Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, August 9, 2016

“ጠላታችን ህወሃት እንጂ የትግራይ ህዝብ አይደለም” አርበኞች ግንቦት 7



“ጠላታችን ህወሃት እንጂ የትግራይ ህዝብ አይደለም”
===============================
የህወሃትን አገዛዝ ለመቃወም ባለፈው ዕሁድ አደባባይ የወጣው የጎንደር ህዝብ ከፍ አድርጎ ሲያስተጋባቸው ከዋለው መፈክሮች አንዱ “ጠላታችን ህወሃት እንጂ የትግራይ ህዝብ አይደለም” የሚል ነበር።
ይህ መፈክር ህወሃት ባለፉት 25 አመታት የሥልጣን ዘመኑ ከትግራይ ውጪ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይ ህዝብንና ህወሃትን አንድ አድርጎ እንዲመለከት በዘረኝነትና በጥቅም በሰከሩ ጥቂት ተከታዮቹ አማካኝነት ሲቀነቀን የኖረውን ቅስቀሳ ዋጋ ያሳጣ ብቻ ሳይሆን ህወሃት ከሌለ የትግራይ ህዝብ አይኖርም ተብሎ በጭፍን ሲነዛ የሰነበተውን መሠረተ ቢስ ፕሮፖጋንዳ አከርካሪ የሰበረ ነው። ህወሃት ስልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ በህዝባችንና በአገራችን ላይ የፈጸማቸው ወንጀሎች የትግራይን ህዝብ በጅምላ ተጠያቂ ሊያደርግ የሚችልበት ህጋዊም ሆነ ሞራላዊ አመክንዖ እንደሌለ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል። “እኔ ከሌለሁ አማራው ወይም ኦሮሞው በጠራራ ጸሃይ ያጠፋሃል ወይም ይበቀልሃል” በሚል ቅስቀሳ የትግራይን ህዝብ መደበቂያ ዋሻ ለማድረግ የሚደረገው ሙከራ ህወሃት በመሣሪያ ትግል ላይ በነበረበት 17 አመታት በትግራይ ህዝብ ላይ የፈጸማቸውን ወንጀሎች ለማድበስበስና ለማዘናጋት ካልሆነ በቀር ለምንም ፍጆታ ሊውል የሚችል ነገር አይደለም። በዚያ የ1977 ደርቅ ወቅት አለም አቀፍ ለጋሾች በህወሃት ቁጥጥር ሥር ለነበሩ የትግራይ ወረዳዎች እንዲከፋፈል የሰጡትን የነፍስ አድን እርዳታ እህል እነ መለስ ዜናዊ፤ ስዩም መስፍን፤ ስብሃት ነጋ እና ብርሃኔ ገብረኪርስቶስ የመሳሰሉ የህወሃት መሪዎች በምን አይነት ማጭበርበር ከረሃብተኛው ጉሮሮ በመቀማት በአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር በሱዳን በኩል ወደውጪ ልከው እንደሸጡና ድርጅታቸውን በመሳሪያና በሎጄስቲክ እንዳጠናከሩበት በዚህም የተነሳ በተላከላቸው የምግብ ዕርዳታ ህይወታቸው ይድን የነበሩ ብዙ ሺህ የትግራይ ተወላጆች በረሃብ እንደቅጠል እንደረገፉ የትግራይ ህዝብም ሆነ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚረሳው ጉዳይ አይደለም። ለርካሽ የፖለቲካ ዓላማ የትግራይን ህዝብ ለማነሳሳትና ከጎኑ ለማሰለፍ ሲባል ብቻ ለደርግ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ገበያ የወጣ ሠላማዊ የሃውዜን ነዋሪዎች በአገሪቱ አየር ሃይል በግፍ እንዲጨፈጨፉ ህወሃት የተጫወተው ሚና በፕሮፖጋንዳ መሣሪያዎች ብዛትና የካድሬዎች ጋጋታ ከታሪክ ማህደር የሚፋቅ አይሆንም። ሌላው