የመንግስት ባለስልጣናት የተለያዩ ቅስቀሳን ቢያደርጉም ነዋሪው እምቢተኛ መሆኑን ከነዋሪዎች ለመረዳት ተችሏል።
በባህር ዳር እና ጎንደር ከተሞች በመካሄድ ላይ ያሉ ሰላማዊ ተቃውሞዎች በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው በየከተሞቹ ያሉ ነዋሪዎች ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።
የተለያዩ አለም ቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በሁለቱ ክልሎች እየተካሄዱ ያሉ ተቃውሞዎች ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆናቸውን በመግለጽ ላይ ሲሆን ለወራት በኦሮሚያ ክልል ከዘለቀው ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በአጠቃላይ ከ500 በላይ ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን ሂውማን ራይትስ ዎች ይገልጻል።

 

No comments:

Post a Comment

wanted officials