ህወሃት በትግራይ ህዝብ ላይ ከፈጸማቸው መልከ ብዙ ክህደቶች ሳይገለጽ መታለፍ የሌለበት “ከደርግ ጋር አብራችኋል” የተባሉ የትግራይ ተወላጆች ቤተሰቦች የደረሰባቸው ስቃይና እንግልት ፤ እንዲሁም ህወሃት በኢትዮጵያና በታሪኳ በተለይም በአማራው ህዝብ ላይ ያለውን የጥላቻ ፖለቲካ የተቃወሙ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶች የራሳቸውን መቀበሪያ ጉድጓድ እንዲቆፍሩ ተደርገው የተፈጸመባቸው ዘግናኝ ጭፍጨፋ አንዱ ነው። እንዲህ አይነት ኢሰብአዊና ዘግናኝ እርምጃዎችን በትግራይ ተወላጆች ላይ እየፈጸመ ለሥልጣን የበቃ ሃይል ዛሬ የፖለቲካ አላማውንና ከመንግሥት ሥልጣን የተገኘ ጥቅሙን እንዲያስከብሩለት ትግሪኛ ተናጋሪዎችን እየፈለገ በመንግሥት ሥልጣንና በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ሃላፊነት ቦታዎች ላይ በብዛት ስለመደበ ወይም ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ ጥቂት የትግራይ ተወላጆች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ዘርፎችን እንዲቆጣጠሩት ስለአደረገ የትግራይ ጥቅም አስከባሪ ወኪል ተደርጎ ሊቆጠር አይችልም ። ህወሃት እራሱን የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ነኝ ስላለ ብቻ የትግራይ ህዝብ ተወካይ የሚያደርገው ህጋዊ ወይም ፖለቲካዊ ድንጋጌ እንደሌለ ማንም አይዘነጋም ። የኢትዮጵያ ህዝብ በጠባብ አላማ የተሰባሰቡ ጥቂት የትግራይ ተወላጆች በህወሃት ሥም ተደራጅተው የአገራችንን በትረ ሥልጣን ከተቆጣጠሩበት ጊዜ ጀምሮ በህዝባችንና በአገራችን ላይ ለፈጸሟቸው ወንጀሎችም ሆኑ በትግሉ ወቅት በትግራይ ወገኖቻችን ላይ ላደረሱት ጥቃት የጊዜ ጉዳይ ካልሆን በቀር በህግ ይፋረዳቸዋል። ያን ጊዜ ተጠያቂ የሚሆኑት ድርጅቱን እንመራለን የሚሉና በተዋረድ የመንግሥትን ሥልጣን የተቆጣጠሩ ህግ አውጭዎች ህግ አስከባሪዎችና በአስፈጻሚነት ላይ ያሉት ብቻ ይሆናሉ። ህወሃት ዛሬ የሚመካበት የሠራዊት ብዛትና የመሳሪያ ጋጋታ በምንም ተአምር ያንን የፍርድ ቀን የሚያስቀር አይሆንም ።
ህዝባችንን ለመግዛት መለኮታዊ ሥልጣን እንዳላቸው ቤቴ እምነቶች ሳይቀሩ ሲያስተምሩላቸው የነበሩ የቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ መንግሥት ከአመት ባነሰ ዕድሜ እንዴት እንደተንኮታኮተ እናስታውሳለን። በሠራዊትና በመሳሪያ ብዛት ብቻ ሳይሆን በወታደራዊ ሳይንስ ብቃቱ በአፍሪካ ተወዳዳሪ ያልነበረው የደርግ ዘመን ሠራዊትም በምን ፍጥነት እንደተበተነ እናውቃለን። ከዚህ ሁሉ ልምድ ትምህርት ለመቅሰም ያልታደለው ህወሃትም አወዳደቁ ከዚህ ያልተለየ ምናልባትም የከፋ ሊሆን እንደሚችል ለመናገር ነቢይ መሆንን አይጠይቅም። ድርጅቱን ከምሥረታው ጀምሮ ያቋቋሙና ለድል ያበቁት ተሰናባች የህወሃት መሪዎቹ በግለሰብ ደረጃ እየመሰከሩ ያለው ሃቅም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው ።
“ጠላታችን ህወሃት እንጂ የትግራይ ህዝብ አይደለም” በማለት የጎንደር ህዝብ ሃምሌ 24 ከፍ ብሎ ሲያስተጋባ
የዋለው መፈክር የመላው ኢትዮጵያዊያን መፈክር እንደሆነ ህወሃት በከፈተው የጥቅም ቦይ ያልተወሰደ የትግራይ ህዝብ ሁሉ በሚገባ ይገነዘባል። የዚህን መፈክር እውነታነት የሚጠራጠሩ በመንግሥትና የህዝብ ሃብት ዘረፋ የከበሩና የሰረቁትን ገንዘብ ማሸሺያ የሚጨንቃቸው ከትግራይ ሰፊው ህዝብ የተገነጠሉ የትግራይ ተወላጆችና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው ብቻ ናቸው። መላው የትግራይ ህዝብ እንደተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ የህወሃት አገዛዝ ይብቃ እያለ መሆኑን በነአብረሃ ደስታ ላይ የተፈጸመው ግፍ ማስረጃ ነው
አርበኞች ግንቦት 7 የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ያነሳውን የማንነት ጥያቄ አስመልክቶ ጎንደር ላይ የተደረገው ሠላማዊ ሰልፍ በመላው አገራችን ላይ ከፈጠረው መነቃቃት በተጨማሪ ለህወሃት መሪዎች ያስተላለፈው ትልቅ መልዕክት እንዳለ ያምናል። ይህ መልዕክት ትዕግሥት እውቀት እንጂ ፍርሃት አለመሆኑን የሚገልጽ መልዕከት ነው። ህወሃት ሺ ጊዜ የሚመካበት የጦር መሳሪያና የሠራዊት ብዛት ህዝብ ለነጻነቱ የሚያደርገውን ተጋድሎ ሊያስቆም እንደማይችል ከራሱ ተሞክሮ ማወቅ ነበረበት ። ህዝብ በሠላማዊ መንገድ ነጻነቱን ለማስከበር የሚያቀርበውን ጥያቄ ህወሃት በለመደው እብሪት በሃይል ለመቀልበስ በሚያደርገው እርምጃ በሰው ህይወትም ሆነ በንብረት ላይ ሊደርስ በሚችለው ጉዳት ተጠያቂው ህወሃት ብቻ እንደሆነ አርበኞች ግንቦት 7 ያስጠነቅቃል። በዚህም ምክንያት በኦሮሚያ ውስጥ በወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለው ግዲያ በአስቸኳይ እንዲቆምና በጎንደርና በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እየቀረበ ያለው የመብት ጥያቄ በአስቸኳይ ምላሽ እንዲያገኝና አገራችን ከገባቺበት የፖለቲካ አጣብቂኝ እንድትወጣ የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት የተጀመረው ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል አርበኞች ግንቦት 7 ለመላው የአገራችን ህዝብ የትግል ጥሪ ያቀርባል። የህወሃት የአፈና አገዛዝ ላለፉት 25 አመታት በህዝባችን ጫንቃ ላይ እንዲንሰራፋ ፖለቲካዊ ፤ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ ሲያደርጉ የኖሩ ምዕራባዊያን መንግሥታትና የወይኔ ደጋፊዎች ድጋፋቸው በአገሪቱ ላይ ሊያመጣ የሚችለውን ጉዳት ቆም ብለው እንዲያስቡና አሰላለፋቸውን እንዲያስተካክሉ በዚህ አጋጣሚ ንቅናቄያችን ያሳስባል።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ

No comments:

Post a Comment

wanted officials